የጨጓራ ካንሰር ከርስ (Stomach) ተብሎ ከሚጠራው የሆድ ዕቃ ውስጠኛው ክፍል ሕዋሳት ላይ የሚነሳ አደገኛ የካንሰር በሽታ ሲኾን በዓለም አቀፍ ደረጃ የአምስተኛነት ደረጃን እንዲሁም ሦስተኛው የካንሰር-ነክ ሞት መንስኤ መኾኑን የአሜሪካ የካንሰር ማኅበር (ACS) መረጃ ያሳያል።
መንስኤዎች (Causes)
የጨጓራ ካንሰር ትክክለኛ መንስኤ ባይታወቅም በርከት ያሉ ነገሮች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡-
1. ሥር ሰደድ ኤች.ፓይሎሪ የጨጓራ ባክቴሪያ (H. pylori) ኢንፌክሽን፡-
- አመጋገብ፡- በጨው የበዛበት፣ ቀይ የጮማ ስጋ እንዲሁም አነስተኛ አትክልትና ፍራፍሬን ማዘውተር
3. ከመጠን ያለፈ ውፍረት
4. አልኮል መጣጠት፤ የንባሆን ማጨስ
5. የጨጓራ አሲድ በጉሮሮ ምልሰት በሽታ (GERD) የመሳሰሉት …
6. ጨጓራ ካንሰር በሽታ ቅርብ ዘመድ ላይ የሕክምና ታሪክ ይበልጥ ለሌላኛው ስጋትን ይጨምራል።
ክሊኒካዊ ባህሪዎች/ ምልክቶች (Clinical features)፦
የጨጓራ ካንሰር መልካም ያልኾነው ጎኑ ካንሰሩ እየገፋ ሲሄድ እንጂ በመጀመሪያዎቹ ኹነቶቹ ላይ ምልክቶች ላይከሰቱ ይችላሉ።
ምልክቶችን ማሳየት ሲጀምር ደግሞ፦
በጉልህ የሚታወቅ ክብደት መቀነስ (significant weight loss)
በላይኛው የሆድ ክፍል ላይ ምቾትን የሚነሳ፡ የማያቋርጥ ና እየተባባሰ የሚሄድ የሆድ ህመም
ትንሽ እንደተመገቡ ቶሎ የመጥገብ ስሜት (early satiety)
ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ (nausea &Vomiting) እንዲሁም ደግሞ በተለይም ወደ ጉሮሮ የተጠጋ አይነት ሲኾን ለመዋጥ መቸገር እና ሕመም (odynophagia/dysphagia)
በላይኛው የሆድ ክፍል ውስጥ የመቃጠል ስሜት (heart burn)
የምግብ አለመፈጨት/መበርከት ስሜት (Indigestion)
የምግብ ፍላጎት ማጣት (loss of appetite)
ሌላው ደግሞ የጨጓራ ካንሰር በግልጽ አሊያም ሳይታይ ደም መፍሰስን ሊያስከትል የሚችልበት ዕድል ያለው ሲኾን ይህም የሰገራ ደማቅ ጥቁርነት (melena/black tarry stool) አሊያም ደም በትውከት ጋር (hemoptysis) ያሳያል፤ ይኸውም ከፍ ሲል የደም ማነስ የጤና ችግርን በማስከተል እንደ ራስን ማዞር፣ በጆሮ የሚያቃጭል ድምፅ መሰማት፣ የዕይታ ብዥታ፤ ሚዛንን ለመጠበቅ መቸገር፣ ፈጣን የልብ ምትን መሰማት ወዘተርፈ… )
ምርመራዎች (Investigations)፡-
የጨጓራ ካንሰር ምርመራው ብዙ ጊዜ ሕሙሙ ከላይ የዘረዘርናቸውን ምልክቶች በሚያሳይበት ኹነት ላይ በመነሳት የሚከውን ሲኾን ውጤቶቹን ለማሻሻል ቀደም ብሎ በተለይም ዕድሜያቸው ከአርባዎቹ እና አምሳዎቹ በላይ ላሉ ጎልማሶች እንደ አስቸኳይ እና ድንገተኛ ማስጠንቀቂያ ዓርማ (Red Flags) በመውሰድ መገንዘብ እና ተገቢውን ምርመራ ማድረግ በጣም ወሳኝ ነው። ነገር ግን እንደአለመታደል ኾኖ፣ የጨጓራ ካንሰር በመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ላይ ምንም አይነት ምልክትን ላይታይበትም ይችላል።
ከምርመራዎቹ መካከል እነሆ፦
ሀ. የላይኛው ሥርዓተ ልመት ኢንዶስኮፒ (Upper GI endoscopy)፡- ካሜራ የተገጠመለት ቀጭን እና ተጣጣፊ ቱቦ ሲኾን ይኸውም በአፍ በኩል እንዲገባ ተደርጎ የላይኛውን ውስጠ ሆድ ዕቃን ይመረምራል፤ ባዮፕሲ (የሕዋስ ናሙናዎችን) ለአጉሊ መነጽር ትንታኔ ቆርጦ ለመውሰድም ያገለግላል።
ለ. የማንጽባራቅ ኤክስሬይ (Contrast X-ray)፦ ይህ የምርመራ አይነት ደግሞ የራጅ ምርመራ ከመደርጉ በፊት ሕሙማን ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጁ ውህዶችን እንዲወስዱ እና ቅጥሎም ራጅ በማንሳት በከርስ ውስጥ ያሉ ማገጃዎችን ወይም ቁስሎችን ለመፈለግ ያገለግላል።
🔭ሐ. ሲቲ ስካን (CT Scan)፡- ይኽ የምርመራ አይነት ደግሞ ካንሰሩ በየት በኩል እንዳለ እና ወደ ሌሎች የአካል ክፍሎች የመዛመት ኹኔታን በዝርዝር ለመገምገም ያግዛል።
መ. ከላይ ከጠቀስናቸው በተጨማሪ ለሕሙሙ ይበጃሉ ተብሎ የሚታሰብ ሌሎች አጋዥ (supportive diagnostic tests)፣ የውስብስብነት እና የወደፊት ዕጣ ፈንታውን ኹነት የሚነግሩ ልዩ ልዩ የቤተ ሙከራ እና የምስል ከሳች ምርመራዎች ሊከወኑ ይችላሉ።
ሕክምናው (Treatment)
የጨጓራ ካንሰር ሕክምና በካንሰሩ ያለበት ደረጃ ላይ ተመስርቶ የሚከውኑ እንደመኾናቸው መጠን የሚለያዩ ቢኾንም ቀጥሎ የቀረቡት አማራጮች ደግሞ አሁን ላይ ባለው የሕክምና ሳይንስ ከሚሰራባቸው መካከል፡-
1. ቀዶ ሕክምና፦ በጣም የተለመደው ዘዴ ሲኾን የአሰራር አይነቶቹ ደግሞ እንደየኹኔታው ይለያያል፤ ይኽም በአንዳንድ ኹኔታዎች ከርስን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ (gastrectomy) አስፈላጊ ሊኾን የሚችልበት ዕድል ያለ ሲኾን ሌላ ጊዜ ደግሞ የተወሰነውን ክፍል ብቻ ቆርጦ ማስወገድ በቂ ይኾናል።
2. የፀረ ካንሰር መድኃኒት ሕክምና (Chemotherapy/ኬሞቴራፒ)፦ የካንሰር ሕዋሳትን ለመግደል የሚያገለግሉ መድኃኒቶች ሲኾኑ ከቀዶ ጥገናው በፊት (neoadjuvant) ዕጢዎችን ለመቀነስ አሊያም ከቀዶ ሕክምናው በኋላ የተደጋጋሚነት/የተኪነትን (recurrence) አደጋን ለመቀነስ ሲባል ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላል።
3. የጨረር ሕክምና (Radiotherapy)፦ የካንሰር ሕዋሳትን ለማጥፋት ከፍተኛ ኃይል ያላቸውን ጨረሮች በመጠቀም በ ለከፍተኛ ነቀርሳዎች ከኬሞቴራፒ ጋር አብሮ (Chemoradiotherapy )ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።
- የድጋፍ እና እንክብካቤ ሕክምና (Supportive and Palliative Care):- ከላይ ከጠቀስናቸው በተጓዳኝ አብሮ እንዲሁ በተለይም ለመጨረሻው ደረጃ ለደረሰ እና ወደ ብዙ ቦታ ካንሰር ከተሰራጨ ደግሞ ለሕሙማን የድጋፍና በርህራሄ ማገዝ ሕክምና (supportive and palliative Care) ክብካቤን እንዲያገኙ ይደረጋል።
የወደፊት ዕጣ ፈንታ/ትንበያ (Prognosis):-
የጨጓራ ካንሰር ያለበት ሕሙሙ በሕይወት የመቆየት ዕድሉን ስንመለከት ደግሞ በምርመራ የተገኘው ደረጃ ላይ የሚወሰን ይኾንና ለምሳሌም ከፍተኛውን ደረጃ አራት (stage IV) የሚባለው ጨጓራ ካንሰር ለአምስት ዓመት በሕይወት የመቆየት ዕድልን ብናይ ከ5% እንደማያልፍ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
መከላከያ መንገዶች (Prevention)፡-
የጨጓራ ካንሰርን ሙሉ በሙሉ ቀጥ አድርጎ ለመከላከል የሚያስችል የተረጋገጠ መንገድ ባይኖርም፣እነሆ እንደሚከተሉት ያሉትን የአኗኗር ዘይቤዎች መከተል ግን አደጋውን ለመቀነስ ይረዳሉ። እሊህም፡-
በፍራፍሬ እና አትክልት የበለፀገ አመጋገብን ማዘውተር እንዲሁም ጮማነት የበዛባቸውን ቀይ ስጋዎችን እና ጨዋማ ምግቦችን መገደብ።
ሲጋራን አለማጨስ፡-
ጤናማ ክብደትን መጠበቅ፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ፦
የኤች.ፓይሎሪ ጨጓራ ባክቴሪያ ኢንፌክሽን ከተገኘ ይኽንኑ ማከም የመሳሰሉት ኹሉ ጉልህ የኾነ ጠቀሜታ አላቸው።
ዋቢዎች | References
➻ Schwartz Principles of Surgery 11th edition
➻ UpTodate 2024 online version
➻ America Cancer Society websites
ሠናይ ጤንነት ተመኜን!
ዶ/ር ፍሥሓ ጓዴ: Medical Intern, SoM, DTU
https://t.me/nisirhikimna