የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አማካሪን ጨምሮ 8 ተከሳሾች ከይዞታ ምዝበራ ጋር ተያይዞ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ።
1ሺህ 800 ካሬ ሜትር ይዞታን በተለያዩ መጠኖች ግለሰቦች ያለአግባብ እንዲወስዱ በማድረግና በየደረጃው ይዞታውን ተቀብሎ በመሸጥ ከ80 ሚሊየን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ተብለው በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት የቀድሞ የከተማ ከንቲባ አማካሪን ጨምሮ 8 ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።
ሌሎች በክስ መዝገቡ ተካተትው በሌሉበት ጉዳያቸው የታዩ 15 ተከሳሾች በሚመለከት የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ብይኑን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና የወንጀል ችሎት በክስ መዝገቡ የተካተተ አንድን ተከሳሽም በቂ ማስረጃ እንዳልቀረበበት ጠቅሶ ከቀረበበት ክስ ነጻ ብሎታል።
እንዲከላከሉ ብይን ከተሰጠባቸው ተከሳሾች መካከል የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽ/ቤት የካሳ ግምትና ምትክ ባለሙያ አፈወርቅ ሀይሌ ገ/ስላሴ፣የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አማካሪ ቶሎሳ ተስፋዬ እና የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ የሰው ኃይል ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አበበ ደጋ እና የኮንስትራክሽን ሰራተኛ የሆነው ኢዶሳ ነገራ ስንኩሬ ይገኙበታል።
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ11 የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞችና 13 ግለሰቦች በአጠቃላይ በ24 ተጠርጣሪዎች ላይ የወንጀል የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በልዩ የሙስና ወንጀል ተካፋይነት በመሆን ስልጣንን አላግባብ መገልገል የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል።
በዚህም በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1(ሀ) ፣ንዑስ ቁጥር 3 እና አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና (ለ) እንዲሁም ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተጠቀሰውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚል ክስ ነው የቀረበባቸው።
በክሱ ላይ ከ1ኛ እስከ 9ኛ እንዲሁም 23ኛ እና 24ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሱት ተከሳሾች የመንግስት የስራ ኃላፊነት ላይ ተመድበው ሲሰሩ በልዩ ወንጀል አድራጊነት የሙስና ወንጀል ተካፋይ ከሆኑት ከ10ኛ እስከ 22ኛ ከተጠቀሱት በግል ስራ ከሚተዳደሩት ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር በልማት ተነሺ ስም ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም እስከ ህዳር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ባሉት የተለያዩ ቀናት ውስጥ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 እና በልደታ ወረዳ 3 በይዞታ ክልል ውስጥ በአርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጆች በሚል ምክንያት ብቻ ተገቢ ያልሆነ የካሳና ምትክ በተለያዩ መጠኖች አጠቃላይ 1 ሺህ 800 ካሬ ሜትር ይዞታን በሕገ ወጥ መንገድ ግለሰቦች እንዲወሰድ መደረጉ በክሱ ተጠቅሷል።
ሌሎቹ ተከሳሾች ላይም ቦታውን ወስዶ በመሸጥ ለራሳቸው የማይገባ ብልፅግና በማግኘትና በመንግስት ላይም የመሬቱ ሊዝ ዋጋ የሆነውን እና ካሳ የተከፈለውን 80 ሚሊየን 755 ሺህ 508 ብር ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በልዩ የሙስና ወንጅል ተካፋይ በመሆን የስልጣን አላግባብ መገልገል የሚል የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ነበር የቀረበው።
በዚህ መልኩ ዝርዝር ክስ ከቀረበባቸው ተከሳሾች መካከል የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽ/ቤት የካሳ ግምትና ምትክ ባለሙያ አፈወርቅ ሀይሌ ገ/ስላሴ፣የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አማካሪ ቶሎሳ ተስፋዬ እና የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ የሰው ኃይል ዳይሬክቶሬት አበበ ደጋ እና የኮንስትራክሽን ሰራተኛ የሆነው ኢዶሳ ነገራ ስንኩሬ ጨምሮ 8 ተከሳሾች ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
እነዚህ ተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ ዝርዝር በንባብ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ የተደረጉ ሲሆን፤ከዚህም በኋላ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው በሰጡት የዕምነት ክህደት ቃል መነሻ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዳሉ ያላቸውን የሰው ምስክሮች አቅርቦ የምስክርነት ቃላቸውን አሰምቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም የምስክር ቃል መርምሮ ወንጀሉ መፈጸሙን መረጋገጡን በመጥቀስ 8 ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡
በተደጋጋሚ በመጥሪያና በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው ችሎት ያልቀረቡ 15 ተከሳሾችን በሚመለከት ጥፋተኛ ተብለዋል።
በሌላ በኩል በክስ መዝገቡ በሌለበት የተከሰሰው 21 ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሰ ተከሳሽን በሚመለከት በቀረበበት ክስ ላይ ማስረጃ እንዳልቀረበበት ተጠቅሶ ነጻ ተብሏል።
ፍርድ ቤቱ ተከላከሉ የተባሉ ተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ ለመጠባበቅ ወደ ሕዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም በማሸጋገር ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ – ፋና ብሮድካስት