በወላይታ ዞን አስተዳደር በሙስናና ብልሹ አሰራር የተጠረጠሩ ስምንት የሥራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የወላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ምክትል ኮማንደር ንጋቱ ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከልና ተጠርጣሪዎችን ለህግ ለማቅረብ ሰፊ ስራ ሲከናወን ቆይቷል።
የሥራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ስልጣናቸውን በመጠቀም የመንግሥትና የህዝብ ሀብት ላይ የሙስናና የመሬት ምዝበራ ድርጊቶችን ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅና የቀበሌ ስራ አስኬያጆችን ጨምሮ ሰባት የስራ ሃላፊዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የወላይታ ዞን ከተማ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊም በወንጀሉ ተጠርጥረው በዛሬው ዕለት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ምክትል ኮማንደር ንጋቱ ገልጸዋል።
ተጠሪጣሪዎች 11 ህገ ወጥ ማህበራትን በማደራጀትና ለአራቱ ማህበራት በህገ ወጥ መንገድ 6 ሺህ 200 ካሬ መሬት በማስተላለፍ የተጠረጠሩበት ወንጀል ድርጊት መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጠርጣሪዎቹ ላይ የተጀመረው ምርመራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁት ምክትል ኮማንደሩ፤ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት እያካሄደ ያለውን ትብብር እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
OBN