ትግሉ ሲጀመር እንዲህ ነበር። የትግሉ አካሄድና ስልት ገና ታሪክ ለመሆን ስላልበቃ ክርክር የለም። በዚሁ ትውልድ በስድስት ዓመት ዕድሜ ውስጥ ያለ ስለሆነ ማስተባበያ የለውም። እናም ሲጀመር እንዲህ ነበር። “ዋይ ዋይ ብልጽግና” ትግሉ እዚህ ደረሰ “ውሮ ወሸባዬ” የሚሉ ድምጻቸውን እየሳሉ ነው። ወደ ትግሉ አጀማመር
ሲጀመር – አብሮ አደጎቹ፣ ዕቁብ ሲታጡት የነበሩ፣ ጎረቤቶቹ፣ ያበደራቸው፣ የተበደራቸው፣ በመቃብር አብረው አፈር የመለሱ፣ በሰርግ አብረው የተውረገረጉ … ሁሉም ተረስቶ አደቡበት። አሴሩበት። ከዛም በደቦ መርጠው አሳደዱት፣ በደቦ ወረሩት፣ በደቦ ፈረዱበት፣ በደቦ ወረዱበት፣ እጃቸው ላይ ያለውን ሁሉ አዘነቡበት፣ ቢጮህ፣ውለታ ቢቆጥር፣ ቢቃትት፣ ቢያጣጥር ምናቸውም አልሆነ፣ በደቦ ገደሉት፣ ሲጥ አደረጉት!!
እያሽካኩ “አይበቃም” አሉ … ሰቀሉት፣ ልብ በሉ በደቦ ነው፤ አሁንም “አልበቃንም” አሉና ሬሳ ሰቅለው በአለት ወገሩ። በድርጊታቸው ጮቤ እየረገጡ ቪዲዮ ቀረጹት፤ ተቀረጹ። በስራ ክፍፍል መመሪያው መሰረት በቅጽበት በማህበራዊ ገጾች እንዲበተን ለሁለተኛው ቡድን ተላከ። በደቦ፣ በፍጥነት፣ በትሥሥር ህዝብ ይህን ” ጀብድ” እንዲያይ ተደረገ …. ከዛስ?
ከዛማ የሌሊት ተረኞች ተተኩ። “ምን አደረጉ?” እነሱም ደቦ አላቸው፣ በደቦ ቪዲዮውን እያሳዩ ብሶት ማዋለድ … ተያያዙ። ምስሉን ያዩ አነቡ። ” እመቤቴ ምንኛ ዘመን ላይ ደረስን” ስትል ቦሰናም ነፍርቃለች። የትግሉ መሪ ቃል “ብሶእት ነው። እሱኑ ማዋለድ። ማራባት። በፍጥነት ማባዛትና አባዝቶ ማከፋፈል። በየቤቱ “ብሶትን” ማከፋፈል
ያበደው ወደ ሁዋላ ተምዘገዘገ። “ብሶት” ሁሌም ይወለዳል። የትግራይ ነጻ አውጪም ” ብሶት የወለደው፣ የብሶት ልጅ” ነበር። ሲመጣ በመጀመሪያዋ ቅጽበት እንደነገረን ከሆነ ከ”ብሶት” ሽንት፣ “ብሶት” ማህጸን ውስጥ ተጸንሶ፣ “ብሶት” ሆኖ አድጎ፣ አስራ ሰባት ዓመት ሲሞላው “በብሶት” ቀንጭሮ ተወለደ። ይህ ታሪኩ ነው። “የህዝብ ብሶት የወለደው” አስራ ሰባት ዓመት ብሶት ማህጸን ውስጥ ሆኖ በሴራ የቀነጨረ …
አሁንም እሱ እንዳለው “ቀንጭሮ” የተወለደው የሌሎችን “ብሶት” ሊጠርግና ሃሴትን ሊያከናንብ ስነበር ነው። ቸኩሎ ቢውለድ “ብሶትን” ስለማይወክል መቀንጨሩ ግድ ነበር …. እናም “ቀንጭሮ” ተወለደና በታም ቀንጭሮ እንኳን የሌሎቹን የተጸነሰበትን ደደቢትን እንኳን …. ሳይስካለት ሃያ ሰባት ዓመት ተርመጥምጦ፣ ዳክሮ ዳክሮ፣ አገሩን ሁሉ በብሄር በተለወሰ የብሶት ችግኝ ” አረንጓዴ ሌጋሲ መሆኑ ነው” አጥለቅልቆ ወደ ደደቢት ተመለሰ።
እሱ በብሄር ለውሶ ብዘራው ችግኝ “አሽቶ” ልክ ሲደርስ ሳይሰበስበው ወደ መነሻው ኮበለለ። እኮበለለበት ስፍራ ሆኖ በሪሞት ምርቱን የሚሰበስቡ አዘጋጀ። የቀረውም በተተከለበት ፍሬው አራገፈ። ዘሩን ረጨ። ወፎችም ሰዎችም እንስሶችም አግበሰበሱት። ምስኪኖች ሳይወዱ በግድ ከፍሬው የሚጠመቀውን ሽመጠጡት። ከፍሬው የተጋገረውን በሉ። ከዛፉ የሚቀጥፈውን ገመጡ። “ክበር ለዚህ ሌጋሲ ባለቤቶች ሁሉ!!” ትላለች ቦሰና። ” መጥኔ ይህን ሁሉ ሌጋሲ ተሽክማችሁ …” ብላ ደግሞ ትተክዛለች። ወደ ጣሪያው እያየች ለአንድዬ ታጉተመትማለች!! ያበደው ተመለሰ። መነሻውን ቀጠለበት። አዎ “ትግሉ እዚህ ደሷል” ነው
ያብደው በዝናባማውን የአውሮፓ በጋ ድብርት ላይ የሌሊት ተረኛ ተንታኞችን አሰበ። ስለ ደቦው ቅብብሎሽ አሰላ። በጀቱና ስልቱ እንዴት እንደሚነደፍ አብላላ። ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን “ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።
“ትግሉ እዚህ ደረሰ” ሲል አምባረቀ። ባቡር ውስጥ “አጨሷት” ሲል ሰምቶ አናቱ ጋለ። ሰሜን ሸዋ ነፈሰ ጡር የገደሉ በኩራት ሸልለዋል። ማንነቱ የማይታወቅ እንጭጭ ገለው ጀግና ሆነዋል። ኮሽታ በማይሰማበት አገር ባቡር ውስጥ ሆነው “ወንዳታ” የሚሉት ሰው ያልሆነ ደም ፣ ደሙን … ያበደው እንዲሰሙት ” እንኳን ደስ ያላችሁ። ትግሉ እዚህ ደርሷል። ትግሉ ነፍሰ ጡርንም አይምርም። ትግሉ ሽልም ይበላል…” እያለ የቁጩ ስልክ የሚያወራ መስሎ አስተጋባ።
“አምርረናል” አለ ያበደው ” አምርረናል። አህያም ቢሆን ፈርስ ለብልጽግና ከተሸከመ ይወገዳል። በሬና ላም ከሆኑ ገቢ ይሆናሉ። ዶሮዎች ከሆኑ ወደ በረሃ ሄደው እንቁላል ይጥላሉ። የበረሃ የልማት ቱርፋት …” ያበደው ሳያስበው ትን አለውና ሳቁን ለቀቀው … ከብቶቻቸውን ለትግሉ በሚል የተነጠቁ ምስኪኖችን አሰበ። ገበሬ ከብቱ ልጁ ነው። ከገበሬ ከብቱን ከተዘረፈ፣ ሰብሉ ከተወረሰ፣ ማዳበሪያ ከተቀማ እንግዲህ ምን ይቀረዋል? ይቅርታ “ትግሉ እዚህ ስለደረሰ ነው” ያለው ተንታኝ … ያበደው ተፋ!!
ገዳይ አለ። ተገዳይ አለ። አስገዳይ አለ። የዚህ ሁሉ ዕቅድ ነዳፊ አለ። አስፈጻሚዎች አሉ። ያበደው ትንተናውን ቆም አድርጎ ጃዋርን አስታወሰ። ጃዋር ሲፈልግ የጀሃድ ካራ አንስቶ ” አንገትህን” ይላል። ሲያሻው ” ሁለት መንግስት አለ” ብሎ ያዛል። ይናዝዛል። ለዚህ ሁሉ ማስፈጸሚያ ሚዲያ አስፈልፍሏል። ገጀራም አንስቶ፣ ኦሮሞ ፈርስትም ብሎ ያሻውን ሃብት ሰብስቧል። በፍጥነት ለዚህ ሁሉ ስኬት እንዴት እንደበቃ ሲጠየቅ በኩራት ” ብብሄር ማደራጀት ደጋፊ ላማብዛትና ለማነሳሳት ዋናው ቁልፍ ስትራቴጂ ነው። ችግሩ ይህን ሃይል ስልታን ስትይዝ መግራት አለመቻሉ ነው” የዛሬን አያድርገውና ባለ ቀለም ፈስ ይፈሳ የነበረው ጃዋር ሰክኖ …. አይታመንም!! ግን ያንን ሁሉ የጃዋር ተከታይ ብልጽግና ምን አድርጎ አደብ አስገዛው? የቦሰና ጥያቄ ነው።
እንደምን ከረማችሁ? የምሳ መመገቢያ ያጣችሁ። እናንተን ሰላም ሳይሉ ማለፍ አይቻልም። ያብደው የምሳ የሌላቸው ቤተክርስቲያን እንደሚያሳልፉ ሲሰማ አዝኗል። የኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት መላ ሊባል ያስፈልገዋል። አንድ መፍትሄ ይሻዋል። አልቃሾቹና አስለቃሾቹን ለይቶ ጉዳዩን በብልሃት መያዝ ግድ ነው።
አውሮፓ ቤት ያፈራውን ከቤት መቋጠር እንጂ ምሳ እየገዙ መብላት ብዙም አልተለመደም። ችግሩን ለማሳነስ ሳይሆን እወነታውን ለማጋራት ነው። አውሮፓ ከቤት ውጭ ለመብላት ውይይት ተደርጎ፣ በካላንደር ተመዝግቦ በዕቅድ እንጂ ዝም ብሎ ዘው ማለት የለም። ጥቆማ ነው።
ያበደው ከተሸሸገበት ክች ብሏል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለመደገፍም፣ ለመቃወምም የሚያስቸግር ክትባት የሌለው በሽታ በመሆኑ ነው ያበደው መሰወርን የመረጠው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጓደኛህ ያሰበውን ካላሰብክ ያኮርፍሃል። ለሰላምታም ይጠየፍሃል። ጓደኞቻቸውን በአቋማቸው የሚጠሉና የሚቀረቅሩ የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ “ድርጅቶች” ችግራቸውን በውይይት መፍታት አይችሉም በሚል ይከሳሉ። የአንገት በላይ እከኩ ሁሉም ጋር ነው። የአጅሬዎቹ ችግኞች እንዲሁ በቀላሉ አይጠወልጉም።
ተንታኞቹ በደቦ “ያሳያችሁ” ይላሉ ቪዲዮውን ከፍተው። “እንዲህ ያለ ጭካኔ ከየት የመጣ ነው” ይሉና ህዝቡን ይጠይቃሉ። ከብብት ውስጥ በሚመዘዝ ዕምባ ቢጤ ኩርፊያ ሃዘን ለመልበስ እየዳዳቸው ” ይህ መንግስት ይውደቅ ስንል በምክንያት ነው” ሲሉ ያብራራሉ። “ወያኔ ምን አለችን፣ በሰላም ወጥተን እንገባ ነበር” የሚለውን ጥንስስ ይከፈታሉ። የሚገባቸው ድራማው እዚህ ላይ ይገባቸዋል። ተንታኞቹ የዋሃንን ካላቀሱና ሙሾ ከሻሙ በሁዋላ ” ላይክና ሼር እንዳይረሳ፣ የአገልግሎታችን በሱፐር ስቲክ፣ በፔይፓል…” ብለው ያሳርጋሉ። ለፍቶ አዳሪዎች መሃለቃቸውን ይረጫሉ። ሳያስቡት ሌሎች እንዲሰቀሉ ያዋጣሉ …. ያበደው “በሰለጠነ አገር የሚኖሩ ገገማዎች” ይላቸዋል። ቦሰና ” የተቸከሉ” ስትል ትወቅሳቸዋለች። “ደግነቱ መቶ ሃያ ሚሊዮን ህዝብ ያለው አገር ቤት በመሆኑ ትጽናናለች!!
የምርት መጨመር ዜና ብቻ ሳይሆን በተግባር የታየ ነው። አፋርና ሶማሌ ክልል ሳይቀር እህል እያፈሱ ነው። ምርቱ ለምን ገበያውን አያወርደውም? ምርት ከበዛ ለምን አቅርቦቱ አይንበሸበሽም… የቦሰና ጥያቄ ነው። “ሌብነት በየፈርጁ” ሴራ አገሪቱን ወሯታል። ገበሬ ምርቱን እንዳይሸጥ ታጣቂዎች ይከለክላሉ። ለገበሬ ማዳበሪያ እንዳይደርስ “ነጻ አውጪዎች” እንቅፋት ይሆናሉ። ሲያሻቸውም ዘርፈው ይሸጣሉ። ሲፈልጉም ያቃጥሉታል። ጤና ጣቢያና ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤቶችና አገልግሎት መስጫዎችን ያወዳማሉ። ተንታኞች ይህን የመጀመሪያው ቀን “ሰበር ዜና” ብለው በድል ኦርኬስትራ በማጀብ “ውሮ ወሻባዬ” ይዘፍኑበታል። ላይክና ሼር፣ “ለጀግኖቻችን ጎ ፈንድ ሚ” አዝማቾች ይለቀቃሉ። የዋሃን ኪሳቸውን ያወልቃሉ። የስልጡን አገር “ሸዋዬዎች”!!
ከራርመው “እህል ተወደደ” የሚል ትንተና በደቦ ያዘንባሉ። መድሃኒት የለም። እከሌ ከሚባል ወረዳ ነብሰጡር በህክምና እጦት ሞተች፣ መድሃኒት ጠፋ … የሚል ሟርት ያሰማሉ። ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ከልክለው “አይ ይህ መንግስት” ብለው ይከሳሉ። በዚህ አሟሙቀው “የቁም ሞት ሞተናል” የሚል ሃዘን ያውጃሉ። ህዝብ እንዲያምጽ ይጣራሉ። የሚወጣውን አዘጋጅተው የሚገባውን በውል ሳያሳዩ “ግፋ በለው” ይላሉ። ገፍተው ማንን ሊጎትቱ ይሆን? የማይጠይቁ ኪሳቸውን ገልብጠው አብረው ይገፋሉ። አብረው ሲገፉ ውለው ያድራሉ። ምስኪኖች በገፊዎች ሳቢያ ይቆላሉ!! ለማይታወቁ ሃይሎች ሲሳይ ምስኪን እናቶች ሃዘን ለብሰው፣ ማቅ ወርሷቸው ጦሪና ቀባሪ … ቤቱ ይቁጠረው።
“ህዝብ እያስቸረሳችሁ እናንተ እዚህ ቁርጥ ትበላላችሁ። አፈር ብሉ። መርዝ ይሁንባችሁ” ብለው ሁለት ጠና ያሉ እናቶች ሜሪላንድ አንድ ሬስቶራንት ውስጥ ያገኙዋቸውን ተንታኞች እንዴት እንደወረዱባቸው ያበደው አስታወሰ። እናቶቹ እንደ ነበር በጥፍራቸው ዘልዝለው ቢበሏቸው ምንኛ ደስ ባላቸው ነበር። ተለምነው ተገፍተው ወጡ …. “ትግሉ እዚህ ደርሷል”
“ትግሉ እዚህ ደርሷል። ለትግሉ ማበብ ሲባል ሙሽሮች ተቆልፎባቸው ከነሙሉ ሰርገኞች በቦንብ አልቀዋል። እሳት ተለቆባቸው አረዋል። አመድ ሆነዋል” የሚለው ዜና ያበደው ጭንቅላት ውስጥ ይጮሃል። “ምን የሚሉት ትግል ነው?” ማንም ያድርገው ማንም ሰርገኞች ላይ በላያቸው ላይ በር ቆልፎ በቦንብ ማቃጠል በምን ዓይነት የፖለቲካ ድል ይወራረዳል? ይህን ትግል ነው ” ትግሉ እዚህ ደርሷል” የሚሉን።
በዚህ ትግል ብልጽግና “ዋይ ዋይ” እንደሚል እየተነገረን ነው። የትግሉ የበላዮች ሙሽራ ቢቃተል፣ ሰው ቢሰቀል፣ ምን ገዷቸው? ላለፉት ስድስት ዓመታት ምስኪኖችን እየነዱ ያስጨፈጨፉ ምን ሆኑ? ትህነግ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ምስኪኖችን አስበልታ ምን ተባለች? ጃዌ ምን ሆነ? ጦርነቱን ተከትለው ትግራይ ገብተው በህይወት የቆመሩና የዘረፉ ምን ሆኑ? አዲስ አበባ ቁጭ ብለው ዶላር የሚያጥቡ ማን ነካቸው? ምንጩ የማይታወቅ ፎቅ የደረደሩ ደረታቸውን እንደነፉ ነው።
ጎበዝ ቦሰና ገብቷታል። ዝርፊያውና ሃብት ማካባቱ የተባባሰው በአቶ ሃይለማሪያም ዘመንና በለውጡ ስድስት አመታት ነው ትላለች። የአቶ ሃይለማሪያምንና የአቶ አብይን ዘመን ስታሰላው አስር ዓመት ነው። ምንጩ የማይታወቅና ማስረጃ የማይቀርበበትን ሃብት ሊስለቅጥ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ደግሞ የሚሰራው ወደ ሁዋላ አስር ዓመታትን ሄዶ ነው። እና ቦሰና ይህን ብታሰላ ምን ይገርማል? ቦሰና የቤቱ ተንታኝ ሆናለች። ትተነትናለች። ቦሰና ትንተናዋን ማዞርም ትችላለች። እጥፍ ስትል ሌላ ናት።
ሙድ ተቀየረ። አሁን ጊዜው የቤት ውስጥ የግል ጨዋታ ነው። የቤት ውስጥ ትግላችን አሸናፊና ተሸናፊ የለውም። በስምምነት፣ በመጠባበቅ የሚደረግ መጋመድ ነው። “አከሲ” ካለች ግን እጅ መስጠት ነው። ቦሰና ነብስ ነገር ናት። “ትግሉ እዚህ ደርሷል” ለሚሉ ልቡና ይስጥልን። ብልጽግና ብዙ ጣጣ ስላለበት በቸዋ ፖለቲካ መበለት እየተቻለ ጨቅላ መብላት ትግል አይደለም። አሸናፊም አያደርግም። ብልጽግናን ” ዋይ ዋይ” የሚያሰኙት ድክመቶችና እጸጾች እልፍ ናቸው። አሁን መሸ። ሰላም ሁኑ። ቸር ያሰማን። የሚቀመስ ያላችሁ ምሳ ቋጥሩ!!