ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን በመውረሯ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በ1942 ዓ.ም ባደረገው ሥብሠባ ሰሜን ኮሪያ የጠብ ጫሪነት ተግባሯን በአስቸኳይ እንድታቆም አስጠነቀቀ።
ሰሜን ኮሪያ ግን ውሳኔውን ወደ ጎን በመተው ወረራዋን አስፍታ ቀጠለችበት። የጸጥታው ምክር ቤትም ለዓለም ሰላም ሲባል በአባል ሀገራቱ ብርቱ ክንድ ወረራው እንዲቀለበስ ወሰነ። በዚህም መሠረት ውሳኔውን የደገፉ አሥራ ስድስት ሀገሮች ወታደሮቻቸውን ለመላክ ወሰኑ፡፡
ኢትዮጵያም ከአሥር መድፈኛ ሻለቃ ተውጣጥቶ የተመሠረተ ቃኘው ሻለቃን ለመላክ ወሰነች፡፡ ሚያዚያ አምስት ቀን 1943 ዓ.ም ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ባሉበት የቃኘው ሻለቃ አባላት ችሎታቸውን በመስክ ትርዒት አሳዩ።
ንጉሡም “እነኾ በጋራ ደኅንነት መርሕ መሠረት እጅግ ቅዱስ ለኾነው ለዓለም ሰላም ዘብ ልትቆሙ የዓለምን ግማሽ የሚኾን ጉዞ ትጓዛላችሁ፤ ሂዱ እና ወራሪዎችን ድል ንሷቸው፤ በኮሪያ ልሳነ ምድርም ሕግና ሥርዓትን አስከብሩ” በማለት ሰንደቅ ዓላማ አስይዘው ሸኟቸው፡፡
አትዮጵያ በአምስት ዙር 6 ሺህ 37 ወታደሮችን አዝምታለች። ሴቶችም ወደ ኮሪያ መዝመታቸው ተዘግቧል።
የኢትዮጵያ ጦር ደቡብ ኮሪያ ሲደርስም የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲንግ ማን በደስታ ተቀበሏቸው። የቃኘው ሻለቃ ከአፍሪካ የሄደ ብቸኛው ጦርም በመኾኑ ውዳሴ ተቸረው፡፡
ይህ የኢትዮጵያ ጦር በኮሪያ ምድር ከዘመቱ የተለያዩ ሀገራት የጦር ምድቦች ሁሉ የተሰጣቸውን ሁሉንም ግዳጅ በድል የተወጣ ብቸኛው ጓድ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ አንድም ወታደር ያልተማረከባት ብቸኛ ሀገር በመኾን ጀግንነቷን ለዓለም ሕዝብ አስመስክራለች።
የኮሪያ ጦርነት በሐምሌ ወር 1945 ዓ.ም በስምምነት ተጠናቀቀ። በቻይና እንዲሁም ሶቭየት ኅብረት በምትረዳው ሰሜን ኮሪያ እና በአሜሪካ እና በሌሎች 15 ሀገሮች በተደገፈችው ደቡብ ኮሪያ መካከል ድንበር ተሠመረ።
ከጦርነቱ በኋላም የቃኘው ሻለቃ አባላት ለሦስት ዓመታት በኮሪያ ምድር በተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኀይል ሥር ሰላም እያስከበሩ ቆይተዋል።
በመጋቢት ወር 1948 ዓ.ም የቃኘው ሻለቃ አባላት ለመጨረሻ ጊዜ የኮሪያን ልሳነ ምድር ለቆ ሲወጣ በደቡብ ኮሪያ ሕዝብ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የጦር ሜዳ የጀግና ኒሻን ተሸልሟል፡፡
በኮሪያ ዋና ከተማ ሴኡል ውስጥ ናምዮንግ ዶንግ ዮንግሳን ጉ በሚገኘው የጀግኖች መታሰቢያ አደባባይ ላይ በጦርነቱ ለወደቁት የኢትዮጵያ ወታደሮች የመታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡
ሰሜን ኮሪያ ታዲያ ደቡብ ኮሪያን የወረረችው በዚህ ሳምንት ሰኔ 17 ቀን 1942 ነበር፡፡ ሰዋሰው ዶት ኮም ድረ ገጽን እና የኢትዮጵያ ታሪክ በሩቅ ምሥራቅ መጽሐፍን በምንጭነት ተጠቅመናል፡፡
👉የኢቦላ መከሰት
የኢቦላ ቫይረስ ገዳይ በሽታ ነው። ይህ በሽታ ከሰው ወደ ሰው እንዲሁም ከእንስሳት ወደ ሰው ይተላለፋል። በሽታው የሚያሳየው ምልክት ከባድ ትኩሳት፣ የሰውነት ድካም፣ ራስ ምታት፣ ማስመለስ እና የኩላሊት ህመም ነበር።
በዚህ በሽታ የተያዘ ሰው የመትረፍ ዕድሉ አነስተኛ እንደኾነ ነው የዓለም የጤና ድርጅት የሚገልጸው። ዋነኛ የመከላከያ መንገዱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን እና እንስሳትን አለመንካት እንደኾነ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ኢቦላ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ኡጋንዳ ውስጥ ነው፡፡ የበርካታ ሰዎችን ሕይወትም መቅጠፉን ልብ ይሏል፡፡ የኢቦላ ቫይረስ ስያሜውን ያገኘው ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ከሚገኘው የኢቦላ ወንዝ ነው፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚጠቁመው በሽታው ዴሞክራቲክ ኮንጎን ጨምሮ በፍጥነት ወደ ኮትዲቯር፣ ደቡብ አፍሪካና ጋቦን መስፋፋቱ ይታወሳል፡፡
የአሶሼትድ ፕሬስ መረጃ እንደሚያመለክተው የኢቦላ ቫይረስ በሱዳን ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በዚህ ሳምንት ሰኔ 19 ቀን 1970 ዓ.ም ነበር፡፡ በወቅቱም የበሽታው ምንነት በውል ባለመታዎቁ በርካታ ሱዳናውያንን ቀጥፏል፡፡
ሳምንቱ በታሪክ (አሚኮ)