1) በየአራት ሴኮንዱ አንድ ሰው በአለም ላይ እስትሮክ ያጋጥመዋል፤
2) በየአራት ደቂቃው በስትሮክ አንድ ሰው ሒወቱን ያጣል
3) ከአራት ሰዎች በሒወት ቆይታቸው አንደኛው ላይ እስትሮክ ይከሰታል
4)በአራት ወር ውስጥ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በእስትሮክ ይያዛሉ
ዛሬም እስትሮክን ለሌላ ለማይታይ ለማይጨበጥ ሐይል ሰጥተን ተቀምጠናል። እስትሮክ ከስራ ገበታ በማስተጓጎል በአለም ሶስተኛ የህመሞች ቁንጮ ላይ እንዲቀመጥ የተደረገው በሰው ልጆች ዝምታ ነው።
ከ90% በላይ የሚሆኑትን የእስትሮክ መንስኤዎች በመከላከል መርህ መግታት ይቻላል። ይኸን የአንጎል አካላዊ ህመም ከማከም መከላከል በእጅጉ ቀላል እና ውጤታማ ቢሆንም ማድረግ ያልቻሉት ዛሬም በትላንቱ የከፋ በትር እየተገረፉ ነው።
አንድ ሰው እስትሮክን በሚከተሉት መከላከያ መንገዶች መከላከል ይችላል፦
1) የደም ግፊት እንዳይከሰት ከተከሰተም በተገቢው መንገድ በመቆጣጠር ለእስትሮክ መንስኤ እንዳይሆን ማድረግ ፤የደም ግፊት አሳሳች ከሚባሉት ህመም አንዱ ነው።ያለ ምንም ምልክት ውስጥ ውስጡን እንደ ብል የውስጥ አካልን እየበላ የሚያዘናጋ መሆኑን ልብ ይበሉ።
2) የስኳር ህመምን መከላከል፤ማከም:- በተለይ አይነት ሁለት ሌላው ምልክት አልባ ሆኖ ለረጅም ግዜ በመቆየቱ ሰዎችን ያሳስታል። የስኳር ህመምን በአግባቡና በግዜ በማከም ለእስትሮክና ሌሎች ህመሞች የመጋለጥ ስጋትን መቀነስ ያስችላል።
3) ውፍረት እና የስብ ክምችትን ማጥፋት:- ቦርጭን ተሸክሞ መጓዝ ጠላትን በቤት ከማኖር በላይ አደገኛ መሆኑን ብዙዎቹ ዘንግተውታል። ቦርጭን የከረባት ማረፊያ ለማድረግ የሚደረግ ሩጫና ዝምታ የሗላ ሗላ አላስፈላጊ ዋጋ እንዲከፍሉ ያስገድድዎታል። በቦርጭና ስብ ክምችት ላይ አብዮት ያድርጉ…
4) ቅጥ ያጣ አመጋገብን ማስተካከል:- ምግብ ገንቢ መሆኑ ቀርቶ እፍራሽ እየሆነ መጥቷል። አመጋገብን ማዘመን ማለት የታሸገ ምግብ አለያም በፍሪጅና ኦቭን የተቃኙ ምግቦችን ከመመግብ ያለፈ ነው። ምግብን ማዘመን አመጣጥኖና ጤናማ አድርጎ መውሰድ ማለት ነው። ጣፋጭ ምግቦችን ፣ከፍተኛ የስብ ክምችት የተሸከሙ ምግቦችን ሲመገቡ ገደብ ይጣሉ። መጠጥም ሌላው ሰውን የሚያፈርስ ነው። ገደብ ይጣሉ!
5) የልብ ህመም እንዳይከሰት ከተከሰተም መታከም። በኛ ሀገር በተለይ ወጣቶችን ለእስትሮክ እየዳረጋቸው ያለው የቶንሲል ኢንፌክሺንን ተከትሎ የሚመጣው የልብ ህመም ነው።
የቶንሲል ህመምን ሳይታክቱ በማከም ብዙ ችግሮችን ማስቀረት ይቻላል።
6) የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ:-አካላዊ እንቅስቃሴ ለሰው ልጅ የሚሰጠው ጥቅም ብዙ ቢሆንም ብዙዎች ሲጠቀሙበት አይታዩም። አንድ ሰዓት ተቀሳቅሶ አንድ ኪሎ በስብ የታጨቀ ምግብ መመገብ ባህል አንንቅስቃሴ አንደለም።
7) ለእስትሮክ የሚያጋልጡ መድሐኒቶችን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ አለመውሰ፤
8) ጭቀትና ውጥረትን ማስቀረት፤
9) ከአንገት በላይ ያሉ ቀላል ኢንፌክሺኖች ሳይራዘሙ ማከም።
10) እራስን ስር ከሚሰዱ ተላላፊ በሸትታዎች መጠበቅ (ቂጥኝ ፣ HIV…)
ከላይ ያሉትን የተከላከለ ፤በአግባቡ ያከመ ከእስትሮክ ብቻ ሳይሆን ከብዙ የውስጥ ደዌ ህመሞች እራሱን ይጠብቃል።
ባለሙያ የማማከርና ምክርን ወደ ተግባር የመቀየር ልማድ ያዳብሩ ፤እስትሮክን ይከላከሉ!!
ዶ/ር መስፍን በኃይሉ ፤ ጥቁር አንበሳ