ተጠርጣሪዋ የስርቆት ወንጀሉን የፈፀመችው ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ቢጫ ፎቅ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡
በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ከቤተል አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በወቅቱ በግምት ከጠዋቱ 12:30 ሰዓት ገደማ የግል ተበዳይ በስፍራው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B32912 አ.አ የሆነ ተሽከርካሪያቸውን መኖሪያ ቤታቸው በር ላይ ሞተር አስነስተው እያሞቁ የነበሩ ሲሆን ወደ ስራ ለመሄድ ጃኬት ሊደርቡ ወደ ቤት በገቡበት ቅስፈት ተሽከርካሪያቸውን ከቆመበት ቦታ እንደሌለ አረጋግጠው ለፖሊስ ሪፖርት ያደርጋሉ። የኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አቤቱታው ከደረሰው ሰዓት ጀምሮ ተሰውሮ የነበረውን ተሽከርካሪ ለማግኘት ግማሽ ቀን በፈጀ ጠንካራ ክትትልና መረጃ የማሰባሰብ ሥራ ተጠርጣሪዋን ከነተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር አውሏታል።
ግለሰቧ የግል ተበዳይ ወደቤት በገቡበት ቅስፈት ተሽከርካሪውን አስነስታ ብትሰወርም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ልዩ ቦታው ሰሚት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በግምት ከቀኑ 9 ሰዓት ገደማ ከነተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውላለች ። የተለያዩ ዘዴዎችንን በመጠቀም የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ የሁሉም ስው ኃላፊነት መሆኑን ያሳሰበው ፖሊስ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ መኪናቸውን አቁመውና የተሽከርካሪውን ቁልፍ በውስጡ ትተው በሚሄዱበት አጋጣሚ ለተመሳሳይ የስርቆት ወንጀል ሊዳረጉ ስለሚችሉ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል ።
ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓም (ኢ ፕ ድ)