መጠኑ የጨመረ የፕሮስቴት ዕጢ የሚያሳያቸው ምልክቶች ይህን ይመስላሉ።
– ሽንት ቶሎ ቶሎ ማለት በቀንም በለሊትም
– ሽንትን ለመሽናት መቸገር(ማስማጥ)
– ሽንትን መቋጠር አለመቻል
– ሽንትን መቆጣጠር አለመቻል(ማምለጥ)
– ከሽንት ጋር ተደባልቆ የሚወጣ ደም መኖር
– ስንፈተ ወሲብ ወይም የወንድ ልጅ ብልት በፆታዊ ግንኙነት ወቅት ለመቆም መቸገር
1) ፕሮስቴት ምንድነው?
ፕሮስቴት ማለት በወንዶች ላይ ብቻ የሚገኝ መጠኑ አነስተኛ የሆነ ፈሳሽ አመንጪ የወንዶች መራቢያ አካል ክፍል ነው። በውስጡ ሽንትን የሚያሳልፍ ቀጭን የሽንት ቱቦ ሲኖረው ከሽንት በተጨማሪ የወንድ ልጅ የዘር ፍሬ ፈሳሽን (Semen) ለማስተላለፍ ይጠቅማል።
2) የፕሮስቴት ካንሰር ምንድነው? እንዴትስ ይከሰታል?
የፕሮስቴት ካንሰር ከፕሮስቴት ዕጢ መነሻውን ሲያደርግ አብዛኛውን ግዜ ዕጢውን ከሚሰሩት ፈሳሽ አምራች ክፍሎች ላይ ይነሳል።(Acinar Adenocarcinoma) ብዙዎቹ የፕሮስቴት ካንሰሮች ቀስ ብለው የሚያድጉ እና ዕድገታቸውም በፕሮስቴት ዕጢ ውስጥ የሚወሰን ነው። አንዳንድ ግዜ ግን በጣም በፍጥነት አድገው ወደ ሌላ የሰውነት ክፍል ሊሰራጩ ይችላሉ‼️
3) ስንት አይነት የፕሮስቴት ካንሰር አለ?
በትንሹ አምስት አይነት የፕሮስቴት ካንሰሮች አሉ። እነሱም:-
ሀ) አሲናር አዴኖካርሲኖማ
በጣም በብዛት የሚታየው የፕሮስቴት ካንሰር አይነት ሲሆን 90% ያክል የካልላል።
ለ) ደክታል አዴኖካርሲኖማ
ይሄኛው ዕድገቱ በጣም ፈጣን የሚባል የፕሮስቴት ካንሰር አይነት ነው።
ሐ) ትራንዚሽናል ሴል ካንሰር(ዩሮቴሊያል)
ይሄኛው አይነት ካንሰር መነሻውን ከሽንት ቀጭን ቱቦ ማለትም Urethra ላይ ያደርጋል። ይህም አነሳሱን ከፕሮስቴት በላይ ከሚገኘው የሽንት ፊኛ ወደ ፕሮስቴት የተዛመተ እንዲሆን ያደርገዋል።
መ) ስኳመስ ሴል ካንሰር
ይሄኛው አይነት ካንሰር መነሻውን ጠፍጣፋ ከሆኑ የፕሮስቴት ህዋሶች ሲያደርግ ዕድገቱም ፈጣን የሚባል ነው።
ሠ) ስሞል ሴል ካንሰር
ይሄኛው ካንሰር መጥፎ የሚባል አይነት ሲሆን የስርጭት መጠኑም ሁለት ፕርሰንት ብቻ ነው።
4) የፕሮስቴት ካንሰር በደረጃ መጠኑ እንዴት ይከፈላል?
በሶስት ደረጃዎች ሲከፈል እነሱም፦
I) ፕሮስቴትን ብቻ የሚያማክል የፕሮስቴት ካንሰር
II) ከፕሮስቴት ዕጢ በተጨማሪ አካባቢው ላይ ወደሚገኙ የወንድ ልጅ መራቢያ ክፍሎች፣ የሽንት እና የሰገራ ቱቦዎች የተዛመተ የፕሮስቴት ካንሰር
III) ከፕሮስቴት ዕጢ ተነስቶ በመላው የሰውነት ከፍል የተሰራጨ የፕሮስቴት ካንሰር ናቸው።
5) የፕሮስቴት ካንሰር ምልክቶች ምን ምን ናቸው?
ፕሮስቴት ካንሰር ሲጀምር ምንም አይነት ምልክቶችን አያሳይም። በዚህም ምክንያት የዕጢው መጠን በጣም ካልጨመረ በቀር በበሽታው የተያዙ ሰዎች ምልክቶቹን አይተው ወደ ህክምና ቦታ የመምጣት ዕድላቸው አነስተኛ ነው። መጠኑ የጨመረ የፕሮስቴት ዕጢ የሚያሳያቸው ምልክቶች ይህን ይመስላሉ።
– ሽንት ቶሎ ቶሎ ማለት በቀንም በለሊትም
– ሽንትን ለመሽናት መቸገር(ማስማጥ)
– ሽንትን መቋጠር አለመቻል
– ሽንትን መቆጣጠር አለመቻል(ማምለጥ)
– ከሽንት ጋር ተደባልቆ የሚወጣ ደም መኖር
– ስንፈተ ወሲብ ወይም የወንድ ልጅ ብልት በፆታዊ ግንኙነት ወቅት ለመቆም መቸገር
እነኚህን ምልክቶች የታየው ግለሰብ በአፋጣኝ በኩላሊት እና የሽንት ፊኛ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሐኪሞች(Urologist) መታየት ይኖርበታል። ነገር ግን ምልክቶቹ ሙሉ በሙሉ የካንሰር በሽታን ያሳያሉ ማለት አይደለም‼️
6) የፕሮስቴት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ምንድነው?
ቅድመ ምርመራው በዋነኝነት ሁለት ምርመራዎችን ያካትታል። እነሱም፦
ሀ) የፕሮስቴት ዕጢ ፈሳሽ የደም ውስጥ ልኬት (Prostate Specific Antigen)
ይህ ፈሳሽ በውስጡ ፕሮቲን የያዘ ሲሆን የዚህ ፈሳሽ ፕሮቲን መጠንም በቀላሉ በደም ውስጥ መለካት ይቻላል። በመጠኑም ቢሆን በጤነኛ ወንዶች ደም ውስጥ የሚገኝ ሲሆን መጠኑ በጣም ሲጨምር ግን የፕሮስቴት ካንሰር መኖሩን ያመለክታል።
ለ) በፊንጢጣ በኩል ጣትን በማስገባት በስፔሻሊች ሐኪሙ የሚደረግ የፕሮስቴት ዕጢ ዳሰሳ ምርመራ(Digital Rectal Examination)
ይህ የፕሮስቴት መጠን ልኬት በጣም አስፈላጊ እና የፕሮስቴትን መጠን፣ ልስላሴ ወይም ሻካራነት እንዲሁም የካንሰሩን ደረጃ በተወሰነ መጠን የሚተነብይ ነው። የሁለቱ ቅድመ ምርመራዎች ግብረ መልስ ለሐኪሙ መንደርደሪያ ሆነው የታካሚውን የወደፊት ዕጣ ይወስናሉ።
7) የፕሮስቴት ካንሰር ስርጭት ምን ያክል ነው?
በተለምዶ የፕሮስቴት ካንሰር የአዛውንቶች ካንሰር በመባል ይታወቃል። የዚህም ምክንያት በበሽታው ከሚያዙት ወንዶች ውስጥ ግማሽ ያክሉ ከሰባ አመት በላይ የሆናቸው ስለሆኑ ነው። ፕሮስቴት ካንሰር በወንዶች ላይ ከሚከሰቱ ካንሰሮች በግምባር ቀደምተኝነት ካሉት ውስጥ ይመደባል። እንደ ኤሮፓ አቆጣጠር በ2020 ብቻ በዓለም ላይ 1.4 ሚሊዮን አዲስ የፕሮስቴት ካንሰር ታካሚዎች እንደተገኙ ሳይንሳዊው ትንበያ ያመለክታል። በዛው ዓመት የሟቾች ቁጥር ወደ ሶስት መቶ ሰባ አምስት ሺህ(375,304) ይገመት ነበር። እንደ አለም አቀፉ የካንሰር አጥኚ ቡድን (GLOBOCAN) ከሆነ በኢትዮጵያ የፕሮስቴት ካንሰር ምጣኔ በአንድ ዓመት ብቻ 2720 ነበር። ይህም በፕርሰንት ሲቀመጥ 10.2% ይደርስ ነበር‼️
8) የፕሮስቴት ካንሰር መንስኤዎች ምንድናቸው?
መንስኤዎቹ ይሄ ነው ተብለው ባይቀመጡም አጋላጭ ሁናቴዎቹ ግን እንዲህ ተዘርዝረዋል።
– ዕድሜ – ዕድሜያቸው ከሀምሳ በላይ የሆነ ጎልማሶች ለበሽታው የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው።
– ዘር – ጥቁር ወንዶች ከነጮች በበለጠ ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው።
– ቤተሰብ(Genetic – መራሄ) – በቤተሰብ አባት፣ ወንድም፣ ልጅ ወይም አጎት የተጠቃ ከሆነ ከሌላው ማህበረሰብ የበለጠ የመተላለፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው።
– የክብደት መጠናቸው ከፍ ያሉ ወንዶች(Obesity)
– በቁመት ዘለግ ያሉ ወንዶች(Tall Stature)
– የሆርሞን መዛባት – በተለይም ኢንሱሊን መሳይ የዕድገት ሆርሞን ከልክ በላይ መጨመር(Insulin like growth factor)
– የፕሮስቴት ዕጢ መቁሰል(Inflammation)
– ካድሚየም ለተባለው ኬሚካል ተጋላጭ የሆኑ ወንዶች – ሲጋራ ማጨስ + ለፋብሪካ ኬሚካሎች መጋለጥ።
9) የፕሮስቴት ካንሰር እንዳለ እንዴት ይታወቃል?(Diagnosis)
የህክምና ታሪክን በመጠየቅ እንዲሁም ጠቅላላ የሰውነት ምርመራን በማድረግ‼️
ሐኪሙ አስፈላጊውን የህክምና ታሪክ ከጠየቀበኋላ የፕሮስቴት ዕጢን ከመመርመር ጀምሮ ሙሉ የሰውነት እና የላብራቶሪ ምርመራዎችን ያደርጋል። የፕሮስቴት ካንሰር የሚመስል ነገር ካለ የደም ምርመራ እንዲሁም የፕሮስቴት ዕጢ የአልትራሳውንድ ምስል ምልከታ ምርመራ እና የናሙና ምርመራ ያደርጋል።
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ የበሽታውን ደረጃ ለማወቅ የተለያዩ የምስል ምልከታ ምርመራዎች ይደረጋሉ። እነሱም የሆድ አልትራሳውንድ፣ የደረት እና የአጥንት ራጅ፣ የሆድ እና የዳሌ MRI, PET scan, CT scan እና የመሳሰሉት ናቸው።
10) የፕሮስቴት ካንሰር ህክምና ምን ይመስላል?
ህክምናው በካንሰሩ የደረጃ መጠን ላይ ተመርኩዞ ሲደረግ የኩላሊት እና የሽንት ፊኛ ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስቶች + የካንሰር ስፔሻሊስት ጠበብቶች + ጠቅላላ ቀዶ ጥገና ሐኪሞች ባሉበት ውይይት ተደርጎ ውሳኔ ይሰጣል። ህክምናው በደረጃው መሰረት፦ ከክትትል ጀምሮ ቀዶ ጥገናን፣ የጨረር ህክምናን፣ የሆርሞን መዛባት ህክምናን፣ በደምስር የሚሰጥ የኬሞቴራፒ ህክምናን ጨምሮ አዳዲስ በመጡ ካንሰሩን ብቻ በሚገድሉ ህክምናዎች(Targeted therapy,Immunotherapy drugs) ይደረጋል። በሽታው ጨምሮ ከተገኘ ደግሞ ታካሚውን በህይወት የማቆየት እና ህመሙን የማቅለል(Palliative Care) ህክምና ይሰጣል‼️
ዶ/ር ሚካኤል ሻውል ለማ
በካንሰር ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር
ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ
ቲክ ቶክ ገፅ – doctormichael12
ቴሌግራም – t.me/drmichaelshawel1221
ስልክ ቁጥር – 0904640890
የስራ ቦታ: ህይወት ፋና ሆስፒታል