እባክዎ ክቡር ፕሬዜዳንት ከታሪክ ተወቃሽነት እንዲድኑ በዩንቨርስቲው የሚታየውን ክፍተት ቀና አስተሳሰብ ካላቸው ጋር በመምከር ዩንቨርሲቲው ሊደርስ የሚችልበት ደረጃ አድርሱት።
መካነ አዕምሮ እውቀት ፤ እውነት ፣ ጥበብና የማደግ ህልም የምንሻበትና ከገዛ ራሳችን ጀምሮ ስለሁሉ ለውጥ የምንተጋበት ታላቅ ሥፍራ ነው፡፡
እውቀት ፣ክህሎትና አመለካከት ከዘመን ፍሰት ጋር እየተመመ ወይም እየተላተመ እዚህ ደርሷል፡፡
ሀገራችን በከፍተኛ ትምህርት ዓይኗን ስትገልጥ ደረጃውን በጠበቀና ጥራቱ የተመሰከረለት እንዲሆን ሆኖ ነበር የተዋቀረው። በዚያንጊዜ ኮሌጅ ይባል በነበረበት ወቅት፤ ምጡቅ ብሩህ አእምሮ ያላቸው ተፈትነው፣ ተመዝነው፣ ተመርጠው ነበር ይገቡ የነበረው። አስተዳደራዊ ሥርዐቱ፣ የመምህራኖቹ ጥራት፣ የተማሪዎቹም ብቃት የተጣጣመ ነበር።
ከዚያን ጊዜ አንስቶ በእድገት እና በአጋጣሚ ንጉሠ ነገስቱ ቤተመንግሥታቸውን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ለእውቀት መቅሰሚያነት እንዲሆን ወስነው ሰጡ።
የመጀመርያዎቹ በዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንትነት ይመሩ የነበሩት የካናዳ ተወላጆች ሆነው ሥርዐተ ትምህርቱንም አዋቅረው ከብዙ የውጭ ዩኒቭርስቲዎች ጋር ግንባር ፈጥረው መልካም ደረጃ አድርሰውታል።
በኋላም ኢትዮጵያዊያን እንዲመሩት ሲደረግ ደረጃው እንዳይወርድ መምህራኑ ካናዳውያን ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር በመሆን የትምህርት ስርዐቱን ለማዘመን በሚያስችል መልኩ የመግባበቢያ ሰነድ ከበርካታ እውቅና ዓለም አቀፍ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመፈራረም እራሱም ታዋቂ ለመሆን የበቃ ዩኒቨርስቲ ሆኖ ነበር።
አሁንስ?
ዩኒቨርስቲያችን የነበረውን እውቅናና ተቀባይነቱን ያወረደው በአንድ ጊዜ፣ የዓመታት የማስተማር ልምድና እውቀት ያላቸው ተመርጠው፣ ከሃገር ውጪ ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ የነበሩትን ከ40 በላይ መምህራን በችሎታ ማነስ በሚል ሰንካላና የማይታመን ሰበብ እንዲገለሉ ሲደረግ፣ ዩኒቨርስቲው እራቁቱን ቀረ። አዳዲስ መምህራን ሥራውን እንዲረከቡ ሲደረግ፣ አዲስ ተረካቢዎቹም አቅማቸውና ልምዳቸው በፈቀደ በወቅቱ የነበሩትንና ቀጥለው የሚቀላቀሉት አስተማሪ በማጣት እንዳይስተጓጉል ጥረው አሁን ያለበት አድርሰዋል።
አሁንስ?
“ቆሻሻ ያለው እጅ በሽታ” የሚባሉት የአንጀት ህመምና ኮሌራን ጨምሮ ነው፡፡
ቆሻሻ ያለው ዕውቀትም የሀገርን ውስጣዊ ህመም ከማባባስ በዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡
አሁንስ? ደግመን እንጠይቃለን፡፡
አሁን ግን ዩኒቨርሲቲውና ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ የተግባቡ አይመስልም። ቀደም ሲል የተገለሉት በከፊልም ቢሆን ተመልሰዋል። ቀደም ሲል ሲሰሩ የነበሩት ልምዳቸውን አካብተው የያሉበትን ክፍል(ዲፖርትመንት) በበቂ ሊወክሉና ስለሃገራችን እውነታ ሊናገሩ ሊሞግቱ፣ የውጭ ሃይሎችን ድንፋታ ሊያቀዘቅዙ ይችላሉ። ዪኒቨርስቲያችን በተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድም ፈራሚዎቹን በመጋበዝ በሃገር ውስጥ ያሉትን በማካተት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ አውደ ርዕዮች በማዝጋጀት የሀገራችንን ችግሮችና መፍትሔውን፣ በሀገራችን ላይ የሚሰነዘረውን የተዛባ አስተያየት ሊያቃኑ እንዲችሉ መምከር መደገፍ የሚያስችል መርሃ ግብር ሊነድፉና ለውጭው ዓለም ሊያሳዩ፣ ሊገልፁ እየተቻለ ለምን ችላ ተባለ የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
ዩንቨርስቲያችን አንድ የኤፍ ኤም ሬዲዮ አለው፣ጣቢያው በብዛት ስለ እንግሊዝ፣ ጣልያን፣ ስፖኒሽ የኳስ ቡድኖች ነው የሚሰማበት። ይህን ሳዳምጥ ምናለ እነዚህ ሰዎች አጠገባቸው ያሉትን ምሁራን በጣቢያቸው እያቀረቡ በተለያየ በሀገራችን ላይ ስለሚነዛው የሀሰት ቱልቱላ እውነቱን ቢያስታውቁ ብዬ እቆጫለሁ።
ይህን ቁጭቴን የጎንደር ዩንቨርሲቲ በአግባቡ አስጠንቶ አንድ ቁምነገር ያለው በጥናትና በምርምር የተደገፈ መፅሐፍ ማሳተሙን ሳይ ፣ ብቸኛው ተዘዋዋሪ ሞጋችና የተማሪዎችን ጥማት የሚያርሰው ዶ/ር ዳኛቸውን ሳይ ተመስገን ብልም ፣ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲስ መች ይሆን ዶ/ር ዳኛቸውንና የአዲስ አበባን ዩንቨርስቲዎችን ሞጋች ምሁራንን የሚያገናኘው? ብዬ እንደገና እቆጫለሁ ።
እባክዎ ክቡር ፕሬዜዳንት ከታሪክ ተወቃሽነት እንዲድኑ በዩንቨርስቲው የሚታየውን ክፍተት ቀና አስተሳሰብ ካላቸው ጋር በመምከር ዩንቨርሲቲው ሊደርስ የሚችልበት ደረጃ አድርሱት።
የሬዲዮ ጣቢያውም በማይረባ የውጭ የኳስ አበደች ፕሮግራም ከሚሞላው ፊቱን መልሶ የሚሻሻልበተን መንገድ የሚጠቁም እንዲሆን ቢደረግ ጠቀሜታው የበዛ ይሆናል።
ከፍ ካለ አክብሮቴ ጋር።
eshetu1943@gmail.com