በብዙ ችግር ውስጥ ላለፈች፣ እያለፈች ላለች፣ ብዙ ፍላጎቶች እና ምኞቶች ላሉባት ሀገር ተስፋ የሚኾን፣ የአንድነት መሠረቷን የሚያጸና፣ እሴቶቿን የሚጠብቅ፣ ያቆሟትን ጠንካራ ምሰሶዎች የሚያበረታ ዘላቂ መሠረት ያስፈልጋታል፡፡
ኢትዮጵያ የልጆቿን መግባባት እና መስማማትም አብዝታ ትሻለች፡፡ የልጆቿ መግባባት እና መስማማት በታሪኳ ውስጥ ጉልህ አሻራዎችን እንድታስቀምጥ አድርጓታልና፡፡
ኢትዮጵያ የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች ሲበዙባት የኖረች፤ እየበዙባት ያለች ሀገር ናት።
ለምን ቢሉ ትኩረት የሚበዛባት እና ብዙ ፍላጎቶች ያሉባት ናትና፡፡ በታሪኳ የውጭ ፈተናዎችን በጽናት፣ በጀግንነት እና በአንድነት ያለፈችው ኢትዮጵያ የውስጥ ፈተናዎች ሲፈትኗት ኖረዋል፡፡
በውስጥ የተነሱባት የሃሳብ ልዩነቶች እያደጉ ሄደው እርስ በእርስ መገዳደል አምጥተው በርካታ ልጆቿን ቀጥፈውባታል፡፡
አሁን ግን የውስጥ ፈተናዎችን እና ችግሮቿን የምትፈታበት ዘዴ ዘይዳለች፡፡ ሁሉም የሚያሸንፉበትን፣ የሁሉም ሃሳብ የሚሰማበትን፣ የሁሉም ሃሳብ ተመክሮበት፣ ተዘክሮበት ለሀገር እንዲጠቅም የሚደረግበትን፣ በሀገር ሰላም እና መረጋጋት የሚመጣበትን መደላድል እየፈጠረች ነው፡፡
ኢትዮጵያ መክራ እና ዘክራ ችግሮቿን ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁማ እየሠራች ነው፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረችም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን ታላቅ ተስፋ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር) ተስፋ የሕይዎት መሠረት፣ የሕይዎት መንኮራኩር ነው፤ ያለ ተስፋ ሕይዎት ትርጉም የለውም፤ ምክክር ሃሳቡ በራሱ ተስፋ የሚሰጥ ነው ይላሉ፡፡
ምክክር ሁሉም አሸናፊ ኾኖ የሚወጣበት መድረክ ነው፣ በምክክር ሁሉም አሸናፊ ኾኖ ሀገር የምትካስበት አውድ ነው፡፡
በምክክሩ ትልቅ ተስፋ የሚደረግበት ሀገር እና ሕዝብ የሚካስበት፣ ሁሉም የሚያሸንፉበት፣ የተደበቀው ዕውነት የሚወጣበት፣ ዘላቂ ሰላም የሚገነባበት፣ የውስጥ ቁስል ኾነው የቆዩት ጉዳዮች ያለ አንዳች መተፋፈር እና መጨናነቅ በግልጽ ተነጋግሮ በመጨረሻ ዕውነት የሚወጣበት በመኾኑ ነው የሚሉት፡፡
የምክክር ፍልስፍና መሠረቱ፣ ፍትሕ፣ አካታችነት፣ ግልጽነት እና ከሁሉም በላይ ሁሉም አሸናፊ ኾነው በሚወጡበት ላይ የተመሠረተ ነው ይላሉ፡፡
ትናንት በተሠራው ዛሬ ላይ መጋጨት አይገባም የሚሉት ኮሚሽነሩ አንድን ሕዝብ የጥፋት ተጠያቂ ማድረግ እርግማን ነው፣ በየትኛውም ሀገር ፍትሕ ሊጓደል ይችላል፤ ፍትሕ ሲጓደል ደግሞ ተጠያቂ መኾን ያለበት ግለሰብ ወይም ቡድን ነው፣ ሕዝብ በጠቅላላ ወንጀለኛ ሊኾን አይችልም ነው የሚሉት፡፡
ምክክሩ እንዲህ አይነት ትርክቶች በሚቀርቡት ጉዳዮች ላይ በግልጽ እንዲመከር የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
ቁስል ኾነው በተደጋጋሚ የሚነሱ ጉዳዮችን ስናወጣቸው እና ስንነጋገርባቸው ነው መፍትሔ የሚመጣው ነው የሚሉት፡፡
በነጭ እና በጥቁር መካከል የነበረው የደቡብ አፍሪካው ልዩነት፣ ለዘር ጭፍጨፋ የዳረገው የሩዋንዳው የዘር ግጭት ተቀርፎ ሰላም የሰፈነው በምክክር ነው፤ በአውሮፓውያን ዘንድም የነበረው መለያየት የተስተካከለው በምክክር ነው፤ እኛም መስማማት እና በስክነት መምከር ከቻልንም ማናቸውንም ችግር መፍታት እንችላለን ይላሉ፡፡
ለራሳችን ጊዜ እንስጥ፤ ለሰላም ጊዜ እንስጠው የሚሉት ዶክተር ዮናስ አዳየ “ጦርነትን የመሠራት ችሎታው ካለን፤ ሰላምንም የመሥራት ችሎታው አለን” ብለዋል፡፡
120 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሁሉም በአካል መሳተፍ አይችልም፤ ነገር ግን የ120 ሚሊዮን ሕዝብ ሃሳብ ሊወከል ይችላል፤ በጣም ትልቁ ነገርም የሃሳብ ውክልና ነው፤ በሕመም ውስጥ ትንሽ የደም ጠብታ ተወስዳ ለመላ ሰውነት ፈውስን የሚሰጥ መድኃኒት እንዲሰጥ ታደርጋለች፣ ምክንያቱም ያቺ የደም ጠብታ የሰውነት ውክልና ናትና፤ የሚወሰደው የሃሳብ ናሙናም ለሁሉም መድኃኒት ይኾናል ነው የሚሉት፡፡
በየትኛውም የትግል መስክ የሚገኙ ወገኖች ለነገ ሕልሞቻችን መሳካት ወደ ምክክር መምጣት አለባቸውም ብለዋል፡፡
የምክክር ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ከፍታ፣ የኢትዮጵያን ተስፋ ከሚፈልጉ ወገኖች ጋር ሁሉ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ትልቁ ጥረት የሁሉም ወገን ሃሳብ እንዲወከል ነው ይላሉ፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲኾን ማስተማር ይገባል፤ ሰላምም ጦርነትም የሚጀመረው ከአስተሳሰብ ነው የሚሉት ኮሚሽነሩ አስተሳሰብ ወደ ቃላት ይቀየራል፤ ቃላቱ ደግሞ ወደ ግጭት ይቀየራሉ፤ ይህ እንዳይኾን መልካም ሃሳቦች እንዲሰፉ ሚዲያዎች መሥራት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ያለ ምክክር ቀጣይነት ያለው እድገት፣ ሰላም ሊመጣ እንደማይችልም አመላክተዋል፡፡
ግጭት የሚያስወግዱ፣ ሰላምን የሚገነቡ ቃላትን መጠቀም ይገባል ነው ያሉት፡፡
አንደኛውን ከሌላኛው የሚያርቅ ሳይኾን የሚያቀራርብ ቃላትን መጠቀም አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት፣ በሕዝብ እና መንግሥት፣ በሕዝብ እና በሕዝብ መካከል መተማመን እንዲኖር ለማድረግ እና ምክክር ባሕል እንዲኾን ለማድረግ ዓላማ ይዞ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ሁላችንም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሚናችንን መወጣት አለብን የሚሉት ኮሚሽነሩ በዓድዋ ላይ ታሪክ እንደሠራን ሁሉ በምክክሩም የሰላም ዓድዋ መደገም አለበት ነው የሚሉት፡፡
መግባባት ሲኖር ዕምነት ይኖራል፤ መተማመን ደግሞ የሚያስተሳስር እና የሚያጣብቅ ነው፣ መተማመን ለማኅበራዊ ውል መሠረት ነው፣ ውል የሚጠብቀው ደግሞ መተማመን ሲኖር ነው፤ እርስ በእርስ መገናኘት፣ መተያየት እና መተማመን እንዲኖር ያደርጋል ይላሉ፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ በስኬታመነት እንዲቀጥል ማድረግ ልጆች ተስፋ እንዲኖራቸው፣ በፈለጉት ቦታ እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል ነው የሚሉት፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ፍትሕ፣ አንድነት፣ መተማመን ለሰፈነባት ኢትዮጵያ መሠረት መጣል ነው፤ ይሄም እንደሚሳካ ተስፋችን ትልቅ ነው ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡
ባለ ተስፋዋ ሀገር ኢትዮጵያ የተስፈዋን ፍሬ ታይ ዘንድ እርስዎስ ምን አስተዋጽኦ ያደርጉ ይኾን?
Via (አሚኮ)