“በጸጥታ እና ተያያዥ ችግሮች ፈተና መውሰድ ያልቻሉ ተማሪዎችን የማካካሻ ትምህርት በመስጠት ፈተናውን እንዲወስዱ ይደረጋል” ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
የአሁኑ የፈተና አሰጣጥ ሂደት የተማሪዎችን የዕውቀት ደረጃ በተገቢው መንገድ የሚለካ መኾኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከሕዝብ እንደራሴዎች ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የመውደቅ ምጣኔ መጨመር፤ የትምህርት ቤቶች የማሻሻያ ሥራዎች እና ሌሎችንም ጥያቄዎች የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የፈተና አሰጣጡ የተማሪዎችን የዕውቀት ደረጃ በተገቢው መንገድ የሚለካ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት የነበረው የፈተና አሰጣጥ ሂደት ኩረጃ የሚስተዋልበት እንደ ነበር የተናገሩት ሚኒስትሩ የአሁኑ የፈተና አሰጣጥ ኩረጃን ያስቀረ መኾኑን ጠቁመዋል።
የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ መቀየር ተማሪዎች በአግባቡ ዝግጅት በማድረግ ለዕውቀት እንዲተጉ የሚያደረግ መኾኑንም ተናግረዋል።
በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና የኦንላይን ፈተና ተጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ መኾኑን ያነሱት ፕሮፌሰሩ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት እና የኢንተርኔት መቆራረጥ ችግርን በመፍታት የኦንላይን ፈተናው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በጸጥታ እና ተያያዥ ችግሮች ፈተና መውሰድ ያልቻሉ ተማሪዎችን የማካካሻ ትምህርት በመስጠት ከተቻለ በ2016 ካልኾነም በቀጣዩ የትምህርት ዘመን የሚሰጥ መኾኑንም አስታውቀዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኅብረተሰቡ በዓይነት በገንዘብ እና በጉልበት ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ለትምህርት ቤቶች ማሻሻያ ሥራዎች ድጋፍ ማድረጉንም ጠቅሰዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በበጀት ዓመቱ 5 ሺህ 873 አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል። ከ14 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ዕድሳት እና ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል ነው የተባለው።
በቀጣይም ኅብረተሰቡን በማስተባበር የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።
(አሚኮ)