የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኩን የፖሊሲ ተመን መወሰን፣ የሰነዶች ግብይት ጨረታ መጀመር፣ የአንድ ቀን የብድር እና የገንዘብ አገልግሎት ማስተዋወቅና የባንክ ለባንክ የገበያ ሥርዓት ማስተዋወቅን ያካተተ አዲስ የፖሊሲ ማዕቀፍ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።
አዲሱ ፖሊሲ የባንኩን አሠራር የሚያዘምን፣ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ጋር የተጣጣመ፣ ለፈጣን፣ ፍትሃዊ እና ሥራ ፈጣሪ የኢኮኖሚ ልማት የሚረዳም መሆኑን የባንኩ ገዢ ማሞ ምህረቱ ተናግረዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና ባንኩ ይፋ ያደረገው አዲሱ ፖሊሲ ወደ ዘመናዊ የባንክ አሠራር የሚያሸጋግር፣ ባንኮች የተረጋጋ አሠራር እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን ያመለክታሉ።
ባንኮች ሊኩዲቲ (የገንዘብ እጥረት) ችግር ስላለባቸው ያንን ለማስተካከል ያስችላልም ነው ያሉት። እንደ ክቡር ገለጻ፤ አንዳንድ ባንኮች የመንግሥት ድጋፍ ባይኖራቸው ኖሮ ከስረው ሊዘጉ ይችሉ ነበር። ነገር ግን ጥንቃቄ የተላበሰ፣ ሥርዓቱን የጠበቀ አሠራር በመኖሩ በኢትዮጵያ ባንኮች በመንግሥት ድጋፍ ጭምር ሊቀጥሉ ችለዋል።
ይፋ የሆነው አሠራር ከዚህ በፊትም ሊኖር ይገባ የነበረ፣ ባንኮች እርስ በእርስ እንዲበዳደሩ የሚያስችል አሠራር የፈጠረላቸው ነው።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርሄ ተስፋ (ዶ/ር) እንደሚሉትም፤ የባንክ ተመን የፖሊሲ አቋም ለመጠቆም፣ ሰፋ ያለ የገንዘብና የብድር ሁኔታዎች ላይ ተጽእኖ ለማድረግ ያግዛል።
ወለዶች ከፍ እያሉ በሄዱ ቁጥር አበዳሪዎች፣ ተበዳሪዎችና ባለሀብቶች ለውጦቹን በቅርበት መከታታል ይጠበቅባቸዋል። እያደገ ያለውን የገበያ ሁኔታ በመገንዘብ ስልቶቻቸውን ማስተካከል ይኖርባቸዋልም ይላሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ክቡር፤ የወለድ አከፋፈል ለባንኮች ዝቅ ቢልም ባንኮች በ17፣ በ18 እና በ19 በመቶ ወለድ ምጣኔ ማበደራቸው አይቀርም፤ በኢትዮጵያ ግሽበቱን ዝቅ ማድረግ እስካልተቻለ ተበድሮ ሥራ ለመሥራት የሚፈልገው ባለሀብት ለመሥራት ያዳግተዋል ይላሉ።
በውሳኔው የሀገር ውስጥ ባንኮች ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚሉት ባለሙያው፤ ገንዘብ ባነሳቸው ቁጥር ግልጽ በሆነ መንገድ የሚሄዱበት፣ በጨረታ ተወዳድረውም ገንዘብ የሚያገኙበት መንገድ በአዲሱ ፖሊሲ እንደተመቻቸም ነው የሚጠቅሱት።
ሂደቱ የዘመናዊ ባንኮች አካሄድ በመሆኑ ዓለምአቀፍ ባንኮች ሀገር ውስጥ ገብተው በሚያጠኑበት ጊዜ እነዚህ አሠራሮች መኖራቸው የበለጠ ዋስትና እንደሚሰጣቸውም ክቡር ይናገራሉ።
የባንኩ ገዢ አቶ ማሞ፤ ከውሳኔዎቹ መካከል ለባንኮች የአንድ ቀን የብድርና የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎቶቹ ባንኮች በአንድ ቀን ውስጥ የገንዘብ አቋማቸውን ለማስተካከል እንዲረዳቸው ታሳቢ የተደረገ መሆኑን ይናገራሉ።
ባንኮች እርስ በእርስ የሚበዳደሩበትን የተነቃቃ የገንዘብ ገበያ ለመመስረት የሚያስችል የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሥርዓት በቅርቡ ለመዘርጋት ዝግጅት ያጠናቀቀበት ውሳኔም ሲተገበር ትርፍ ገንዘብ ያላቸው የገንዘብ እጥረት ላጋጠማቸው ባንኮች ማበደር እንደሚችሉም አቶ ማሞ ይናገራሉ።
እርስ በርስ ብድር መውሰድ በባንኮች የተለመደ አሠራር ነው። በተጀመረው አሠራር ባንኮች ለአንድ ቀን ከሌላ ባንክ ይበደራሉ ወይም ደግሞ ራሱ ብሔራዊ ባንክ ያበድራቸዋል።
ከእዛ በላይ ደግሞ የተወሰኑ ቀናት የሚያስፈልግ ከሆነም እርስ በእርስ ብድር የሚወስዱበት ሥርዓት ክፍት ሆኗል። ይህ ጅማሮም የባንክን አሠራር ወደ ዘመናዊነት ይቀይረዋል ይላሉ ክቡር ።
ብሔራዊ ባንክ መጪውን ጊዜ የሚመጥን የማስተዳደር ከፍተኛ ክህሎት ሊያሳድግ ይገባዋል የሚሉት ቆስጠንጢኒዎስ (ዶ/ር)፤ በዓለም የፋይናንስ ሥርዓት በየሰከንዱ ከትሪሊዮን ዶላር በላይ በኢንተርኔት ይሸጋገራል። ይህንን ተከትሎም ነው የሀገር ኢኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው።
ሁሉም ማዕከላዊ ባንኮች ተጠቃሚ እንደመሆናቸው ተጎጂም ሊሆኑ ስለሚችሉ የአስተዳደር ክህሎታቸውን ማሳደግ አለባቸው ፤ማሻሻያዎቹም ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ ለመጀመሪያ ጊዜ 15 በመቶ ተደርጓል፤ ቀላል ማበደሪያ አይደለም፣ ከፍተኛ ነው የሚሉት ክቡር፤ ባንኮች የሚያበድሩት ከእዛ በላይ ነው ቀንሰን እናበድር የሚል እሳቤን ይዟል፣ ነገር ግን ባንኮች በሚያበድሩበት ጊዜም ከተበዳሪው ወለድ ይጠይቃሉ።
ዛሬ አንድ ድርጅት ሥራ ከፍቶ 20 እና 30 በመቶ አትርፎ 15 በመቶ ለባንክ እዳውን ከፍሎ ያዋጣኛል ብሎ ለመቀጠል ያስቸግራል። ሆኖም ግን እንደእኛ አይነት ሀገር ላይ ይደረጋል። አፍሪካ ውስጥም ወለዳቸው በጣም ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት ግሽበቱ ከፍተኛ በመሆኑ ነው። ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ ነው ብለን ልንገምት እንችላለን።
የብሔራዊ ባንኩ ፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ ለመጀመሪያ ጊዜ 15 በመቶ ይሆናል። ተመኑ አሁን የሚታዩ ማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎችንና በከፍተኛ ደረጃ እየወረደ የመጣውን የባንክ ብድር እድገት ግምት ውስጥ ያስገባ ነው።
ባንኮች በውድድር ላይ ተመሥርተው ለደንበኞቻቸው በሚሰጡት ብድር ላይ የሚያስከፍሉትን የወለድ መጠን በራሳቸው መወሰናቸውን እንደሚቀጥሉ፣ ባንኮች በቁጠባ ገንዘብ ላይ የሚከፍሉት ዝቅተኛ የሰባት በመቶ ወለድ በፖሊሲ ተመኑ ምክንያት ለውጥ እንደማይደረግበትም አቶ ማሞ ያመለክታሉ።
ከገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ጨረታዎችን በየሁለት ሳምንቱ እንዲካሄድ የተደረሰው ውሳኔም ከዚህ በፊት ያልነበረ፣ ባንኮች በተለያየ መንገድ የሚያጋጥማቸው የገንዘብ እጥረት ለመሸፈን የሚረዳቸው አሠራር መሆኑን ክቡር ይጠቁማሉ።
አቶ ማሞ ለባንኮቹ ተጨማሪ ገንዘብ ለማቅረብ የሰነዶች ግብይትን ይጠቀማልም ብለዋል።
ቻይና በኢኮኖሚ በአንዴ የተመነደገችው እ.አ.አ በ2001 የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ከሆነች በኋላ የውጭ ባንኮችን አስገብታ ነው። የሀገር ውስጥ ባንኮች እንዲያድጉ የውጭ ባንኮች ቅርንጫፍ መክፈት እንዳይችሉ፣ ከሕዝቡ የቁጠባ ሂሳብ መሰብሰብም እንዳይፈቀድላቸው ገድባ እንደነበር ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ያነሳሉ።
የውጭ ባንኮች ሲመጡ ገንዘብ፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ፣ ከፍተኛ የሥራ ልምድ፣ ዘመኑ የደረሰበትን የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ይዘው ይመጣሉ። በፖሊሲው የውጭ ባንኮች የተወሰነ ሼር ከሀገር ውስጥ ባንኮች እንዲገዙ ስለሚፈቅድ የሀገር ውስጥ ባንኮችም አብረው ያድጋሉ።
እንደቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ፖሊሲዎቹ በኢኮኖሚ አስተዳደር ላይ መተማመንን ይፈጥራሉ። ብሔራዊ ባንክ ካፒታሉን ከፍ እያደረገ መሄዱ አይቀርም። የሀገር ውስጥ ባንኮች አሁን ሰብሰብ ማለት ይጠበቅባቸዋል።
የትላልቅ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ለባለሀብቶች መተማመንን ይፈጥራሉ። በሀገር ውስጥ ሰላምና የኢኮኖሚ አስተዳደር ከሰፈነ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።
የሀገር ወስጥ ባንኮችም በከፍተኛ ደረጃ ሊያድጉ የሚችልበት አጋጣሚ ስለሚፈጥር ባንኮቹ በመደራጀት ዓለም አቀፍ ባንክ ደረጃን በማሟላት መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።
እያንዳንዱ የባንክ ሠራተኛ በዘፈቀደ መረጃ አይቶ ለሌላ አካል የሚያስተላልፍ ከሆነ ተአማኒነት ስለሚጠፋ ባንኮች ጠንካራ መታመንን መገንባት አለባቸው ነው ያሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)። ባለሙያዎቹ በማጠቃለያነት ርምጃው የሀገር ውስጥ ባንኮችን ተወዳዳሪ ያደርጋል፣ በኢትዮጵያ የባንክ አሠራር ቅልጥፍናን የተላበሰና የዘመነ እንዲሆን ያስችላል የሚለውን በጋራ ይስማሙበታል።
ዘላለም ግዛው addis zemen