በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አልፎ አልፎ ያለፕላን የተሰሩ አጥሮች፤ የከተማውን ውበት መቀነሳቸውን የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የህዝብ ህብረት ማስፋፊያና የዜና ማቅረቢያ መስሪያ ቤት አስታወቀ፡፡
በተለይም በዋና ዋናዎቹ ጎዳናዎች ዳርቻ የተሰሩት የአጠናና ቆርቆዎች አለመስተካካል፤ የግንቦቹ አለመጠንከር በአሁኑ ጊዜ ከሚያስቀይሙት ነገሮች የመጀመሪያዎቹ ናቸው ሲል የዜና ማቅረቢያው መስሪያ ቤት አስገነዘበ፡፡
የህንፃዎቹ መሰራት፣ የቪላዎቹ መደርደር ብቻውን አይበቃም የሚለው የዜና ማቅረቢያው መስሪያ ቤት አጥሮቹ በዚሁ አይነት በፕላን እየተጠኑ መሰራት ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ይህን ለማስተካካል በዋና ዋና ጎዳናዎች ዳርቻ ላይ ያሉትን የአጥር አይነቶች ፕላን መስራቱን የዜና ማቅረቢያ መስሪያቤት ያብራራል፡፡
ፕላኑ እንደሚያስረዳው የአዲሱ አጥር ማሰሪያ ቆርቆሮ ተገዝቶ ከሚሰራበት ዋጋ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
የመጀመሪያው ፕላን እንደሚያመለክተው ፤ሃምሳ ሳንቲም ከመሬት በግንብ ይወጣና ከግንቡ በላይ አንድ ሜትር ከአስር ሳንቲ ሜትር የብረት አጥረት መሆኑም ይገልጣል፡፡
ሁለተኛው ፕላን ሃምሳ ሳንቲ ሜትር ከመሬት በላይ ግንብ ሆኖ ፤ከዚያ በላይ ያለው አንድ ሜትር ከሰላሳ ሳንቲ ሜትር በእንጨት ይታጠራል፡፡
ሶስተኛው ፕላን ደግሞ ከመሬት በላይ ሀምሳ ሳንቲሜትር ግንብ ይሆንና አንድ ሜትር ከሃያ ሳንቲሜትር በወንፊት ብረት ማጠር ይቻላል ሲል ዜና ማቅረቢያው መስሪያ ቤት አስረድቷል፡፡
ይህ በማናቸውም ዋና ዋና ጎዳናዎችና አደባባዮች አከባቢ ላይ የሚሰሩት አጥሮች ሲሆን ፤ በአጥሮቹም ስር አበባ ያላቸው ሀረጎች ቢተከሉባቸው የበለጠ ውበት ሊኖራቸው ይችላል፡፡
ማንኛውም ባላቦታ አጥር ለማሰራት ሲፈልግ መጀመሪያ ለዚህ ቦታ ምን አይነት ፕላን እንደሚያስፈልገው ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ስራ ፍቃድ መስጫ ክፍል መጠየቅ ይኖርበታል፡፡
የዛሬዬቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ህዳር 16 ቀን 1965 ዓ.ም ከታታመው የተወሰደ
በሀይማኖት ከበደ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም