የክልሉ መንግሥት የአስተዳደር መዋቅሩንና የፀጥታ ኃይሉን እንደገና አደራጅቶ ወደ ሥራ በመግባቱ ከስምንት ወረዳዎች ውጪ ያሉት ወረዳዎች በክልሉ መዋቅር ውስጥ እየተዳደደሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
አማራ ክልል ያደረገውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ከ10 ሺህ በላይ የታጠቁ ኃይሎች ለሰላም
እጃቸውን እንደሰጡ የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ በተሠራው የሕግ ማስከበር ሥራ የስምንተኛ ክፍል ፈተና በሁሉም የወረዳ ማዕከላት መድረሳቸው ተመላክቷል።
የቢሮው ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የነበረውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በተሠራው የሕግ ማስከበር ሥራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል።
ክልሉ ባደረገው የሰላም ጥሪ መሠረት ለሰላም እጃቸውን የሰጡት ከ10 ሺህ በላይ የታጠቁ ኃይሎች ምክርና ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ትውልድ አካባቢያቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የጽንፈኛ ኃይሎችን እንቅስቃሴ በመግታት ሰላም ለማስፈን በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት መንገሻ (ዶ/ር)፤ በዚህም ጥቆማ በመስጠት፣ መንገድ በማሳየት፣ ትጥቅና ስንቅ በማቀበል ሲተባበሩ የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመምከርና በማወያየት እጃቸውን እንዲሰጡና የሰላም ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት የአስተዳደር መዋቅሩንና የፀጥታ ኃይሉን እንደገና አደራጅቶ ወደ ሥራ በመግባቱ ከስምንት ወረዳዎች ውጪ ያሉት ወረዳዎች በክልሉ መዋቅር ውስጥ እየተዳደደሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በክልሉ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለመቀየር ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው ያለው አመራር ቀበሌ ድረስ በመውረድ ለማህበረሰቡ ሰላም የሚሰፍነው በውይይትና በምክክር እንጂ በጠመንጃ አለመሆኑን በማስረዳት ትክክለኛውን መንገድ እንዲረዱ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በክልሉ በነበረው የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት የግብርና፣ የትምህርትና የጤና ግብዓቶችን በሚፈለገው ደረጃ ማቅረብ እንደማይቻል እና የእንቅስቃሴ ገደብ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ የመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የፀጥታ ኃይል በጋራ በሠሩት የሕግ ማስከበር ሥራ ችግሮቹን መፍታት ተችሏል ብለዋል።
የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በተሠራው የተቀናጀ ሥራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል ያሉት ኃላፊው፤ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለመቀየር የክልሉ የሰላም አስከባሪ የፀጥታ ኃይሎች ከፌዴራል የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሠሩ እና ኅብረተሰቡም የሰላም ጠባቂ እንዲሆን ተናግረዋል።
የክልሉን ሰላም ከማስከበር ጎን ለጎን ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶች የማስጀመር፣ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ የማጠናቀቅና አዳዲስ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን የማስጀመር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ መንገሻ (ዶ/ር) ገለጻ፣ በተሠራው ሥራ ተቋርጠው የነበሩ የጤና፣ የትምህርት የግብርና እና ሌሎች አገልግሎቶችን ማስጀመር ተችሏል። የትምህርት ዘመኑን የስምንተኛና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በሰላማዊ መንገድ ለማስፈተን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ሲሆን፤ የ12ኛ ክፍል ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች ይሰጣል ብለዋል።
የስምንተኛ ክፍል ፈተና በተያዘው ሳምንት በሁሉም የወረዳ ማዕከላት የደረሰ ሲሆን፤ በቀጣይ ሳምንት ወደ የፈተና ማዕከላቱ ተሰራጭቶ በተያዘው የፈተና ጊዜ ገደብ ፈተናው እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
ግብርናን በሚመለከት ከአራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ክልሉ በማስገባት ለአርሶ አደሩ የማሰራጨት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
ሰላም ከማስከበርና የተቋረጡ አገልግሎቶችን ከማስጀመር በተጨማሪም የተለያዩ የልማት ሥራዎች በሁሉም አካባቢዎች እየተሠራ ሲሆን፤ የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ የማጠናቀቅ፣ አስፓልት፣ የኮብልስቶን እና የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችና አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንዲጀመሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
Via አዲስ ዘመን