ካንሰር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱ እና በመከሰት ላይ ካሉ በሽታዎች ለየት የሚያረግ ባህሪ አለው። ለምሳሌ የወባ በሽታ በወባ ትኝኝ አማካኝነት፣ የስኳር ህመምደሞ የኢንሱሊን ማነስ ወይም ሰውነታችን ለኢንሱሊን ምላሽ ባለመስጠት፣ እንዲሁም በቅርቡ የተከሰተው ኮቪድ19 በሽታ በ SARS-CoV-2 በተሰኘ ቫይረስ ይከሰታሉ… ነገር ግን ካንሰር እጅግ የተወሳሰበ ከመሆኑ የተነሳ አንድ ወጥ በሆነ መንስኤ የመከሰት እድሉ ጠባብ ነው።
ይልቁንስ የተለያዩ ምክንያቶች፣ የጤና ክስተቶች፣ እና ጥንቃቄ ጉድለት ከዛም ባስ ካለ ምንም በሚባል ደረጃ ለውጥ በማናመጣበት መልኩ በዘር የመተላለፍ አቅም ያለው በሽታ ነው።
ለካንሰር ሚያጋልጡ እልፍ አዕላፍ የሆኑ ምክንያቶች ከመኖራቸው የተነሳ የካንሰር ህክምና አጥኚ ሳይንቲስቶች “በሂወት መኖር በራሱ ለካንሰር አጋላጭ ነው” እስከማለት ደርሰዋል። ሆኖም ግን በጣም የተለመዱት እና በተደጋጋሚ የካንሰር መነሻ ወይም መባባሻ መንስኤ የሚሆኑትን አሳጥረን እንይ።
- በዘር በቤተሰብ የሚተላለፍ – እንግዲህ ሁሉም የካንሰር አይነት በዘር የመተላለፍ ከፍተኛ የሆነ አዝማሚያ ቢያሳዩም በይበልጥ የጡት፣ የአንጀት እንዲሁም የፕሮስቴት ካንሰር አይነቶች በተደጋጋሚ በቤተሰብ እና በዘር ሲተላለፉ ይታያሉ።
- ትምባሆ/ሲጋራ- ትንባሆ ለኛ እንደሚታየን 1 ቁስ ብቻ ሳይሆን በውስጡ እስከ 60 ገደማ ሊካንሰር የማምጣት አቅም ያላቸውን አደገኛ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ ይዟል። ከነዚህም ውስጥ የሳንባ ካንሰር፣ የጉሮሮ ካንሰር እንዲሁም ራቅ ብሎ የሽንት ፊኛ ካንሰርን የማስከተል አቅም አላቸው።
- ቫይረሶች – በተለይ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር (HPV በሚባል ቫይረስ ምክንያት) እንዲሁም የተወሰኑ በአፍ ውስጥ ሚከሰቱ ካንሰሮች እና የጉበት ካንሰርን (በHepatitis A and B ቫይረስ ምክንያት) ያስከትላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ የታሸጉ ምግቦችን ማዘውተር፣ እና የፀሃይ UV ጨረር (በተለይ የቆዳ) ካንሰርን ማምጣት አቅም አላቸው።
ይህንንም ለመከላከል እና ከተከሰተም ለማዳን በመላው አለም ታላቅ የምርምር እየተደረገ ቢገኝም እስካሁን አመርቂ መከላከያ ካመጡ መንገዶች ውስጥ ጥቂቱን ልጥቀስ እና ላጠቃል
- ከላይ የተጠቀሱ መንስኤዎችን በተቻለ አቅም መቀነስ። በቤተሰብ በካንሰር የተያዘ ሰው ካለ በህክምና ተቋም በመሄድ በዘር ከሚተላለፉ አይነቶች አንዱ መሆኑንን ማረጋገጥ
የHPV እና የጉበት ቫይረስ (Hepatitis virus) ክትባትን መውሰድ፣ እንዲሁም የማህፀን በር ጫፍ የቅድመ ካንሰር ምርመራ/PAP smear ምርመራ ማድረግ
- በተወስነ ግዜ ልዮነት የጡት ምርመራ ማድረግ። በተለይ ሴት እህቶች እራሳቸው ጡታቸውን ሆን ብለው መፈተሽ። በዳበሳ የሚያገኙት እብጠትም ካለ በቶሎ በህክምና ተቋም መታየት።
- ማንኛውንም እብጠት እንደ እንቅርት እና በሌላ ሰውነት ላይ ያሉ እጢዎችን በህክምና ቦታ ሄዶ ማስመርመር በተለይ በአጭር ግዜ በመጠን የመተለቅ፣ ህመም የማምጣት አዝማሚያ ካላቸው ወደ ካንሰር የመለወጥ ሂደት ውስጥ ሊሆኑ ስለሚችሉ በጊዜ አውቆ እርምጃ ለመውሰድ ይበጃል።
ዶ/ር መላኩ አባይ ፤ የስነ ደዌ ህክምና ስፔሻሊስት
ለተጨማሪ መረጃዎች ቴሌግራማችንን ይጎብኙ: t.me/HakimEthio