“ለምን እኛ ይህን ማድረግ ያቅተናል?”
“ምን ጎደለን?”
“እነሱ ያላቸው እኛ የሌለን ነገር ምንድን ነው? እኛ ሞልቶን እነሱ ግን ሳይኖራቸው ግዙፍ ህልሞችን ማሳካት እንዴት ቻሉበት?”
“የነሱ ህዝቦች ከባድ እና አስቸጋሪ በሆኑ ግዜዎች ሁሉ እንዴት ሀገራቸውን መቀየር ቻሉ?”
እነዚህ ሁሌ በሀሳቤ የሚንከራተቱ ጥያቄዎች ናቸው። ለስራ በምናደርገው ጉብኝት ወቅት ከማያቸው እና ከምሰማቸው የሚመነጩ ጥያቄዎች። በግሌ ካደረኳቸው የተለያዩ ሀገራት ጉብኝቶች እና ገጠመኞች የሚነሳ የሁልጊዜ ቁጭት።
ሰሞኑንም ይህ ቁጭት በውስጤ ተንሰራፍቷል። ገዝፏል። በኮሪያ ህዝብ ስርዓት እና የስራ ቅልጥፍና ተደምሜ ሳላበቃ ወደ ሲንጋፖር አቀናን።
ሲንጋፖር እጅግ በጣም ብዙ የሚነገርላት ሀገር ናት። ብዙ ሀገሮች እንደምሳሌ ያነሷታል። አኔም ላያት እጓጓላት ነበር። እዛ ስደርስ ከጠበኳት አንሳ ብትገኝስ የሚል ፍራቻ ነበረኝ። ምዕራባውያን “managing expectations” ይሉታል።
ሲንጋፖርን ግን በነበረን አጭር ቆይታ ‘ሆኖ የመገኘት’ ማሳያ ነው የሆንችብኝ። የከተማዋ ንጽህና እና አረንጏዴነቷ፤ የህዝቡ ትህትና እና ቅንነት፤ የተላበሱት የሀገር ኩራት፤ ለህግ ተገዥነታቸው እና በሰላም ተዋህዶ የመኖር ፍላጎት እና ሌላ ምርጫ እንደሌላቸው የማመን ፅኑነት። አስገራሚ ነው።

ሲንጋፖር የተለያዩ ዘሮች ውቅር እንደመሆኗ multiculturalismን እንደ ዕድል እንጂ እንደ ሸክም የቆጠረች ሀገር አይደለችም። ማንኛውም multi-ethnicity society እንደሆነ ሀገር ችግሮችን ሳታልፍ ያደገች ሀገርም አይደለችም።
በታሪካቸውም የዘር ፖለቲካ ሳይነካቸው ያለፉም አይደሉም። ነገር ግን በአብሮነት ለመኖር የወሰኑ ህዝቦች ናቸው። ጠንክሮ ከመስራት በቀርም ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ያመኑ እና የወሰኑ መሆናቸውን ከመሰረተ ልማታቻው፤ ከሰርቪስ አሰጣጣቸው፤ አንድን ቦታ እሴት በሚጨምር መልኩ ለህዝብ ማቅረብ ከመቻላቸው እና ለመሪ አቅጣጫ እና ራዕይ ክብር ያላቸው መሆናቸው በቅንጭቡ ማየት ይቻላል። ይህንን ሁሉ ያደረጉት እንግዲህ በ59 አጭር የነጻነት ዓመት ታሪካቸው ውስጥ ነው።
አንድን ታሪክ ጠገብ፤ ባለ ብዙ ባህላዊ እና ተፈጥሮአዊ እሴት እና ባለ ብዙ የሰው ሀይል ያላት ሀገር እንዴት በራሷ መልክ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ዘገየን?
ለምንድን ነው ምንጓተተው እና ምንጎተተው? ከቶ ምንም የሌላቸው ከባዶ ተነስተው ተራራ ሲወጡ ባለ ብዙ የሆንነው ኖሮን እንዴት እንደሌለን መኖርን መረጥን? መጨካከንን እና እርስ በራስ መጠላለፍን እንዴት ተላመድን?
አቃለሁ ይህን እያነበበ እንዴት ባለስድብ መልስ ለመስጠት እና ለማንቋሽሽ እንደሚችል እያሰበ የሚቻኮል ብዙ ነው። ይህን ጥያቄ ስለጠየኩ በacademic ቋንቋ እና ቃላት አቃቂር የሚያወጣለትም ብዙ ነው። ስድብ ከችኩል ምላስ ጫፍ ይነሳል…የስራ አድራሻው ግን ከልብ ነው።
በሁለትዮሽ ስብስባ ላይ ያሁኑ የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ምን አሉ መሰላችሁ? “የሀገራችን መሪ የነበሩትን Lee Kuan Yewን አንዳንዶች በግዜው ‘አትክልተኛ’ ብለው ያንቋሽሹት ነበር።” ይህም አረንጏዴ ክባቤን ለመፍጠር ካላቸው ጉጉት እና ክትትል ነበር። የዛሬ 40 ዓመት ከሴኔጋል አስመጥተው የተከሉት ችግኝ ዛሬ ከአየር ማረፍያ ተወጥቶ ወደ ከተማ ሲነዳ በመንገዶች ግራ እና ቀኝ ፤ እንዲሁም ባካፋዩ በመደዳ ገዝፈው፤ አምረው፤ ጥላ እየሰጡ፤ ከመኪና የሚወጣ የካርበን ብክለትን sequester እያደረጉ ጸንተው ቆመዋል።
ዛሬ ይህቺ ሀገር መሬት አንሷት ባህር ላይ መሬት እየሰራች፤ እየሰፋች ያለች አረንጏዴ ሀገር ናት። በ2019 ብቻ ከሀገሪቷ ህዝብ ቁጥር ሶስት እጥፍ የሚሆኑ ጉብኚዎች ሄደው ጎብኝተዋታል። ካለቻቸው ትንሿን አብቃቅተው፤ አሳድገው፤ የሌላቸውን ፈጥረው፤ እሴት ጨምረው የአለምን ህዝብ ያስደምማሉ።
እኛስ? በርካታ ምድረ ገነቶች በጏሯችን ናቸው እኮ። በርካታ እድሎች በጃችን ናቸው እኮ! ብዙ ተቆልፈው የቆዩ በሮች ተከፍተውልናል። ለትውልድ ስንል እንበርታ፤ እናበረታታ። ተዉ እንስራ፤ እናሰራ።
ጎበዝ ከቀኑ አይቀር በሀገር ነው እንጂ ከጎንህ ቆሞ ለሀገር በሚተጋ አይደለም። ቅንነት እንላበስ። ይህ ካቃተን ግን፤ ለቅን ልቦች መንገዱን እንልቀቅ።
https://www.facebook.com/share/p/HRHpKs8SBgi72WuY/
- ቢልለኔ ስዩም (ግንቦት 29 ፤ 2016)