“ሰርገኞቹ ቤት ውስጥ እያሉ በር ዘግተውባቸው ቦምብ ወረወሩባቸው። ቤት ውስጥ ከነበሩት አንድም በሕይወት የወጣ የለም። እዚያው ተቃጥለው አልቀዋል” ከሚለው ዜና ጋር ተያይዞ የተነሳው የፋኖ ስም ነበር። ዜናው ዘግናኝና አሁን ድረስ ለሰሚው ግራ ነው። ከየአቅጣጫው “ሙሽሮችን በሰራጋቸው ዕለት ከነቤተዘመድ ቤት ዘግቶ ማንደድ የሚቀርብለት ፖለቲካዊ ምክንያትስ ይኖራል?” በሚል ጥያቄ ያቀረቡ በርካታ ቢሆኑም፣ ጉዳዩን አማራና ኦሮሞ ወገን ለይቶ እንዲጫረስ ለማነሳሳት የተጠቀሙበትም አልታጡም።
የአካባቢው አስተዳደሮች፣ ምስክሮችና የኮማንድ ፖስት ሃላፊዎች ድርጊቱን የፈጸሙት የፋኖ ታጣቂዎች እንደሆኑ መናገራቸውን ተከትሎ ” ፋኖ ምዕራብ ሽዋ ዘልቆ ለዚያውም ሙሽሮችን በዚህ መልኩ የሚገድለው ምን ፈልጎ ነው?” በሚል የኦሮሞ ብሄረተኞች በር ዘግተው በተለያዩ አውዶች ሲመክሩ ሰንብተዋል።
ዛሬ ኦፌኮ ባወጣው መግለጫ ለእልቂቱ ሙሉ በሙሉ ፋኖን ተጠያቂ አድርጎ ካወገዘ በሁዋላ ” … ሰፊውና ሰላም ወዳዱ የአማራ ህዝብም ሆነ በስሙ የተደራጁ ፓርቲዎች በግልጽ ሊያወግዙ ይጠበቅባቸዋል” ሲል ጥሪ አቅርቧል።
“እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች በኖኖ የፈጸሙት ተግባር ለዘመናት ተከባብረው የኖሩና የሚኖሩ የኦሮሞና የአማራ ብሄር ተወላጅ ንፁኃን መካከል ጥላቻንና የበቀል ስሜትን በማነሳሳት ማህበረሰባዊ ግጭትን ለመቀስቀስ ያለመ እንደሆነ ይሰማናል” ሲል የውግዘት ጥሪ ያስተላለፈው ኦፌኮ፣ ይህ አደገኛ ተግባር በአፋጣኝ ካልተገታ ሁለቱን ማህበረሰቦችና ሃገሪቱን ወደ ማይወጡት ተጨማሪ አዘቅት ሊያስገባ እንደሚችል በማሳሰብ ነው።
“በመሆኑም” ይላል የኦፌኮ መግለጫ፣ ” በመሆኑም ፓርቲያችን ይህንን አሰቃቂ ተግባር በፅኑ ያወግዛል፡፡ ከየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢዎች በላይ ብዛት ያላቸዉ የአማራ ተወላጆች ኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ተሰባጥረው እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ ፓርቲያችን እነዚህ ዜጎች እንደማንኛውም የክልሉ ነዋሪ ሰላማቸው ተጠብቆ ሃብትና ንብረታቸው ተከብሮ የመኖር መብታቸው መጠበቅ እንዳለበት በፅኑ ያምናል፡፡ ነገር ግን፤ በኖኖ ወረዳ የተፈጸመው አይነት አሰቃቂ ጭፍጨፋ በስሙ በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሲፈፅሙ ሰፊውና ሰላም ወዳዱ የአማራ ህዝብም ሆነ በስሙ ተደራጁ ፓርቲዎች በግልጽ ሊያወግዙ ይጠበቅባቸዋል”
ማውገዝ ብቻ ሳይሆን በመግለጫው ስለግድያው ሚስጢር ጉዳይ ብልጭ ያደረገው ኦፌኮ፣ “ፅንፈኛ የፋኖ ታጣቂዎችም ሆኑ መሸሸጊያዎቻቸዉ አደብ ሊገዙ ይገባል” በሚል ርዕስ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል ከስር ተያይዟል»
የኖኖ ወረዳ ሙሽሮችና ቤተሰቦቻቸዉ ግድያን በማዉገዝ ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ
በኢሮሚያ ክልል መዕራብ ሸዋ ዞን የኖኖ ወረዳ ሙሽሮችና ቤተሰቦቻቸዉ ከውጭ በር ተዘግቶባቸው በቦንብ እንዲቃጠሉና በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲሞቱ መደረጉን ተከትሎ “ፅንፈኛ የፋኖ ታጣቂዎችም ሆኑ መሸሸጊያዎቻቸዉ አደብ ሊገዙ ይገባል” ሲል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ኦፌኮ አስጠነቀቀ፤ በአማራ ክልል የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችና ፓርቲዎች ድርጊቱን ግድያን በማዉገዝ አቋማቸውን ይፋ ሊያደርጉ እንደሚገባም አስታውቋል።ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ
ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ቢፍቱ ጃላላ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቆንዳላ በሚባል ቦታ በሁለቱ ሙሽሮችና ቤተሰቦቻቸዉ ላይ በተተኮሰዉ የኡሩምታ ቶክስና በተወረወረባቸዉ ፈንጂ ሁለቱን ሙሽሮችን ጨምሮ 27 ሰዎች ወዲያዉኑ መገደላቸዉንና 17ቱ ቆስለዉ የሕክምና ዕርዳታ ሳያገኙና እያገኙም እያሉ መሞታቸዉን ከተለያዩ የዜና ማሰራጫዎችና ከወረዳዉ አባሎቻችንና ነዋሪዎች አረጋግጠናል፡፡
ጥቃት የደረሰባቸዉን ወገኖች አስከሬን ለመለየት ባለመቻሉ የተቃጠሉ አካሎቻቸዉ እየተለቀመ በአንድ ጉድጓድ መቀበራቸዉን ስንሰማ ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶናል፡፡ ጥቃቱን ያደረሱትም በሰላሙ ጊዜ የኦሮሞ ሕዝብ ጉያ ዉስጥ ገብተዉ ሲኖሩ የነበሩ ፅንፈኛ የፋኖ ታጣቂዎች መሆናቸዉን ስናረጋግጥ ደግሞ ሐዘናችን ድርብርብ ሆኗል፡፡ እነዚህ ሃይሎች ከተጠቀሰዉ ቀን ሁለት ቀን በፊትም በዚያዉ ወረዳ የጅሩ ገመቹ ቀበሌ ነዋሪ በሆኑ ሁለት ሰዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዉ እንደነበር የቀበሌዉ አስተዳዳሪ ለአንድ የዜና ማሰራጫ ከሰጠዉ ቃል ተረጋግጧል፡፡
እነዚህ ፅንፈኛ ታጣቂዎች በተለያዩ ጊዜ በወለጋ የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ነዋሪዎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶችን ሲያደርሱ እንደነበሩና እንደዚያም እንዲያደርጉ የልብ ልብ የሰጣቸዉ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት እስከ አፍንጫቸዉ የታጠቁት የጦር መሳሪያና ያገኙት ሎጂስቲክስ እገዛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ፅንፈኞቹና መሸሸጊያዎቻቸዉ የሆኑ በሃብት የደረጁ ቡድኖችም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ንጹኃንን በመግደልና በተለያዩ ኃይሎች ላይ በማላከክ በኦሮሚያ የሚኖሩ አማራዎች በማንነታቸው እየታደኑ ነው የሚለውን ትርክት ለማንበር በየሚዲያዎቻቸው የሃሰት ፐሮፓጋንዳ ሲያራግቡ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡
ከዚህም በላይ የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ መሰረታዊ ኃላፊነቱን መወጣት ያልቻለው መንግሰት የአማራ ተወላጆች በኦሮሚያ ውስጥ ተጠቁ በሚል ትርክት እራሳቸውን እንዲጠብቁ በሚል ሰበብ ባለፉት አመታት በመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጭምር መታጠቅ እንዳለባቸው ሲነገር መቆቱም ይታወቃል፡፡ ፅንፈኛ የፋኖ ታጣቂዎቹ እና መሸሸጊያ የሆኗቸዉ ጥቂት ደጋፊዎቻቸው በኖኖ የፈጸሙት አሰቃቂ ተግባር የነዚህ ድምር ውጤት እንደሆነ መገንዘብ ያሻል፡፡ ድርጊቱም የቅርብ ቤተዘመድና ጎረቤት ካልሆኑ በስተቀር ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ወደየመጡበት ከተመለሱ በኋላ የተፈጸመ ስለሆነ አክራሪ ቡድኖች በሊቢያ ባህር ዳርቻ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን ለይተዉ የፈፀሙትን አሰቃቂ ግድያ ጋር ይመሳሰላል፡፡
እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች በኖኖ የፈጸሙት ተግባር ለዘመናት ተከባብረው የኖሩና የሚኖሩ የኦሮሞና የአማራ ብሄር ተወላጅ ንፁኃን መካከል ጥላቻንና የበቀል ስሜትን በማነሳሳት ማህበረሰባዊ ግጭትን ለመቀስቀስ ያለመ እንደሆነ ይሰማናል፡፡ ይህ አደገኛ ተግባር በአፋጣኝ ካልተገታ ሁለቱን ማህበረሰቦችና ሃገሪቱን ወደማንወጣው ተጨማሪ አዘቅት የሚከት ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም፤ ፓርቲያችን ይህንን አሰቃቂ ተግባር በፅኑ ያወግዛል፡፡ ከየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢዎች በላይ ብዛት ያላቸዉ የአማራ ተወላጆች ኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ተሰባጥረው እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ ፓርቲያችን እነዚህ ዜጎች እንደማንኛውም የክልሉ ነዋሪ ሰላማቸው ተጠብቆ ሃብትና ንብረታቸው ተከብሮ የመኖር መብታቸው መጠበቅ እንዳለበት በፅኑ ያምናል፡፡ ነገር ግን፤ በኖኖ ወረዳ የተፈጸመው አይነት አሰቃቂ ጭፍጨፋ በስሙ በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሲፈፅሙ ሰፊውና ሰላም ወዳዱ የአማራ ህዝብም ሆነ በስሙ ተደራጁ ፓርቲዎች በግልጽ ሊያወግዙ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የፓርቲያችን ጽ/ቤት እንደ አባሎቻችን ሐሳብና ደጋፊዎቻችን ጥያቄ ብዙ የምንላቸዉ ነገሮች ቢኖሩም፤ ከሚሰማን ኃላፊነት በመነሳት ተቆጥበን፤ ለሟቾች ጥልቅ ሐዘናችንን በድጋሚ እየገለፅን፤ እነዚህ ፅንፈኛ የፋኖ ታጣቂዎችና መሸሸጊያዎቻቸዉ ከመሳሰሉ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች አደብ ይገዙ ዘንድ፤ መንግስት ሕዝብን የመጠበቅ ግዴታዉን እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ በተጨማሪም ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሕዝብ ወዳጆችና የመብት ተሟጋቾች ይሄን እኩይና አፍራሽ ተግባር በፅኑ እንዲያወግዙ ጥሪ እናደርጋለን፡፡
ሕዝባችንም መንግሰት ደህንነቱን እያስጠበቀለት ስላልሆነ ተደራጅቶ የራሱን ሰላም እንዲጠብቅ፣ ከጎኑ ለሚኖሩ ንጹሃን የአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ጥበቃ ሊያደርግ እንደሚገባም ጨምረን እናሳስባለን፡፡ በኦሮሚያ ክልል የአማራ ተወላጆችም በስሙ ተደራጅተዉ ንጹኃን ላይ ጥቃት የሚያደርሱ የታጠቁ ፅንፈኛ ኃይሎች መሸሸጊያ እንዳይሆን አጥብቀን እንመክራለን፡፡
በኖኖ ስለተፈጸመው ጭፍጨፋ በነጻና ገለልተኛ አለማቀፍ ተቋማት ምርመራ እንዲደረግ፤ ጭፍጨፋውንም የፈፀሙ ኃይሎች ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፡፡
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጽ/ቤት

