ብዙ ጊዜ በስፖርቱ አለም በውጭም ሆነ በሀገራችን “ምላሳቸውን ውጠው” ሲባል እንሰማለን ይህ ችግር አልፎ አልፎ የሚከሰት ቢሆንም አደገኛ እና በቀላሉ ህይወትን የሚያሳጣ ክስተት ነው።
ስለዚህ ሁላችንም የምላስ መታጠፍ (Tongue fallback) ችግር የደረሰበት ሰው መቼ እና እንዴት እንደሚገጥመን ስለማናውቅ እና ትንሽ የማውቀውን ነገር ለእናንተ ላካፍላችሁ ወደድኩኝ
እንደምታውቁ ምላሳችን ከታችኛው የአፋችን ክፍል ጋር በጠንካራ ጡንቻዎች የተያየዘ የሰውነት ክፍል ነው በምንም ተዓምር ወደ ውስጥ ልንውጠው አንችልም። ይህን ያልኩበት ምክንያት TV ላይ ወይንም ሌሎች ሚድያዎች ላይ ሰምታችሁ ከሆነ “The Player Swallows his Tongue” (ተጨዋቹ ምላሱን ዋጠ) የሚል የተለመደ ንግግር ስላለ ነው!
ምንም እንኳን በጠንካራ ጡንቻዎች የተያየዘ ቢሆንም በተለያዩ ምክያቶች ለምሳሌ እንደ እግር ኳስ ፣ ራግቢ የመሳሰሉ ከፍተኛ ትግል በበዛባቸው እንቅስቃሴዎች ሰዓት የታችኛው የአፍ ክፍል ሲመታ ምላሳችን ወደኋላ ሊታጠፍ ይችላል።
ሌላው ደግሞ በመድሀኒት ወይንም በሌሎች ምክንያቶች እራሳችንን የመሳት አደጋ ሲገጥመን ምላሳችንን የሚያንቀሳቅሱቱ ጡንቻዎች ስለሚደክሙ ወደ ኋላ ሊታጠፍ እና የተለመደውን የአየር ዝውውር በማስተጓጎል ምንም አየር ወደ ሳንባችን እንዳይገባ ያደርጋል ይህ ደግሞ በደቂቃዎች ውስጥ ህይወትን ያሳጣል።
እንደዚህ ያለ አደጋ በሌሎች ሰዎች ላይ ተከስቶ ቢገጥመን ምን ማድረግ አለብን?
አሁን በተለያዩ ሚድያዎች እንደምንሰማው እና እንደምናየው ምላስን በእጃችን ለማውጣት መሞከር ብዙም አይመከርም ምክንያቱም እርዳታ በሚሰጠው ሰው ጣቶች ላይ ጉዳት መድረስ ከዚህ አለፍ ሲል ሙከራችን ላይሳካ ይቀር እና አደጋ የደረሰበት ሰው እስከወዳኛው ሊያሸልብ ይችላል።
የሰውየውን አፍ ለመክፈት እና ምላሱን ወደነበረበት ለመመለስ በምንታገልበት ሰዓት ያለን ሰዓት አጭር ስለሆነ ከ2-3 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ የአየር ቧንቧውን መክፈት ካልቻልን የሰውየው ህይወት ሊያልፍ ይችላል!
በጣም ቀላሉ ፣የሚመከረው እና ውጤታማ የሆነው ዘዴ ይህን እርዳታ በሚሰጠው ሰው ምንም ጉዳት የማያደርሰው ከታች በምስሉ ላይ ለማሳየት የሞከርኩት ዘዴ ነው።
Head tilt, Chin lift and Jaw thrust ዘዴዎች ይባላሉ ( እነዚህን ቃላት ወደ አማርኛ አቻ ትርጉም ለመቀየር ስለተቸገርኩኝ ከታች ያለውን ምስሉን አይታችሁ ለመረዳት ሞክሩ)
የምላስ መታጠፍ አደጋ የደረሰበት ሰው በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ከገጠማች መጀመሪያ ማድረግ ያለባችሁ
👉በፍጥነት አደጋ የደረሰበትን ሰው በቶሎ በጀርባው ማስተኛት በመቀጠል
👉Head tilt, Chin lift and Jaw thurst በማድረግ የተዘጋውን ወይንም እክል የገጠመውን የአየር ቧንቧ ወደ ነበረበት በቀላሉ መመለስ ከሞት እንታደጋለን!
እርዳታ የሚሰጠው ሰው አደጋ በደረሰበት ሰው በጭንቅላቱ አቅጣጫ በኩል ቢሆን እነዚህን ዘዴዎች ለመጠቀም ቀላል ያደርግለታል።
ዋሲሁን አራጌ አንስቴቲስት እና በአድስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አንስቴዥያ ት/ክፍል ማስተርስ ተማሪ
Via – HakimEthio