አሶሳ:- በቤኒሻንጉል ክልል የነበረው የሠላም መደፍረስ፣ የፀጥታ ችግርና የደህንነት ስጋት በተደረጉ ከፍተኛ ሰላምና ፀጥታን የማስፈን ሥራዎች ተወግዶ ክልሉ ሙሉ ለሙሉ ወደ ነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ መመለሱ ተገለጸ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በፅህፈት ቤታቸው በሰጡት ማብራሪያ እንደገለፁት፤ ጥቅሜ ተነካ በሚሉ ሃይሎች ቀስቃሽነት ተጀምሮ የነበረው ክልሉን የመረበሽ፣ የሕዝቡን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የመጣል ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ዛሬ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል።
እንደ ርእሰ መስተዳድሩ ማብራሪያ የለውጡን መምጣት ተከትሎ ጥቅሜ ይቀራል በሚል ያኮረፉና ወደ ጦርነት ሳይቀር የገቡ ኃይሎች የነበሩ ሲሆን፣ እነዚህ ኃይሎች የፈጠሩት ቀውስ በክልሉ ሰላም እንዲደፈርስ አድርጎ ቆይቷል። ይሁን እንጂ፣ በተከፈለው ውድ መስዋእትነት አሁን በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ሊገኝ ችሏል።
በአሁኑ ሰአት በየትኛውም የክልሉ አካባቢዎች በነፃነት መንቀሳቀስ የሚቻል መሆኑን የገለፁት አቶ አሻድሊ ሀሰን የተወሰኑ ችግሮች ያሉት ከአጎራባች ክልሎች ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች ሲሆን፣ እነሱንም ከየክልሎቹ መስተዳድሮችና የሥራ ሃላፊዎች ጋር በመገነጋገር ለመፍታት እየተሞከረ መሆኑን ተናግረዋል።
“በአጎራባች ክልሎች አሁንም የፀረሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴዎች አሉ፤ ይህ ደግሞ የሸቀጥ ምርችን ከማሳለጥ አኳያ የራሱ የሆነ ችግር ፈጥሯል። ልማት ላይ ሳይቀር እንቅፋት እየሆነ ነው ያለው። ሁሉም በእርግጠኝነት በቅርቡ መፍትሄ ያገኛል ብዬ አስባለሁ” ሲሉም አቶ አሻድሊ ተናግረዋል።
ክልሉ የተከሰተውን የሠላም እጦት፣ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ሁሉ ወደ አንፃራዊ ሠላም በመመለስ ለውጥና ብልፅግናን የማምጣት ጉዞውን የተያያዘው መሆኑን የገለፁት ርእሰ መስተዳድሩ ያለ ምንም ዓላማ አኩርፈው ጫካ ለገቡት፣ ወደ ጎረቤት ሀገር በመሄድ ተመልሰው ሀገራቸውን ሲወጉ ለነበሩት ቡድኖች ተከታታይ የሰላም ጥሪ በማድረግ፤ ለጠረጴዛ ውይይት በመጋበዝና ″ችግሮች″ በተባሉት ላይ በግልፅ በመወያየት ከ90 በመቶ በላይ ጫካ ገብተው የነበሩ ሰዎችን ወደ ሰላም ማምጣትና በማደራጀት በክልሉ ልማት ውስጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የተቻለ መሆኑን፤ ይህም ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል አንዱና ትልቁ ስኬት መሆኑንም አስረድተዋል።
“ክልሉ የጠረፍ አካባቢ እንደመሆኑ መጠን፣ ረዘም ላለ ጊዜ የፀጥታ ችግር ውስጥ መቆየቱ ጎድቶናል። አሁን አንፃራዊ ሰላም አግኝተናል። የመልሶ ግንባታ ሥራዎችንም በተሻለ እየሠራን እንገኛለን” የሚሉት አቶ አሻድሊ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም ከፌዴራል መንግሥት፣ ከጀግናው መከላከያ ሠራዊት፤ እንዲሁም የአስተዳደር ወሰን ከሚጋሯቸው ክልሎች መስተዳድሮች ጋር በጋራ በመሥራት ላይ መሆናቸውንም በወቅታዊ ሁኔታ ገለፃቸው ወቅት አንስተዋል። በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ጽሕፈት ቤት አቋቁመው በመሥራት ላይ እንዳሉም ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ሁሉ እንደ ክልልም እኛንም ፈተና ውስጥ የከተቱን በርካታ የሰላም እጦት ችግሮች አጋጥመውናል። በተለይ የሰላም ማጣት ከፍተኛ ፈተና ሆኖብን ነበር። ይሁን እንጂ፣ በዛ ውስጥ ሆነን ነው ብልፅግናን ማምጣት የቻልነው ብለዋል።
ግርማ መንግሥቴ
የብልፅግና መንግሥት ችግሮችን፣ ፈተናዎችን ወደ እድሎች መቀየር የሚችል መንግሥት በመሆኑ እነዛን ሁሉ አልፈን ነው እዚህ ውጤት ላይ ለመድረስ የቻልነው የሚሉት አቶ አሻድሊ በእርግጠኛነት መናገር የሚቻለው የሰላም ችግሮቻችንን ሙሉ ለሙሉ ካስወገድን በጥቂት ዓመታት ውስጥ የፈለግነው የብልፅግና ምእራፍ ላይ እንደርሳለን። ራሳችንን ከመቻልም አልፈን ለሌላውም በመትረፍ የሀገራችንን ብልፅግና እውን እናደርጋለን በማለት ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም