ወደ ምክር ቤት ከተመሩ ህጎች መካከል ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ማስመለስን አስመልክቶ የወጣው ረቂቅ አዋጅ የሰሞኑ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ መክረሙ አይዘነጋም። የተሳሳተ ትርጉምና ከህጉ እሳቤ በተለየ ትርጉም በመስጠት የተለያዩ አስተያየቶች ቢቀርቡበትም በአዋጁ የማርቀቅ ስራ አባል የሆኑት ሃወኒ ታደሰ የህጉን አጠቃላይ ገጽታ አስረድተዋል። ሃብታቸውን እንዴት እንዳፈሩ ባለቤቶቹ ያውቁታል። እነሱ ቢፈሩ የሚጠበቅ እንደሆነም አመልክተዋል።
“በጥቁር ገበያ ሃዋላ ገንዘብ ሲልኩና ሲቀበሉ የኖሩ ተግባራቸው ወንጀል መሆኑን ተግባሩን ሲፈጽሙ ያውቁታል” ሲሉ ያስታወቁት የህግ ባለሙያ ” መንግስት በህጋዊ መንገድ ሃብት ያገኙ ዜጎች ደጅ አይደርም” ብለዋል። በቀላል አማርኛ ” ገቢያችሁ ይህን ያህል ነው። ይህን ሃብት ማፍራት አትችሉም። ከየት እንዳመጣችሁት አስረዱ ነው የሚባለው” ሲሉ ህጉ አንዳችም አስፈሪ ጉዳይ እንደሌለበት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የመንግስት ኮሙኑኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስይትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ አዋጁን አስመልክቶ በማህበራዊ ገጻቸው የሚከተለውን አስፍረዋል።
ወንጀል አትራፊ መሆን የለበትም
ማንም ሰው ከወንጀል ሊያተርፍ አይገባም።በሠራው ወንጀል መጠየቅ እና ህጋዊ ቅጣት ማግኘት አለበት። ተገቢውን ቅጣት ሲያገኝ ሌሎች ትምህርት ይቀስሙበታል። ህግና ስርዓት ከሚፈቅድላቸው ውጭ በእጃቸው የገባው ሀብት እና ንብረትም ለህዝብ ጥቅም ይውላል። ይህ የሰለጠነው ዓለም እየተገበረ፣ እየተመራበት ያለ እውነታ እንደሆነ ይታመናል። አዲሱ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ ህግም ማዕከላዊ ነጥብ ይኸው እና ይኸው ብቻ ነው፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ አንዳንድ ሰዎች እውነታውን ካለመረዳት ይሁን ሆን ብለው ከረቂቅ አዋጁ መንፈስ ጋር የማይሄዱ እና የተዛቡ መረጃዎችን እያስተጋቡ መሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ እነዚሁ ሰዎች በአንድ በኩል መንግስት ብልሹ አሰራሮችን አልደፈነም፤ ሙስናን አልተቆጣጠረም፥ ህገወጦች ተገቢውን ቅጣት እያገኙ አይደለም በሚል መንግስትን ይከሳሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ይህን እውነታ በማጤን የህግ ክፍተት ያለባቸውን ጉዳዮች አጥንቶና ለይቶ፥ አለም ከደረሰበት ሁኔታ ጋር የሚሄድ ህግና አሰራር ለማበጀት ሲንቀሳቀስ መንግስት የዜጎች የንብረት ማፍራት ህገ መንግስታዊ መብት እንደተጋፋ በማስመሰል የሀሰት መረጃ ያሰራጫሉ፡፡
የራሳችን የሀገራችን ልምዶች እንደሚጠቁሙን በልዩ ልዩ መንገዶች የህዝብን ሀብት የዘረፉ ሰዎች በሠሩት ወንጀል እየተቀጡ ቢመጡም የዘረፉትን ሀብት ግን በሌሎች ሰዎች በማስመዝገብ በህግ ያልተገኘን ሃብት የራሳቸው ሲያደርጉ ቆይቷል። ይህን ሀብት ለማስመለስ ጥረት ቢደረግም ለዚህ አጋዥ የሆነ የተደራጀ እና ወጥነት ያለው አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት ሰዎች ተመሳሳይ ድርጊት እንዲፈፅሙ እየገፋቸው መጥቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ከአንድ አካባቢ የህዝብ ሀብት እና ንብረት ዘርፈው በሌሎች አካባቢዎች ህጋዊ የማድረግ እንቅስቃሴዎች እየተበራከቱ መጥቷል። የዓለም ሀገራት ይህን ችግር ቀድመው በመረዳት ተመሳሳይ ህጎችን ተግባራዊ ከማድረገቸውም በላይ በዚሁ አግባብ ትብብራቸውን ከሌሎች ሀገራት ጋር እያጠናከሩ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን እየተከላከሉ ይገኛሉ።
የኛም አዲሱ የሀብት ማስመለስ ረቂቅ ህግ ይህን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ይታመንበታል። ከአዋጁ ጀርባ ያለው ምክንያት ወንጀል አትራፊ መሆን የለበትም የሚል ነው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ለቅሶው ከየት የመነጨ ነው የሚል ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል። እውነት ለዜጎች መብት ከመቆርቆር ወይንስ የቀማኞች መደብ እንዲንሰራራ ከመፈለግ ነው? እንደኔ አስተያየት ግን ለቅሶው ከፍየሏ ሞት በላይ ነው እንደሚባለው ነው።