የአፍሪካ አመራር ልህቀት ኘሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ ከወልድያ ከተማ እና ሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ጋር በነበራቸው የምክክር ጊዜ ወልድያ ከተማ ሲመጡ የተሰማቸውን ስሜት እና በወቅታዊ የራያ ጉዳይ ላይ ንግግር አድርገዋል።
ወልድያ ከተማን ከልጅነታቸው ጀምሮ እንደሚያውቋት እና በልጅነታቸው የከተሞች ሁሉ አውራ አድርገው ይስሏት የነበረች የልጅነት ትዝታቸውን የምትጋራ ከተማ መኾኗን የአፍሪካ አመራር ልህቀት ኘሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ አስታውሰዋል።
ዛሬ የሰሜን ወሎ ዞን መቀመጫ በኾነችው ወልድያ ከተማ ንግግር የማድረግ እድል ሳገኝ የተሰማኝ ደስታ ከሁለም የላቀ ጥልቅ ስሜት ነው ብለዋል። ምክንያቱም የቅርብ ቤተሰቦች ጋር በመገናኘቴ ወደር የሌለው ደስታ ተሰምቶኛል ነው ያሉት።
አዲስ አበባ ልኑር እንጂ ሃሳቤ እዚህ አካባቢ ነው ምክንያቱም ሕዝቤ ለዓመታት እያደርገው ያለው ትግል ይታወሰኛል ነው ያሉት። የራያ ሕዝብ ለማንነቱ የሚያደርገው ትግል ሃቅ ላይ የተመሰረተ መኾኑን አቶ ዛዲግ አስረድተዋል።
በራያ ሕዝብ ትግል ከጎኑ ለቆሙ የፌደራል፣ የክልል እና የዞን መሪዎች ምሥጋና አቅርበዋል። የራያን ሕዝብ እውነተኛ ትግል ባልተገባ መንገድ ለመሳል የምትሞክሩ የህወሓት ካድሬዎች መጨረሻችሁ አያምርም ነው ያሉት።
የራያ ሕዝብ በክፉም በደጉም ወሎየነቱን ከልቡ አርቆ አያውቅም። ወሎየነቱ ሲደሰት ግርማ ሞገሱ እና ካባው፣ ሲያዝን ደግሞ መተከዣው እና ማኩረፊያው ኾኖ ለዘመናት ኖሯል ብለዋል።
ራያ ወሎ ነው፤ የራያ እጣፋንታው እና አምሳያው አማራ ነው ብለዋል የአፍሪካ አመራር ልህቀት ኘሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ። እኔ በግሌ ለዚህ አላማ መሳካት ሲባል እስከመጨረሻው ዝግጁ መኾኔን ላሳውቅ እወዳለሁ ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ ለራያ ሕዝብ የመጥፎ ጊዜ መከታ፣ አለኝታ እና ማገር ኾኖ ቆይቷል። የአማራ ሕዝብ ለራያ ሕዝብ እያደረገው ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ህወሓት የራያ ሕዝብን በጉልበት ያለውዴታው እና ፍለጎቱ በጉልበት መግዛት ከቆመ ከለውጡ ጀምሮ 6 ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህንን ወደ ኋላ መመለስ እንደማይቻል ተናግረው ህወሓት ይህን በመገንዘብ ካለፈው የተሳሳተ መንገድ ትምህርት በመውስድ ወደ ቀና መንገድ እንዲመለሱ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ካሳሁን ኃይለሚካኤል አሚኮ