ወትሮ ከጥፋቱ የማይማረውና ከግጭት አዙሪት ውጭ ህይወት የሌለው አሸባሪው ህወሃት ከራያ አካባቢወች ለቆ እንዲወጣ የራያ ህዝብ በተለያዩ ከተሞች ሰልፍ እያካሄደና ጥያቄውን ግልጽ እያደረገ ይገኛል።
ራያን በወረራ የያዘው ህወሃት ቀጠናውን በማስፋት በጠለምት በኩል የሞከረው የወረራ ትንኮሳ በጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በአካባቢው ሚሊሻና በህዝቡ አንድነት ግንባሩን ተብሎ ተመልሷል።
ሀገርና ህዝብ በህወሀት የደረሰበትን መጠነ ሰፊ ጉዳት በመቻል ለጋራ ሰላም ሲባል እድል ሰጥቶ ይገኛል። ሆኖም ህወሀት የሰላም ቋንቋ ስለማይገባው በአመራሮቹ አማካኝነት አሳሳች ፕሮፓጋንዳ እያሰራጨ፣ ነገር ያልተገለጠላቸውን ሀይሎች እያምታታ፣ የእርስበርስ ግጭት እየፈጠረ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሽብርን እየጠመቀና ሰላም ከሀገሪቱ ጨርሶ እንዲጠፋ አሁንም በሰፊው አበክሮ እየሰራ ይገኛል።
የራያ፣ የኦፍላ፣ የወልቃይት ጠገዴና የጠለምት ህዝብ ማንነቴ ይከበርልኝ ሲል ጥያቄውን በአደባባይ ሲገልጽ ቆይቷል እየገለጸም ይገኛል።
ይህ የህዝብ ሰልፍ በራሱ ነባሪ (default) ህዝበ ውሳኔ መሆኑን መንግስትና ህዝብ ሊያውቅለት ይገባል። ይህንንም የ”መገፋት ይብቃኝ፣ ማንነቴና ምርጫየ ይከበርልኝ” የህዝብ ድምጽ በቅጡ ሊደመጥና ህጋዊ እውቅና ሊሰጠው ይገባል!
በርግጥም ይህንን ሰፊ ህዝባዊ ጥያቄ የትግራይ ህዝብ ሊያደምጥና ሊደግፍም ይገባዋል! የትግራይ ህዝብ በህወሃት የእብሪት ወረራ ምክንያት ልጆቹ ለዳግም እልቂት እንዳይማገዱ አስቦ የመወሰኛው ጊዜው ነገ ሳይሆን ዛሬ መሆኑን ማጤንና መወሰን ይኖርበታል። ስለሆነም ለትግራይ እህት ወንድሞች እንደወትሮው ሁሉ ዛሬም ማስተላለፍ የምንፈልገው መልክት ህወሃት የትግራይን ህዝብ ከዚህ በላይ ከኢትዮጵያ ህዝብ እንዳያቆራርጠው፣ ከዚህ በላይ ደም እንዳያቃባው፣ ከዚህ በላይ እንዳይጎዳው እና የህወሃትን የታደሰ የወረራ ፍላጎትና የጥፋት እርምጃ አበክሮ እንዲቃወም ነው።
ሰኔ 07/2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ