በአማራ ክልል ሰፋፊ ሊታረስ የሚችል መሬት ካለባቸው አካባቢዎች ምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ይገኙበታል።
ከደጋማው አካባቢ በመነሳት ወደ ሱዳን የሚፈስሱ እንደ አይማ፣ ሽንፋ፣ ጓንግ እና አንገረብ የመሳሰሉ ትላልቅ ወንዞች የሚያልፉባቸው ዞኖች ናቸው።
ታዲያ ዞኖቹ ካላቸው ሰፊ ሊታረስ የሚችል መሬት እና ከፍተኛ የውኃ ሃብት አኳያ የመኸርን ወቅት ጠብቆ ከማልማት የዘለለ ልማት ሲለማ አይታይም። እነዚህን ወንዞች በዘመናዊ መንገድ በመገደብ ለማልማት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በፌዴራል እና በክልሉ መንግሥት ጥናት እየተካሄደ ይገኛል። ከጥናቶቹ ውስጥ ደግሞ የአንገረብ የመስኖ ፕሮጀክት አንዱ ነው።
ፕሮጀክቱ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ በዋናነት የሚሸፍን ሲኾን ምዕራብ አርማጭኾ፣ ማዕከላዊ አርማጭኾ እና የተወሰኑ መተማ ወረዳ ቀበሌዎችን ጭምር የማልማት አቅም እንዳለው የጠገዴ ወረዳ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጥላሁን ነጋ ነግረውናል።
ከታኀሣሥ/2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ/2015 ዓ.ም ድረስ 25 በመቶ የጥናት እና ዲዛይን ሥራውን ማከናወን ተችሎ እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ በ2016 ዓም በጀት ዓመት መጀመሪያ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት መቆሙን ገልጸዋል።
በአካባቢው የተከሰተው የጸጥታ ችግር ከፕሮጀክቱ ባለፈ ትላልቅ የልማት ሥራዎች ላይ እንዲቆም ማድረጉን ነው ያነሱት።
የአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየልኝ መሳፍንት በፌዴራሉ መንግሥት እየተጠኑ ከሚገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ አንገረብ መስኖ ልማት ፕሮጀክት መኾኑን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ 50 ሺህ ሄክታር መሬት ያለማል ተብሎ እስከ 30 በመቶ ጥናት ተደርጎ ነበር ብለዋል። ይሁን እንጂ ግድብ ሲገደብ በርካታ ነባር ገዳማትን የሚነካ ኾኖ ተገኝቷል። ለዚህ ደግሞ ካሳ ይከፈል ቢባል እንኳ ከፍተኛ ወጭ የሚያስወጣ በመኾኑ ግድቡ የሚያርፍበት ቦታ እንዲቀየር መደረጉን አሳውቀዋል።
አሁን ላይም 21 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ማልማት በሚያስችል ቦታ ላይ ጥናት እየተካሄደ ነው፤ አጠቃላይ ጥናቱም በቀጣይ ይፋ ይኾናል ብለዋል።
ጥናት እየተደረገባቸው ከሚገኙት ሌሎች ፕሮጀክቶች ውስጥ በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙት የአይማ እና ሽንፋ የመስኖ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል። አይማ መስኖ ፕሮጀክት 25 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው ሲኾን 15 በመቶ ማጥናት ተችሏል።
ሌላው የሽንፋ መስኖ ፕሮጀክት ሲኾን እስከ 85 ሺህ ሄክታር የማልማት አቅም አለው። በ2015 ዓ.ም 50 በመቶ ጥናቱ ተጠናቅቋል። በ2016 ዓ.ም ሥራ ተጀምሮ እንደነበር ገልጸዋል። የፕሮጀክቶቹ ጥናት በዚህ ወቅት በጸጥታ ችግር ምክንያት መቆሙን ነው ያነሱት።
ፕሮጀክቶቹ የሚከናወኑባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ አኩሪ አተር፣ ሰሊጥ እና ጥጥ የመሳሰሉ ገበያ ተኮር ምርቶች የሚመረቱበት በመኾኑ በአካባቢው አግሮ ኢንዱስትሪ ዞን ለመመሥረት አቅም እንዳለው ምክትል ኀላፊው ገልጸዋል። ለቆላ ስንዴ ልማትም ከፍተኛ አቅም እንዳለው ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ በሽንፋ የመስኖ ፕሮጀክት አካባቢ ትልቅ ከተማ ለመመሥረት መታቀዱን ገልጸዋል።
ግድቦቹ ከሚያለሙት የሰብል ልማት ባለፈ ለዓሣ፣ ለአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፤ ለመዝናኛነትነም ያገለግላል ነው ያሉት።
Via Amhara massemedia