የቀብድ ትርጉም እና ዓላማ
ከብላክስ ሎው ዲክሽነሪ መረዳት እንደሚቻለው የቀብድ ክፍያ ማለት ውል መደረጉን ለማረጋገጥ ገዥ ለሻጭ የሚሰጠው ገንዘብ ወይም ዋጋ ያለው ዕቃ ማለት ነው ብሎ ይተረጉመዋል፡፡ በኢትዮጵያ ቀብድ ከጥንት ጀምሮ ህብረተሰቡ ሲጠቀምበት የነበረ ሲሆን በሀገራችንም የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 1883 የቀብድ ትርጉም ሳያስቀምጥ አንድ ወገን ለአንዱ ወገን ቀብድ መስጠቱ በማያከራክር ሁኔታ ውል መደረጉን ያረጋግጣል በማለት ይገልፃል፡፡ ይሁን እንጂ በፍትሐብሔር ህግ ስለውል አፈፃፀም ድንጋጌዎች መሰረት በፅሁፍ ሊደረጉ እና በፍ/ቤት መዝገብ ወይም ውል የማዋዋል ስልጣን በተሰጠው አካል ፊት መሆን የሚገባቸው ውሎች በፅሁፍ ሳይረደጉ ቀርተው ቀብድ መሰጠቱ ብቻ ውል መፈፀሙ አያረጋግጥም፡፡
በሌላ አባባል የቀብድ ክፍያ ማለት በተዋዋይ ወገኖች መካከል ውል መኖሩ እና ተዋዋይ ወገኖች በውሉ ለመገደድ ወይም ውሉን እስከ መጨረሻው ተከታትሎ ለመጨረስ ያላቸውን ፍላጎት ለማሳየት ሲባል በመያዣነት ቀብድ ሰጪ ለቀብድ ተቀባይ የሚሰጠው ክፍያ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ክፍያ በተዋዋይ ወገኖች መካከል የሽያጭ ወይም የአገልግሎት የውል ስምምነት መኖሩን፤ በቀጣይም ሁለቱም ተዋዋይ ወገኖች በውል ስምምነቱ ለመገደድ ያላቸውን ፍላጎት የሚገልፁበት ነው፡፡ የሚከፈለውም የክፍያ መጠን እንደ የአከባቢው ሁኔታ ወይም እንደስራው ዓይነት እና ስምምነት ሊለያይ ይችላል፡፡
የቀብድ ክፍያ ውጤት
በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 1884 ስር እንደተደነገገው ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በቀር ቀብድ ተቀባይ ውሉ ከተፈፀመ በኋላ የቀብዱን ገንዘብ መመለስ ወይም ውሉ ሲፈፀም ከጠቅላላው ክፍያ መቀነስ ያለበት መሆኑ ያስቀምጣል፡፡ ይህም ለተዋዋይ ወገኖች ምርጫ የተወወ ቢሆንም ሌላ ስምምነት ካላደረጉ ውሉ ሲፈፀም የቀብድ ክፍያ እንደ ቅደመ ክፍያ ይቆጠራል ወይም ቀብድ ተቀባይ ለቀብድ ሰጪ ይመልሳል፡፡
ቀብድ ሰጨና ቀብድ ተቀባይ ውሉን ለመተው ቢፈልጉ በቀብድ ክፍያው ላይ የሚኖረው ውጤት የተለያየ መሆኑም ከፍትሀ ብሄር ህጉ ድንጋጌ መገንዘብ እንችላለን፡፡ በፍ/ህግ ቁ. 1885 ላይ እንደተቀመጠው ሌላ ስምምነት ከሌለ በስተቀር ቀብድ ሰጪ የሰጠውን የቀብድ ክፍያ በመልቀቅ ውሉ መተው ይችላል፡፡ ይህ ማለት ቀብድ ሰጪ ውሉን የሚያፈርስ ወይም የሚተው ከሆነ የከፈለውን የቀብድ ገንዘብ ከቀብድ ተቀባይ ላይ ላለመቀበል መወሰን ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል ቀብድ ተቀባይ የተቀበለውን ቀብድ አጠፌታ በመክፈል ውሉን መተው ወይም ማፍረስ ይችላል፡፡ ከዚህም ቀብድ ሰጪና ቀብድ ተቀባይ ውሉን ሲያፈርሱ የሚከፈለው የቀብድ ክፍያ መጠን አንድ አይነት አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ቀብድ ተቀባይ የቀብዱን እጥፍ እንዲከፈል ህጉ አስገዳጅ ያደረገው ውሉ ባለመፈፀሙ ምክንያት በሌላኛው ወገን (በቀብድ ሰጪ) ላይ ሊደረስ የሚችለውን ጉዳት እንደማካካሻ እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡
የቀብድ ክፍያ (earnest) እና የቅድመ ክፍያ (advance payment) ልዩነት
በተዋዋይ ወገኖች ውል የመፈፀም ሂደት ውስጥ ሌላው የሚነሳው ጉዳይ የቀብድ እና የቅድመ ክፍያ ልዩነት ሲሆን አንድ ክፍያ ቀብድ ከሆነ ከፋይ ውሉ ቀሪ ቢሆን የሚያስመልሰው የቀብዱን እጥፍ ሲሆን አንድ ክፍያ ቅድመ ክፍያ ከሆነ ግን ከፋይ አካል ገንዘቡን የሚያስመልሰው በፍ/ቤት ክስ በመመስረት ውሉ ባለመፈፀሙ የደረሰበትን ኪሳራ በማስረዳት እና ያወጣውን ወጪ በመጠየቅ ነው፡፡ እዚህ ጋ መረዳት እንደምንችለው ቀብድ በሚሆንበት ወቅት ጉዳት መኖሩን ሳያመለክት ቀብድ ሰጪ ውሉን ካፈረሰው ሰው ላይ የተከፈለውን ገንዘብ እጥፍ መቀበል እንደሚችልና ቅድመ ክፍያ ከሆነ ግን ከፋይ የሚቀበለው የተከፈለውን ገንዘብ ያክል ብቻ ሆኖ ተጨማሪ ክፍያዎችን ለመቀበል ጉዳት መኖሩን ማመልከት እንዳለበት ነው፡፡ ይሁንና በአብዛህኛው ማህበረሰብ የሚረዳው መጀመሪያ የሚከፈለው ቅድመ ክፍያ ቀብድ እንደሆነ እና ውሉን ለመፈፀም ተዋዋይ ወገኖች ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩበት እንደሆነ ነው፡፡ ቀብድ የተቀበለ ሰው ውሉን ለመፈፀው ቀብድ ካልተቀበለ ሰው ይልቅ የሚተጋ/ውሉን ለመፈፀም የሚታትር/ ሲሆን ቀብድ የከፈለ ሰውም ውሉን ላለማፍረስ እንደማሰሪያ የሚይዘው ይሆናል፡፡ ውሉን ለማፍረስ ሲወስን ገንዘቡን ለመተው አምኖበታል ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ቀብድ ተቀባይ የተቀበለውን ቀብድ እንዲመልስ አይገደድም፡፡
በቅድመ ክፍያ ወቅት ግን ይህ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡ በመሆኑም ለዚሁ ውል ያወጣቸው ወጪዎች ከሌሉ በቀር የተቀበለው ቅድመ ክፍያ እንዲመልስ ይገደዳል ማለት ነው፡፡
ለዚህም ነው አብዛኛውን ጊዜ ቀብድ ሰጪ ውል ሲያፈርስ ገንዘቡን ማስመለስ ሲፈልግ የሰጠሁት ቅድመ ክፍያ እንጂ ቀብድ አይደለም የሚሉት፡፡ የሁለቱን የክፍያ አይነቶች ጥቅምበምንመለከትበት ወቅት ቀብድ የፍርድ ቤት እንግልትና ወጪ የሚቀንስ እና በአብዛኛው በእርግጠኝነት የሚገኝ ስለመሆኑ እንረዳለን፡፡ የቅድመ ክፍያ ገንዘብ የሚከፈለው በውሉ ለመገደድ ያለን ፍላጐት ለመግለፅ ሳይሆን ወደ ፊት የሚመጣውን የእዳ መጠን ለመቀነስ ታስቦ የሚከፈል ክፍያ ነው፡፡ ቃብድ ግን በውሉ ለመታሰር እና ውል ስለመኖሩም ለማስረዳት በማሰብ የሚደረግ የውል አይነት ነው፡፡
ፍትህ ሚኒስቴር በንቃተ ህግ፣ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት