ምንጩ ያልታወቀ ንብረት የሚወረስበት ረቂቅ አዋጅ መውጣቱና ለምክር ቤት መላኩን ተከትሎ የሚሰማው ጩኸት ከወትሮው ለየት ያለ ሆኗል። አዋጁ ከመጽደቁ በፊት ከወዲሁ ጫና ለመፈጠር ርብርብ ተያዟል። በርብርቡ የገባቸውም ያልገባቸው እየተሳተፉ ነው። ጉዳዩ ግን የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ወንበራቸው ላይ የነበሩበትን አራት ዓመትና የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ስድስት ዓመት የስልጣን ዘመን የሆነውን ያሰላ ረቂቅ አዋጅ በመሆኑ ተግባራዊነቱን በጉጉት መጠበቅ እንደሚሻል “ገብቶናል” የሚሉ እየተናገሩ ነው።
ዓመጽና ቁጣ ሲባባስ ኢህአዴግ አገዛዙን በአቶ ሃይለማሪያም በኩል አደረገ። ከየአቅጣጫው የነበረው የ”በቃን” ትግል እየተፋፋመ የሄደበት ይህ ጊዜ መረጃው ላላቸው አገሪቱ ስትዘረፈ የነበረው ንብረት የሸሸበትና በብዛት ቋሚ ንብረት ላይ የዋለበት ወቅት ነው። በተለይም በሁሉም አቅጣጫ ኦሮሚያና አማራ ክልል የፈነዳው ተቃውሞ ሲካረር ሃብት ማሸሽና ቋሚ ንብረት መግዛት በርክቶ ተመዝግቧል። ኑሮውም እየጋለ ሄዷል።
ሃይለማሪማ ሌብነት ላይ እንደሚዘምቱ በተደጋጋሚ ቢናገሩም የተተበተቡበት የሌብነት ድር፣ በግል ካላቸው ስልታንን በቅጡ የመጠቀም ድክመት ጋር ተዳምሮ እንደ ፎከሩ ሄዱ። እንደዛቱ ተሰናበቱ። እንኳን ሌብነትን ሊታገሉ “የመለስ ሌጋሲ ወይ ሞት” ብለው ከቋሚው ይልቅ ለሙት መንፈስ ሰግደው አለፉ።
ለውጡ ከመጣና ሃይለማሪያም በ”በቃኝ” ሲለቁ አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲተኩ ዝርፊያው፣ ሃብት ማጋዙ፣ ቋሚ ንብረት ለመግዛት የተፈጠረው መስገብገብና የቋሚ ንብረት ዋጋ በፍጥነት መሰቀል ላስተዋለው የጤንነት እንደማይመስል የረቂቅ አዋጁን ሚስጢር ቀንጨብ አድርገው ያካፈሉን ነግረውናል።
“የኢሚግሬሽን አዋጅ ማሻሻያ፣ በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰልና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው ረቂቅ አዋጅ እና የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ረቂቅ አዋጆች ሁሉም ተመጋጋቢ እንደሆኑ እነዚሁ ወገኖች ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ ይተላለፉ የነበሩ ዕግዶችን እና ውሳኔዎችን ለአስፈጻሚው አካል የሚያጋሩ በመሆናቸው የህግ የበላይነትን አደጋ ላይ እንደሚጥሉ አስተያየት የተሰጠባቸው እነዚህ ረቂቅ ህጎች እንደሚባለው ሳይህን ጸድቀው ተግባር ላይ ሲውሉ መንግስት ሌብነትን ለመዋጋት ቆርጦ መነሳቱን የሚያሳዩ እንደሚሆኑ መረጃውን የሰጡን በሙሉ እምነት ይናገራሉ። ጫጫታውም አካሄዱ የገባቸውና እነሱ ያሰማሩዋቸው ክፍሎች የጀመሩት ዘመቻ ብቻ እንደሆነም አምልክተዋል።
ሌብነትን ለመዋጋት የተቋቋመው ብሄራዊ ኮሚቴ ከሺህ በላይ ጥቆማ እንደደረሰው የሚናገሩ ወገኖች መንግስት ወደ እርምጃ ያልገባው ዕግሩን በደንብ ባለማጽናቱ፣ በተለይም ከትህነግ ጋር የገባበት ህግ የማስከበር ዘመቻ ገድቦት ነበር። ያም ቢሆን ግን ሌብነትን ለመዋጋት የሚያስችል አቅም ሲገነባ እንደነበር ገልጸዋል።
ከልዩ የሙስና መርማሪና የኢኮኖሚ ደህንነት ስልጠና ጀምሮ የቀረቡ ጥቆማዎችን በዝግ ሲያጠኑ የነበሩ ስራቸውን አጠናቀዋል። መንግስትም አሁን ላይ ክንዱ በመፈርጠሙ እርምጃ ለመውሰድ ስለማይቸገር ህግ ማዘጋጀት አግባብ ሆኖ መገኘቱን የዜናው ሰዎች ያስረዳሉ።
ሽሽት ስለሚኖር በቀረበው ጥናት መሰረት ተፈላጊዎች ከአገር እንዳይወጡ አሰራሩን ማሳጠር አግባብ በመሆኑ ቀደም ሲል በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካልሆነ በስተቀር ከአገር የመውጣት መብትን የሚነፍግ አካል አልነበረም። ህጉ በተደጋጋሚ እየተጣሰ በርካታ ሰዎች ከአገር እንዳይወጡ ሲደረግ ቢቆይም በህግ ደረጃ ስልጣኑ የፍርድ ቤት ብቻ ነበር። አሁን ግን ማንኛውም ሰው ከአገር እንዳይወጣ የማገድ ሥልጣንን ለኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሚሰጥ ረቂቅ ተዘጋጅቷል።
ይህ ህግ የሰንብአዊ መብትን እንደሚጥስ በመግለጽ ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው አስተያየት የሚሰጡ አሉ። የህጉ ይዘት በይፋ ማብራሪያ ሳይቀርበበት ትችት በዝቶበታል። የዜናው ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ “ዘመቻው ከድሆች አጥንት ላይ ሲግጡ በነበሩ አካላት ላይ በፍጥነትና በአጭር ጊዜ የሚሰራ በመሆኑ የሚባለው ችግር አይኖርም። ህጉ በሚያዘው መሰረት ጉዳያቸው የሚታየው በፍርድ ቤት በመሆኑ ስጋት አይኖርም”
የግል አስተያየታቸው እንደሆነ ጠቅሰው ” እግድና የፍርድ ቤት መከላከያ በማውጣት ዘመቻውን የሚያስተጓጉሉ አካሄዶችን መንግስት ለማስቀረት ሲል፣ ረቂቅ አዋጁን እንዳዘጋጀ አስባለሁ” ብለዋል።
ጫጫታ ያስነሳው ‹‹የንብረት ማስመለስ አዋጅ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ረቂቅ አዋጅ ሲሆን አስር ዓመት ወደ ሁዋላ ተመልሶ የሚሰራ ነው። ረቂቅ ህጉ “ሃብትህን ከየት አመጣኸው” የሚል ጥያቄ ያነሳል። በአጭሩ መንግስት ለሚጠረጥረው ሃብት ማስረጃ አቅርብ የሚል ደብዳቤ ይሰጥና በቀነ ገደብ ምላሽ እንዲቀርብ ያዛል።
ለምሳሌ ከውጭ አገር ሆኖ የውጭ ምንዛሬ ከሚሰበስቡ ነጋዴዎች በመስማማት (በጥቁር ገበያ ማለት ነው) ገንዘብ አከማችቶ ሃብት የገዛ ሰው፣ ወይም ቤተሰብ ” ይህን ቪላ ቤት ከየት አመጣኸው ወይም አመጣሽው” ሲባሉ ” ከውጭ አገር ልጄ፣ አጎቴ፣ ባሌ፣ሚስቴ፣ ዘመዴ…ልኮልኝ ነው” የሚለው መልስ ረቂቁ ህግ ሲጸድቅ ከቀልድ ያለፈ ምላሽ አይሆንም።
“ሌብነትና ማጭበርበር ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚጀመረው ዘመቻ ፊሽካ ሲነፋ፣ ጨዋታው ሁሉ በስነድ ይሆናል” የሚሉት የዜናው ሰዎች፣ ይህ ዘመቻና የዘመቻው ዕቅድ የሚያስፈራቸው በጥቁር ገበያ የሚነግዱትን፣ ህግ ተላልፈው በድሃው ጫንቃ ላይ ሲዘሉ የነበሩትን እንጂ ሰላማዊ ዜጎችን እንዳልሆነ አስመረውበት ነው የተናገሩት።
“ሌባ መንግስት፣ የሌቦች ስብስብ መነግስት” በሚል ሲተች የነበረ መንግስት ሌብነት ላይ ጎራዴ ሲመዝ ሚዲያው “አይዞህ ከጎንህ ነን” በሚል ሊያበረታታ ሲገባ የሰጉ ሌቦችን ጩኸት ማስታጋባቱ ሲያልፍ ከማስተዛዘብ ሌላ የሚፈይደው አንዳችም ጉዳይ እንደሌለ ዜናውን ያጋሩን ክፍሎች ገልጸዋል።
ከውጭ በተላከ ገንዘብ ሀብት አፍርቶ የተላከበትን ደረሰኝ ያላቀረበ ሰው ወይም ሊታወቅ ከሚችል ገቢው በላይ ሀብት አፍርቶ ምንጩ ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ ያልቻለ ሰው፣ ንብረት በመንግሥት እንዲወረስ የሚፈቅድ ድንጋጌ የያዘው ረቂቅ አዋጅ እንዴት ህጋዊ ለሆኑ ዜጎች አስፈሪ ሊሆን እንደሚችል ሊገባቸው እንዳልቻለ እነዚሁ ወገኖች በጥያቄ መልክ ያስቀምጣሉ።
በደፍናው በመብትና በህግ የበላይነት ስም ስጋትን ከመግለጽ ይልቅ በግልጽ “ህገወጥነትንና ሌብነትን መንግስት እንዳይነካ” በሚል መከራከሪያ አደባባይ ቢቀርቡ እንደሚያዋጣቸው ዜናውን ያካፈሉን ወገኖች ተናግረዋል።
በተለያዩ ውይይቶች ህዝብ በግልጽ ስም እየጠራ ሲወቅስ፣ ለአንዳንድ ሃብትና ግንባታዎች ስም እየሰጠ ሲያሽሟጥጥ እንደነበር ይታወሳል። በድንገት ሃብት ያከማቹና የተተኮሱ አብሮ አደጎቻቸውን እየዩ አስማት የሚሆንባቸው ዜጎች መንግስት ርምጃ እንዲወስድ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።
አስቀድሞ ፍንጭ መስጠት አግባብ ባለመሆኑ እንጂ ከውጭ ምንዛሬ ለቃሚዎች ጋር በተያያዘ አገሪቱ ላይ የተፈጸመው ወንጀል የከፋ ነው። ወደ አገሪቱ የሚገባውን ምንዛሬ በውጭ አገር ሆኖ ማፈን ብቻ ሳይሆን፣ የተዘርፈና በኮንትሮባንድ የተሰበሰበ ገንዘብ በመርጨት አገር ቤት የገባውንም ምንዛሬ በመልቀም ኑሮውን ያስወደዱ አካላት ላይ ዝምታን የመረጡ ሚዲያዎችን ጉዳይ ህዝብ ሊያጤነው እንደሚገባ ዜናውን የሰጡን ገልጸውልናል። አሁንም ስላልረፈደ ይህን አደገኛ ዘረፋ ሊያወግዙና ሊያጋልጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
“የውጭ ምንዛሬ በጥቁር ገበያ ናረ ” ከሚለው ዜና በላይ በሌብነት ገንዘብ የሚሰበስቡ ከፍተኛ ገንዘብ እያፈሰሱ የዶላር ዋጋን ሲያንሩ ህዝብ በኑሮ ውድነት እንደሚሰቃይ የማይዘግቡ ሚዲያዎች ራሳቸውን ሊመረምሩ እንደሚገባ እነዚሁ ወገኖች መክረዋል። መንግስትን ጥፋቱ እየነቀሱ ማሳየትና መተቸት፣ አገር ላይ እዳ የሚጥሉትን ደግሞ ከፖለቲካ ገለልተኛ በመሆን ማጋለጥ የሚዲያ ሚና ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።
ዲያስፖራው ሃብቱን በህጋዊ መንገድ ቢያደርግ እነደሚያዋጣው ያመለክቱት እነዚሁ ወገኖች፣ ለመጠነኛ ጥቅም ሲባል በጥቁር ገበያ የሚፈጸም የምንዛሬ ግብይት ዋጋ የሚያስከፍልበትና በዜሮ ብዜት ባዶ እጅ የሚያስቀርበት ዘመን መቅረቡን ሊያውቁ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ከሁሉም በላይ ምንም የውጭ ምንዛሬ ማግኛ መንገድ ለሌላቸው ጠላቶች ምንዛሬን ማሸከም በምንም መስፈርት ኢትዮጵያዊ እንደማያሰኝም ገልጸዋል።
ተመጋጋቢ የሆኑት ረቂቅ ህጎች ” በጎራዴ” መስለው ሲያቀርቡት መስማታቸውን ጠቁመው አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉ ” በብሄር ስም ጫካ ገብተው በዘረፋ ከፍተኛ ሃብት ያካበቱና ንብረት ያከማቹ፣ በውጭ አገር ሆነው ይህንኑ እንቅስቃሴ እየመሩ ሃብት የሰበሰቡ ስላሉ ለነሱ በርግጥም ጎራዴ ነው” ብለዋል። በቅርቡ በይፋ የሚታይ ዘመቻ ሲጀመር ሁሉም ነገር እንደሚገለጥ አስታውቀዋል።