የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያን፣ በሀገራዊ እና በወቅታዊ ዐበይት ጉደዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳለፈ። ፈር የለቀቁ አሰራሮችና የመግለጫ አሰጣጥ ላይ መመሪያና ህግ ማውጣቱ የተመለከተ ሲሆን በርካታ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አስተላለፈዋል። ቤተክርስቲያኗ ሃዋሪያዊ ምግባር ባልተከተሉ አባቶች ሳቢያ ዋጋ መክፈሏም ተመልክቷል። ቤተክርስቲያኒቱን የማይወክል፣ ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጭ የሆኑ አካሄዶችን አውግዟል። ገደብም ጥሏል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሲጠናቀቅ በዐበይት እና ወቅታዊ የሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል። ውሳኔውን አስመልክቶ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ብፁዕነታቸው በመግለጫቸውም፦
በቅድስት ቤተክርስቲያን እና በሀገሪቱ መንግሥት መካከል ሊኖር ስለሚገባው መልካም የሥራ ግንኙነት በቅዱስ ፖትርያርኩ መሪነት ከመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር የሚመካከር የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ልዑክ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል።
በመላው ሀገሪቱ በተፈጠሩ ግጭቶች የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከግጭት እና ከጥፋት ድርጊት ተቆጥበው የተፈጠረውን አለመግባባት እና ግጭት በውይይት እንዲሁም በምክክር እንዲፈቱ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ጥሪውን አቅርቧል።
በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ምክንያት ለፈረሱ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች የከተማ አሥተዳደሩ ምትክ ቦታ በመስጠት እና ቤተክርስቲያንን ወደ መልሶ ማልማት እንድትገባ ድጋፍ በማድረግ በተሰጠው ምትክ ቦታ ላይም የከተማው ፕላን በሚፈቅደው መሠረት የመልሶ ማልማት ሥራው እንዲከናወን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።
የሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በረቂቅ አዋጁ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ብሎ ያመነባቸውን የማሻሻያ ሐሳቦች በማዘጋጀት ለሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም እንዲላክ እና ረቂቅ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት የተሰጡት የማሻሻያ ሃሳቦች በረቂቁ ስለመካተታቸው ክትትል የሚያደርግ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል።
ከሀገሪቱ ውጭ ባሉ አሕጉረ ስብከት መደበኛ አገልግሎት ለመስጠት የሚላኩ አገልጋዮች በክፍሉ ሊቀጳጳስ ሲጠየቅ በሙያ ብቃታቸው፣ በምግባራቸው እና በመንፈሳዊነታቸው የተመሰከረላቸው አገልጋዮች ከሁሉም አሕጉረ ስብከት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቅራቢነት በውድድር እየተለዩ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲላኩ ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል።
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሥተዳደር ዘመኑን የዋጀ እንዲኾን ቅዱስ ሲኖዶስ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ በማጽደቅ ወደ ትግበራ እንዲገባ የወሰነ በመኾኑ በዚሁ መሠረትም ለአፈፃፀሙ ያመች ዘንድ በባለሙያዎች ተዘጋጅቶ የቀረበውን መዋቅራዊ አደረጃጀት በማጽደቅ በሕገ ቤተክርስቲያኑ እና በቃለ ዓዋዲው ተካቶ ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበውን የ2017 ዓ.ም ዓመታዊ በጀት በማጽደቅ በሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ በመወሰን ላለፉት ቀናት ሲያካሄድ የቆየውን መደበኛ ሥብሠባውን አጠናቅቋል።
በመግለጫቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ የሚተላለፉ መልዕክቶች ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉና ቅዱስ ሲኖዶስ የማይቀበላቸው እንዲሁም በጥብቅ የሚያወግዛቸው መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተክርስቲያንና ለሀገራችን ህዝቦች ጠቃሚ ውሳኔ አሳልፏል ብለዋል በመግለጫቸው፡፡
በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተመሥርቶ አባታዊ ምክርና ተግሣጽ ማስተላለፍ ከቀድሞ ጀምሮ የነበረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው መሆኑን አንስተው ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ የሚተላለፉ መልዕክቶች ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉና ቅዱስ ሲኖዶስ የማይቀበላቸው እንዲሁም በጥብቅ የሚያወግዛቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ወደ ፊት እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም ወጥ የሆነ የመግለጫ አሰጣጥና የትምህርተ ወንጌል ተልእኮ ሕገ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምልዐተ ጉበኤ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑንም ጠቁመዋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ ላይ በሰፊው ተወያይቶ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ሀሳቦችን ለሚመለከተው የመንግስት ተቋም መላኩን ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ከመጽደቁ በፊትም የተሰጡ የማሻሻያ ሐሳቦች በአዋጁ ስለመካተታቸው ክትትል የሚያደርግ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟልም ነው ያሉት በመግለጫቸው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን የዐሥር ዓመት መሪ ዕቅድ በማጽደቅ ወደ ትግበራ እንዲገባ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
ለአፈጻጸም እንዲያመችም የተዘጋጀው መዋቅራዊ አደረጃጀት በሕገ ቤተ ክርስቲያኑና በቃለ ዓዋዲው ተካቶ ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑን ጠቁመዋል፡፡
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበው የ2017 ዓ.ም ዓመታዊ በጀት ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውልም ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑን ከመግለጫው ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ሲኖዶስ በአገሩቱ ስላለው ግጭትና ሰለ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በመግለጫው አካቷል። በዚሁ መግለጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ፥ ” በመላው ሀገራችን በተፈጠሩ ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና የሰላም ዕጦት በርካታ የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት እንደቀጠለ በመሆኑ በእጅጉ እናዝናለን ” ብሏል።
ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከግጭትና ከጥፋት ድርጊት ተቆጥበው የተፈጠረውን አለመግባባትና ግጭት በውይይትና በምክክር እንዲፈቱ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በአጽንኦት ጥሪ አቅርቧል። በሌላ በኩል ቅዱስ ሲኖዶስ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አካሄድ ጋር በተያያዘ ቅሬታ እንዳለው ገልጿል።
” ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት አዋጅ መረዳት እንደሚቻለው ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ ሁኔታ ሀገራዊ ችግሮችን በምክክርና በውይይት ለመፍታት የተቋቋመ መሆኑን ተረድተናል ” ብሏል።
ይሁን እንጅ ” ሀገረ መንግሥትን ከመመሥረት ጀምሮ በአስታራቂነትና በሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ለሆነችው እናት ቤተ ክርስቲያን እስከአሁን ድረስ በይፋ የቀረበ የተሳትፎ ጥሪ ሳይኖር ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታንና አጀንዳ መረጣ አጠናቆ ወደ ምክክር ትግበራ እየገባ መሆኑ ቅር አሰኝቶናል ” ብሏል።
በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱ ተሳትፎና አጀንዳ የማቅረብ መብቷ እንዲረጋገጥ ከኮሚሽኑ ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ተከታትሎ ለፍጻሜ የሚያበቃ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ መሰየሙን አሳውቋል።