“ የተወሰኑ ሺህ የማይሞሉ ነጋዴዎችን ለመጠበቅ ስንል በሀገር በቀል ነጋዴ ስም፤ ሚሊዮኖችን የጎዳ የንግድ ስርዓት ይዘን መቀጠል የለብንም” – ዶ/ር እዮብ ተካልኝ
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተከልለው የነበሩ የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላ እና የችርቻሮ የንግድ ዘርፎችን፤ አቅሙ ላላቸው የውጭ ባለሃብቶች እንዲከፈቱ የሚያስችል መመሪያ ባለፈው መጋቢት ወር አውጥቷል። መንግስት የንግድ ስርዓቱን ለገበያ ክፍት የማድረግ አቅጣጫ መያዙ፤ “በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው” ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ዛሬ በፓርላማ በነበረ ሰብሰባ ላይ ተናግረዋል።
ዶ/ር እዮብ ይህን ያሉት በ2017 የፌደራል መንግስት በጀት ላይ ለመወያየት፤ የፓርላማው የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጠራው ስብሰባ ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው። ሚኒስትር ዲኤታው በዚሁ ማብራሪያቸው የኢትዮጵያ መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት እና ከሀገር ውስጥ የሚሰበስበውን ገቢ ለማሳደግ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን ዘርዝረዋል።
“የንግድ ስርዓታችን ይዞት የሚመጣው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እያየን ነው። ይሄንን ማስቀጠል የለብንም” ሲሉ የተደመጡት ዶ/ር እዮብ፤ ይህን ችግር ለመፍታት መንግስት በመፍትሔነት ያስቀመጠው ውድድር እንዲኖር ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል። “ልክ በቴሌኮም ዘርፍ ውድድር በመደረጉ ምክንያት ያየናቸው ወሳኝ ለውጦች፤ በንግድ ስርዓት ውስጥም ማካተት አለብን” ሲሉም ተደምጠዋል።
“የተወሰኑ ሺህ የማይሞሉ ነጋዴዎችን ለመጠበቅ ስንል፤ በሀገር በቀል ነጋዴ ስም ሚሊዮኖችን የጎዳ የንግድ ስርዓት ይዘን መቀጠል የለብንም። የንግድ ስርዓቱ ለውድድር ክፍት መሆን አለበት። ጎረቤት ሀገር ያለ አንድ ዕቃ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ ዕቃ የበለጠ የሚወደድበት ምንም ምክንያት የለም” ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው ጠንከር ያለ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ የዛሬ ሶስት ወር ገደማ ባወጣው አዲስ መመሪያ መሰረት፤ ማንኛውም የውጭ ባለሃብት ከዚህ ቀደም ለሀገር ውስጥ ባለሃብት በተከለሉ “የችርቻሮ ንግድ ኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት ይችላል። ይኸው መመሪያ፤ ከማዳበሪያ እና ነዳጅ ገቢ ንግድ በስተቀር “ማንኛውም የውጭ ባለሀብት ለሀገር ውስጥ ባለሃብት በተከለሉ በሁሉም የገቢ ንግድ ኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት እንደሚችል” ደንግጓል።
(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)