እነዚህ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ፕሮፌሰር እና የፖለቲካ ሳይንቲስት እሌኒ ሳንቲም ዘለቀ ቃላት ናቸው። ፕሮፌሰር እሌኒ ይህን መልዕክት በማኅበራዊ ትስስር ገጿ ካስተላለፈች አንድ ሳምንት በኋላ ኒው ዮርክ በሚገኘው ኢስት ኢንድ ሆስፒስ ውስጥ ሕይወቷ አልፏል።
‘ተጨዋች፣ ሳቂታ፣ ብልህ፣ ደግ፣ ጽኑ፣ አብዮተኛ…’ የመሳሰሉት ቅጽሎች ፕሮፌሰር እሌኒን ለመግለጽ በወዳጆቿ ይዘወተራሉ። የፕሮፌሰር እሌኒ ወዳጆች የሚጠሯት ‘ሳንቲም’ እያሉ ነው። እኛም ሳንቲም እያልን እናዝግም።
ሳንቲምን በቅርበት የሚያውቃት ሰው ከላይ ያሉትን ቅጽሎች ከሰው መስማት አያሻውም። ሳንቲም ተጫዋች ናት። ‘ምድርን ተሰናብታለች’ ካልን ዘንዳ ‘ተጫዋች ነበረች’ ማለቱ ሳይሻል አይቀርም።
ነገር ግን ወዳጆቿ ስለእሷ ሲያወሩ ኃላፊ ጊዜን መጠቀምን አይመርጡም። መቼስ . . .
ሳንቲም መምህር ናት፣ ተማሪዎቿ “ቀኖናዊ (dogmatic) የሆነች አስተማሪ አልነበረችም” ሲሉ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
ሳንቲም ለተማሪዎቿ በጥያቄ እና መልስ ጓደኝነትን ፈቅዳለች።
ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል ነጻነት ገብረሚካኤል እና ሠራዊት በቀለ ይጠቀሳሉ። ሳንቲም፣ ነጻነት እና ሠራዊትን ከ16 ዓመታት በፊት አስተምራቸዋለች። እነሱ የማስተርስ ተማሪዎች ሁነው እሷ ደግሞ ፒ.ኤች. ዲ ጥናቷን እየሠራች።

“አስተማሪነቷ ሰብዕናዋ ጋር በጣም የተያያዘ ይመስለኛል” የምትለው ነጻነት፤ “ከእሷ ያገኘነው ትልቁ ነገር ጠያቂ መሆንን ነው። ተማሪ መሆን ማለት ጠያቂ መሆን ማለት እንደሆነ። የእሷን ምሁርነት የምረዳው በጥያቄ ዙሪያ ነው” ትላለች።
ነጻነት እና ሠራዊት የቀድሞ የኔታቸው የተማሪ እና መምህርን ግንኙነት እንደገና እንዲፈትሹ ያረገቻቸው መሆኗን ይናገራሉ። ሁለቱም የማይረሱት አንድ ገጠመኝ አላቸው፤ ከትምህርት ክፍለ ጊዜው መጠናቀቅ በኋላ ሳንቲም ሁሉንም ተማሪዎቿን [13 ተማሪዎች] ሬስቶራንት ይዛቸው ትሄዳለች።
ቁም ነገሩ ሬስቶራንት መሄዱ ብቻ አልነበረም ተማሪ እና የአስተማሪን የሥልጣን ተዋረድ እንደገና መፈተሹ እንጂ። ከ16 ዓመታት በፊት መምህር እና ተማሪዎች ፒዛቸውን በሚንት ሻይ እያጣጣሙ ምሁራዊ ውይይቶችን አድርገዋል፣ ተሟግተዋል የማይረሱትንም ትዝታ ሰንቀዋል።
ሳንቲም መዋኘት ትወዳለች። ይህን የኬንያ ላሙ ደሴቶች ይመሰክራሉ። ዳንስ እና ሙዚቃም ወዳጅ ናት። ዲጄም ነበረች። ለወዳጆቿ ለጓደኞቿና ለሥራ ባልደረቦቿ ምግብ ማብሰል እና መጋበዝም ትወድ ነበር። ሳንቲም ዳንስ እና ሙዚቃ ውስጥም ምሁራዊ ፕሮጀክቷን ታንጸባርቃለች።
ሠራዊት በቀለ “[ሳንቲም] ዝም ብላ ስታወራም ስትጫወትም፤ የምታወራው ለምሳሌ የሳቅ የጨዋታ የቀለድ የማኅበራዊ ሕይወት ነገር ይሆንና ወደ ምሁራዊ ነገሩ ትሄዳለች፤ ሁሌ ይሄ አቅም አላት፤ ሳቅ ጨዋታውን ረቂቅ ወደ ሆነ ምሁራዊ ንግግር የመሳብ የሚገርም መንገድ አላት። እሷ ስታደርገው ከባድ አይደለም፤ ልብ ላትለው ሁላ ትችላለች። አጠገቧ ያለነው ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ ነው ከእሷ እየተማርን የምናልፈው። በሳቅ በጨዋታ።” ትላለች።
ሳንቲም ከአምስት ዓመት በፊት በጻፈችው መጽሐፍ የምስጋና ክፍል ላይ ሁለቱን ተማሪዎች በስም ጠቅሳ ታመሰግናቸዋለች። በአፍሪካ ቀንድ ስለ ሂሳዊ አስተሳሰብ እርስ በእስ እየተማማርን የምንደጋገፍ ቤተሰብ ሆነናል ትላለች።
በብዙዎች የምትወደደው እና የምትወደሰው ሳንቲም ሰኔ 28/2016 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች። ሳንቲም ሕይወትን አፍቃሪ ነበረች። እንዲሁ ብቻ የሚኖሩበትን ሕይወት ሳይሆን ሰው ያለበትን…ለዚያም ነው የሰው ልጅ ስቃይ ግድ የሚላት።
የሰው ልጅን ዋጋ በቅጡ የምትረዳ ነበረች። ሳንቲም እሴት ያለው፣ ደርዝ ያለው ሕይወት ኑራ አልፋለች። ማለፏ የሚጠበቅ ቢሆንም የወዳጆቿን ልብ የሰበረ እና ያሳዘነ ነበር።
ወዳጆቿ፣ ጓደኞቿ፣ ተማሪዎች እና ሥራዎቿ ስለ ፕሮፌሰር እሌኒ ሳንቲም ዘለቀ ምን ይነግሩናል? ሳንቲም ማን ናት?
ልጅነት ከጎንደር እስከ ጋያና

ከ53 ዓመታት በፊት ጎንደር፣ ኢትዮጵያ።
የዶ/ር ዘለቀ በቀለ ባለቤት ወይዘሮ እሌኒ እምሩ ሦስተኛ ልጃቸውን ለመውለድ ምጥ ላይ ሳሉ፤ አንድ የእጅ አመል ያለበት ሰው ከጥንዶቹ ቤት ሳንቲም ይዞ ሮጠ። ዶ/ር ዘለቀ ሌባውን ለመያዝ ሞከሩ ግን አልቻሉም።
ዶ/ር ዘለቀ ገንዘባቸውን ማስመለስ ባይችሉም፣ ባለቤታቸው ግን ሌላ ሳንቲም ሰጧቸው። ይህቺ ሳንቲም የዶ/ር ዘለቀ አራተኛ የወይዘሮ እሌኒ ደግሞ ሦስተኛ ልጅ የሆነች እሌኒ ሳንቲም ዘለቀ ናት።
ጎንደር የተወለደችው እሌኒ ሳንቲም ዘለቀ በጋያና፣ በባርቤዶስ እና በካናዳ ነው ያደገችው።
አባቷ ዶ/ር ዘለቀ ቀላል ሰው አልነበሩም። የጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅን በዲንነት በመምራት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ናቸው። በአሁኑ ሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ የመጀመሪያው ዘመናዊ ሆስፒታል እንዲቋቋም የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር።
ስማቸውን ያወረሷት እናቷ ወይዘሮ እሌኒ እምሩ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የአክስት ልጅ እና የአገር አስተዳዳሪ የነበሩት ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ልጅ ናቸው።
ሳንቲም የሁለት ዓመት ህጻን እያለች ከየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት አንድ ዓመት በፊት ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ ካናዳ ተጓዘች።
ዶ/ር ዘለቀ በካናዳ ለተወሰኑ ዓመታት ከኖሩ በኋላ የዓለም የጤና ድርጅትን ተቀላቅለው ወደ ጋያና ቀጥሎም ወደ ባርቤዶስ አቀኑ። ሳንቲም እስከ ሁለተኛ ደረጃ የተማረችው በካሪቢያን ደሴት በሚገኙት ሁለቱ አገራት ነው።
ሳንቲም በጋያና የነበራትን የልጅነት ጊዜ በቃለ መጠይቆቿ ደጋግማ ታነሳለች። ወዳጇ ነጻነት ገብረሚካኤል “ጋያናን ከኢትዮጵያ እኩል ነበር የምታነሳው፤ ሁላችንም ከጋያና እንደሆነች ነበር የምናውቀው” ትላለች።
በካሪቢያን ደሴቶች የነበሯት ዓመታት አስተሳሰቧን እንደቀረጹት በአንድ ቃለ ምልልሷ ላይ ጠቁማለች። ምሁራዊ አቅጣጫዋ መልክ የያዘው፤ የዓለም አቀፍ ንግድ እና የአትላንቲክ-ተሻጋሪ የባሪያ ንግድ ማዕከል በነበሩት የካሪቢያን አካባቢዎች የባርነት ሥርዓትን የተመለከቱ ውይይቶች እና ተዋስዖ (discourse) ሲካሄድ ነበር።

“በካሪቢያን አካባቢ ባለው እና ምናልባትም በኢትዮጵያ ወይም በምሥራቅ አፍሪካ በተመሳሳይ መልኩ የለም ብዬ በማስበው ኮስሞፖሊታኒዝም ነው” ትላለች።
በዚሁ ምክንያት “በካሪቢያን አካባቢ ያለው ፓን አፍሪካኒዝም ምናልባትም በኢትዮጵያ ካለው የፓን አፍሪካኒዝም የበለጠ ጠንካራ የሆነ የፓን አፍሪካኒዝም ዓይነት ይመስለኛል” ትላለች። ሳንቲም ኢትዮጵያ በካሪቢያን ሕዝቦች ዘንድ ያላት ቦታ ትልቅ መሆኑንም ታነሳለች።
ሳንቲም ባለፈው ጥቅምት ወር በተላለፈው በዚሁ ቃለ ምልልሷ “የፓን-አፍሪካኒዝም ስሜት እና ምናልባት ከመኖር በተገኘ ልምድ በካሪቢያን አገራት እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ቦታዎች በላይ ይበረታል።እኔም በእነዚህ ነገሮች በብዙ የተሞረድኩ ይመስለኛል” ትላለች።
በዚህ ምክንያት ነው ከምርምር ጥያቄዎቿ መካከል አንዱ “በፓን-አፍሪካኒዝም ተጠቃሽ ከሆነችው ኢትዮጵያ በላይ በካሪቢያን አገራት ውስጥ ለምን በርትቶ ተገኘ ?” የሚለው የሆነው።
ሳንቲም ለኮሌጅ ትምህርቷ የኋላ ምሁራዊ አስተሳሰቧ የተቀረጹበትን የካሪቢያን ደሴቶችን ለቅቃ ከመጀመሪያ እስከ ዶክትሬት ዲግሪያዋን ወደ ተማረችበት ካናዳ አቀናች።
በ18 ዓመቷ በካናዳ ቫንኩቨር በሚገኘው ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን መማር ጀመረች።
የካናዳ ኑሮዋ ጥቁርነት እና አፍሪካዊነት እንዴት አንድ ላይ እንደተሳሰሩ፤ አንዱን መሆን ማለት ሌላኛውን መሆን ማለት እንደሆነ የተገነዘበችበት ወቅት ነበር።
ሳንቲም ከ24 ዓመታት በፊት በጻፈችው አንድ መጣጥፍ፤ “‘ጥቁር’ ፖለቲካዊ ቃል እንደሆነ የተረዳኹት ካናዳ ነው። ሰውነቴ፣ ራሴ፣ ማንነቴ በዘረኝነት መነጽር ሲቃኝ ካየሁ በኋላ እኔም ራሴ ጥቁርነትን እንደ መለያዬ መግለጽ መረጥኩ” ትላለች።
የምሁርነት ሀ ሁ በጋዜጠኛነት በኩል. . .

ሳንቲም ይህን ጥልቅ የዘር እና የማንነት አረዳድ ይዛ ነው ከብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የወጣችው።ከዚያም የጋዜጠኝነት ሙያን ተቀላቀለች።
ሳንቲም ለአስር ዓመታት ጋዜጠኛ ሆና ሠርታለች። ይህ የጋዜጠኝነት ሥራዋ “ጠያቂ እንድሆን አድርጎኛል” ትላለች።
ከኮሌጅ ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ አጋማሽ በካናዳ ማኑቨር በሚታተም “ኪኔሲስ” በተሰኘ ጋዜጣ ላይ መጣጥፎችን ጽፋለች።
ኪኔሲስ የድሮ የትምህርት ቤት ጋዜጣ ነበር።
በየወሩ እየታተመ የሚወጣው ይህ የ’ፌሚኒስት’ ጋዜጣ እጅ አጠር ስለነበር በበጎ ፈቃደኞች ትክሻ ላይ ያረፈ ነበር።
ለጋዜጣው መታተም ጊዜ እና ጉልበታቸውን ከሚቸሩ ሴቶች መካከል ሳንቲም አንዷ ነበረች።
በጊዜው የጋዜጣው አርታኢ የነበረችው ፋጢማ ጃፈር “ሳንቲም ለዕድሜዋ ያልተለመደ የማወቅ ጉጉት ነበራት” ትላላች።
በሳንቲም እና ፋጢማ መካከል ያለው የዕድሜ ልዩነት አስር ዓመት ነው። ይህ የዕድሜ ልዩነት ኮከባቸው እንዳይገጥም አላደረገውም። ሁለቱም ለሚዲያ የነበራቸው ፍላጎት እና የፀረ ቅኝ ግዛት እና ፀረ ዘረኝነት ፖለቲካቸው ቃል ሳይለዋወጡ አግባባቸው።
ሳንቲም እና ፋጢማ ግን ብቻቸውን አልነበሩም።
ጋዜጣው ለብዙ አፍሪካውያን ተማሪዎች እና ከካሪቢያን፣ ከካናዳ እና ከአሜሪካ ለመጡ ጥቁሮች መሰባሰቢያ ዋርካ ነበር። በኪኔሲስ ጋዜጣ ስር የተሰባሰቡት ሴቶች ግራ ዘመም የፌሚኒስት አክቲቪስቶች ነበሩ።
ያነቧቸው ከነበሩት ነጭ ያልሆኑ ሴት ፀሐፊያን መካከል ኦድሬ ሎርድ፣ አሳታ ሻኩር፣ ቶኒ ሞሪሰን፣ ፋጢማ ሜርኒሲ፣ ጁምፓ ላሂሪ፣ ሳንድራ ሲስኔሮስ፣ ቼሪ ሞራጋ ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ሴቶች ብዙ ጊዜ አብረው ያሳልፋሉ።ፖለቲካ ያወራሉ፣ ይስቃሉ፣ ይዝናናሉ በወር አንድ ጊዜ የምትወጣውን ጋዜጣም ቆንጆ አድርገው ያዘጋጃሉ።ሳንቲም በቫንኩቨር ቆይታዋ ጥበብ፣ ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ ማንነት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መጣጥፎችን ጽፋለች።
ፋጢማ “በ20ዎቹ መጀመሪያ የምትገኘው ሳንቲም እንደዚህ ዓይነት ድንቅ ሥራዎችን ትሠራለች የሚል ምንም ሀሳብ አልነበረንም” ትላለች።
ከእነዚህ ድንቅ ሥራዎቿ መካከል አንዱን እንምዘዝ….
ከ28 ዓመታት በፊት እ.አ.አ 1996 የፀደይ ወራት በካናዳ 50 ሺህ ሴቶች የተሳተፉበት “Women March against Poverty” በሚል ስያሜ ብሔራዊ የሴቶች ንቅናቄ ነበር። ሳንቲም አንዷ ናት።
ሳንቲም ለሚዲያ፣ ለዕውቀት እና ፌሚኒዝም የነበራት ፍቅር በዚህ ንቅናቄ ላይ አንድ ሃሳብ ይዛ እንድትሳትፍ አነሳሳት። መጽሐፍትን በተሽከርካሪ ጭኖ እየዞሩ በነጻ ለሴቶች ማደል።
“ከከተማ ውጪ የሚኖሩ ሴቶች በቤተ-መጽሐፍት ውስጥ እንደ ልብ የማይገኙትን ነጭ ባልሆኑ ሴቶች የተጻፉ መጽሐፍት የማንበብ ዕድል እንዲኖራቸው ትፈልግ ነበር” ስትል ፋጢማ ታስታውሳለች።
ይህን ፍላጎቷን ነጮች በሚበዙባቸው የብሪቲሽ ኮሎምቢያ እና ሌሎች አውራጃዎች መጽሐፍትን ጭኖ እያደሉ በመዞር እውን አደረገችው።

“ትዝታ” ከሙዚቃ ቅኝት ባሻገር
በቫንኩቨር የአስር ዓመታት የጋዜጠኝነት ቆይታዋ በኋላ በኩቤክ አውራጃ የምትገኘው ሞንትሪያል ከተማ የሳንቲም መዳረሻ ሆነች። በሞንትሪያል ከሚገኘው ኮንኮርዲያ ዩኒቨርሲቲ በተግባቦት ጥናት (communication studies) የማስተርስ ዲግሪያዋን ተቀብላለች።
የኢትዮጵያን ታሪክ እና ፖለቲካ መረዳት የጀመረችው ገና በአሥራ አንድ ዓመቷ ቢሆንም፣ ይህ ወቅት ሳንቲም ወደ አካዳሚያው አንድ እግሯን ያስገባችበት እና ስለኢትዮጵያ የጠለቀ ጥናት እና ምርምር ወደ ማድረጉ ይበልጥ የተሳበችበት ነበር ማለት ይቻላል።
ከላይ በተጠቀሰው መጣጥፏ ላይ፤ “በአስራ አንድ ዓመቴ የአገሬን ታሪክ መረዳት ነበረኝ። ለ1966ቱ አብዮት ምክንያት የሆኑትን የተወሰኑ የፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች ተረድቼ ነበር” ትላለች።
በለጋ ዕድሜ የጀመረው ይህ መረዳት ኋላ ላይ ጎምርቶ በቅጡ የተሰነደ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ላይ ትኩረት ያደረገ መጽሐፍ ወጥቶታል። “Ethiopia in Theory: Knowledge Production and Social Change, 1964-2016” የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፏ የታተመው ከአምስት ዓመታት በፊት ነው።
ይህ መጽሐፍ ሳንቲም በቶሮንቶ በሚገኘው የዮርክ ዩኒቨርሲቲ በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እሳቤ (Social and Political Thought) ከሠራችው የሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ የጥናት ጽሑፍ ያደገ ነው።
ሳንቲም በአንድ ቃለ ምልልሷ መጽሐፉን በቶሮንቶ በሚገኝ ሰገነት ላይ እንደጻፈችው ተናግራለች። በዚህ ሰገነት ስለ ከኢትዮጵያ አብዮት የወረሰችውን እያሰበች፣ ትላንትን እያስታወሰች ባለፈው ጊዜ እየተብሰለሰለች፤ ትዝታ በናፍቆት እና ማጣት በኩል እንዴት ዛሬም አብሮን እንዳለ በማሰላሰል በጽሞና ታሳልፍ ነበር።
በቶሮንቶ ሰገነት ላይ የተፀነሰው የሳንቲም የመብሰልሰል ጊዜ እና ጽሞና “Ethiopia in Theory…”ን ወለደ።
የሳንቲም መጽሐፍ ዘር የተዘራው በልጅነቷ ነው። በልጅነቷ “አሳዛኝ” የምትለውን የትዝታ ሙዚቃ ደጋግሞ ማጫወት በትኩስ ቁስል ላይ ጨው መነስነስ ሆኖ ስለሚሰማት የትዝታ ሙዚቃ ወዳጅ አልነበረችም።
በዙሪያዋ ያሉት አዋቂዎች ትላንትናቸው አብሯቸው አለ። ትዝታቸው ያብሰለስላቸዋል። በዚሁ ሁሉ ጊዜ ሳንቲም እነዚህ አዋቂዎች አብሯቸው የሌለውን ትውስታ መናፈቅ እንዲያቆሙ ትጥር እንደነበር ታስታውሳለች።
ከብዙ ዓመታት በኋላ ግን ትዝታ የሃሳቧ ዋና ማብሰልሰያ አንጓ ሆኖ መጣ። የኋላውን መተው የሚያስከትለውን ጎዶሎነት ትዝታን ይዛ በመጽሐፏ ተከራከረች።

የሳንቲም መጽሐፍ በሁለት ክፍሎች የተዋቀረ ነው። በ1960ዎቹ በ“ታገል” እና “ቻሌንጅ” መጽሔቶች ላይ ይወጡ የነበሩ የተማሪ ጽሑፎችን ይመረምራል። አብዮተኛ ተማሪዎቹ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዴት ተረዱት? ከዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ጋር እንዴት አስተሳሰሩት? የሚለውን ይተነትናል።
በኢትዮጵያ አብዮት ተሳታፊ የነበሩ ተማሪዎች እና ሃሳቦቻቸው እንዴት የኢትዮጵያን ፖለቲካ በምን መልኩ ቅርጽ እንዳስያዙ ታሳያላች። በተጨማሪም በተማሪዎች ንቅናቄ ዋና መነጋገሪያ ሆኑት ጉዳዮች በወቅታዊ የአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ትቃኛለች።
እሌኒ በመጽሐፏ የትዝታ ሙዚቃን እንደ ኅልዮት መቀመሪያ አድርጋ አብዮቱ የሠራውን ፖለቲካዊ ሁኔታ ትተነትናለች። በተለይም ከመሐሙድ የትዝታ ሙዚቃ ፡
“ትናንትን ጥሶ፤ ዛሬን ተንተርሶ
ከነገም ተውሶ፤ አምናንም አድሶ
ይመጣል ትዝታ ጓዙን አግበስብሶ”
የሚሉትን ስንኞች እንደ መንደርደሪያ በመውሰድ ቅድመ-አብዮት የተማሪዎች የፖለቲካ ንቅናቄ በአብዮቱ ውስጥ እንዲሁም ከአብዮቱ በኋላ ያለ የፖለቲካ ተዋስዖ ውስጥ የማይለቅ ጥላውን እንደጣለ ታሳያለች።
ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው አፍሪካ የማኅበራዊ ሳይንስ የጥናት መስኮች በምን ያህል መጠን የፖለቲካ እሥረኛ እንደሆነ ትዘክራለች።
በተማሪዎች የሚቀመሩ የፖለቲካ እሳቤዎች ከጽሑፍ ሙግት እና የጠረጴዛ ላይ ውይይት በዘለለ አጠቃላይ አገራዊ ጉዳዮችን የሚወስኑ ሆነው ይገኛሉ። ለዚህም እንደ ማሳያ፣ ሳንቲም ከአብዮቱ በፊት በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ልሳን የነበረው “ቻሌንጅ” መጽሔትን በመውሰድ በመጽሔቱ ውስጥ የተነሡ የተማሪዎች ሙግቶች ቀጣይ የአገሪቱ የፖለቲካ ዕጣ-ፈንታዎችን እንደወሰነ ታስገነዝባለች።
እሌኒ በመጽሐፏ ብዙ ኢትዮጵያዊ ምሁራን የዘነጉትን አፍሪካዊ ጉዳዮች በሁለተኛው የመጽሐፏ ምዕራፍ ታነሣለች። ‘በተለይም ከ1970ዎቹ በኋላ ከመጠን በላይ ጥቅል አልያም በነጠላ ጉዳዮች ላይ አተኳሪ የሆኑ ትንተናዎችን’ በማምጣት የሚከሰሰውን የአፍሪካ ጉዳዮች ጥናት መስክ ከተለያዩ ሥፍራዎች በመቃኘት ሰፊ ትንተናን አቅርባለች።

እዚህ ጋር የቀድሞ ተማሪዋ ሠራዊት ስለ “Ethiopia in Theory” የምትለውን ቃል በቃል እንውሰድ. . .
ሠራዊት ስለመጽሐፉ ስታወራ “ብዙ ነገር አለው…” ብላ ነው የምትጀምረው።
“በእያንዳንዳችን ውስጥ ስላለ መቃተት በትላንት እና በዛሬ መካከል ስላለ ውጥረት እና በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ስለመመላለስ ነው የምታስበው። ግን እሱ እንዳለ ሆኖ፤ ለእኔ ትልቁ ነገር የማኅበራዊ ሳይንስን የፖለቲካ ሚና ነው የሚያሳየኝ።
“ማኅበራዊ ሳይንስ የሰውን ልጅ ውስብስብ ችግሮች መፍታት የምንችልበት ቁልፍ ሊሰጠን መቻሉ እንዳለ ሆኖ ጥያቄ አነሳሳችን የምርምር ዘዴያችን ትወራችን ከሕይወት የተላቀቀ እና ያለንበትን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ከመሆኑ የተነሳ በተለይ በአህጉራችን የሰውን ልጆች ሰቆቃ የማራባት እና የማስቀጠል ሚና መጫወቱን ታሳያለች። በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ብቻ ሳይሆን አሁን ድረስ ያንን የማኅበራዊ ሳይንስ ቋንቋ እንዴት እንደምንኖረው በአገሪቱ ታሳየናለች። ይህንን ስታደርግ ግን ያለተስፋ አትተወንም። መንገድም ትቀይሳለች።
“ሌላው ብዙ ተመራማሪዎች ስለ አፍሪካ ሲጽፉ እንደ ጂኦግራፊያዊ ቦታ ብቻ የማየት እና ግዛታዊ የማድረግ ነገር አለ። እሷ የአፍሪካ ጥናትን እንደ ፖለቲካዊ እና ኢፒስቲሞሎጂካል (ሥነ-ዕውቀት) ፕሮጀክት እንድናየው ነው የምትጋብዘን። የእውቀት ምርት ሂደቱ ከቅኝ ግዛት እና ከካፒታሊዝም ጋር ያለውን መጠላለፍ (ትስስር) እንድናይ ታግዘናለች።
“ሳንቲም መጻፍን የህልውና ጥያቄ አድርጋ ታመጣዋለች። ሕይወቷን ስንመለከተው ያንን ያስረግጥልናል።መጨረሻ ላይ እስከ ምትሄድ ድረስ ከአልጋዋ ራስጌ መጽሐፍ ወይም የሆነ ነገር አለ፤ እያነበበች ነው ወይም እያሰላሰለች ነው።
“መጻፍ ቅንጦት አይደለም። እየጻፍን ትግል እያደረግንም ነው። የመሄዷ ጉዳት ለእኛ ትልቅ ነው። በተለይ የሴት ምሁራን ቁጥር እጅግ አናሳ በሆነበት እንደሷ የሚያየን የሚሰማን አብሮን የሚያስብ መልኅቅ ማጣታችን ብቸኝነት እንዲሰማ ያደርጋል።ግን ደሞ በዚህ መንገድ የእሷን ሃሳብ ስንኖረው ሳንቲም ትቀጥላለች።”
ካንሰር እና ጦርነት በለጋ ዕድሜ እየሞቱ መኖር…

ፕሮፌሰር እሌኒ ሳንቲም ዘለቀ ከሁለት ሳምንት በፊት ሕይወቷ ያለፈው በደረጃ አራት የጡት ካንሰር ነው። ሳንቲም ከካንሰር ጋር ለዓመታት ስታደርግ የቆችውን ትግል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጿ በኩል ስታጋራ ቆይታለች።
ሳንቲም ከካንሰር ጋር የነበራትን እንዲሁ የህመም ስሜትን እና የህክምና ሂደት መዘገብ አልነበረም። በህመሟ ስለ ዕኩልነት ስለ ጤና ተደራሽነት ገጠመኟን አጋርታለች።
ከካንሰር ጋር መታገል ምን ማለት እንደሆነ፣ የተማረችውን እና ስለ ካንሰር የተገነዘበችውን ሰንዳለች።
የማኅበራዊ ሳይንስ እና ሥነ-ሰብ ጥናቷ የትኞቹ ዶክተሮች ስለ ህክምናዋ ውሃ የማይቋጥር ክርክር እያቀረቡ መሆኑን እድታውቅ እና የህሙማን ጠበቃ እንድትሆን እንዳደረጋት በአንድ ወቅት ገልጻለች።
ሳንቲም እንደ ማንኛውም የካንሰር ታማሚ አልነበረችም። ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለው “ለካንሰር እጅ ሰጠች” [she lost her battle to cancer] ለእሷ የሚሆን አይደለም።
ሠራዊት በቀለ “ [ሳንቲም] እሱን አገላለጽ የምትስማማበት አይመስለኝም። ካንሰርን የምታስበበት መንገድ በጣም ውስብስብ ነው” ትላለች።
ለዚህ የራሷ የሳንቲም ማስታወሻ እማኝ መሆን ይችላል። ሳንቲም ካንሰርን እንደ አንድ ዓይነት ክፉ፣ ከውጭ የሚመጣ ባዕድ ኃይል ሳይሆን በመኖር ሂደት ውስጥ ያለ ሕይወትን የመፈለግ ጥረት አድርጋ ነው የምትመለከተው።
ሳንቲም የካንሰር ህመሟን ተጠቅማ ምሁራዊ ማሰላሰሎችን አድረጋለች። ከፍልስጤም እስከ ኢትዮጵያ የሰው ልጅን ሰቆቃ ህመሟን አስታካ ለመገንዘብ ጥራለች።
ህመም ስለጦርነት፤ ጦርነት ስለ ህመም ጦርነት ያስተማራትን አስታወሳ ሳንቲም፤ “ሁለቱም አቅም፣ ፍትሃዊነት እና ደንዳና ትከሻ ያለንን እሳቤ ይንዳሉ። ስለዚህ እነሱን በሞኝ የጀግንነት ታሪኮች ወይም በሽልማት/ቅጣት ማዕቀፍ ለመቅበር እንሞክራለን” ትላለች።
እዚህ ጋር ፈውስ የሌለውን እና የራሷን ደረጃ አራት የጡት ካንሰር እና “በጋዛ የሚዘንበውን የማያባራ የቦምብ ዝናብ” መሳ ለመሳ ታስቀምጠዋለች።
ሳንቲም በግላዊ ካንሰር ህመሟ አጮልቃ ለሁለት ዓመታት የቆየውን በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ትግራይ ክልሎች ወደተዛመተው የእርስ በእርስ ጦርነት ትተነትናለች። እየጻፈችው ስለነበረው መጽሐፍ ስለ ትችቷ፣ ትንታኔዋ ከቀድሞ ተማሪዎቿ የተሻለ እማኝ ላናገኝ እንችላለን።
ሳንቲም በህመሟ ውስጥ “ሰውነታችን በምን ዓይነት ሂደት ውስጥ እንደሚያልፍ እየሞትንም እየኖርንም በምን ዓይነት ሂደት ውስጥ እንደሚሄድ የምታስብ ነው የሚመስለኝ” ትላለች ሠራዊት በቀለ።

የሳንቲም ሁለተኛ መጽሐፍ ከሁለት ዓመት ሰባት ወራት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት አባቷ የተጻፉ ደብዳቤዎች ናቸው። አራት ደብዳቤዎች አራት የመጽሐፍ ምዕራፎች።
ሳንቲም ከአባቷ ዶ/ር ዘለቀ ጋር ነበራት ግንኙነት ከአባት እና ልጅነት የዘለለ ነበር። ርዕዮተ ዓለማዊ እና ጽንሰ ሃሳባዊ ውይይቶችን ያደርጉ ነበር። “በቢሮዬ መስኮት አሻግሬ ስመለከት የአባቴን አንድ የታሪክ ዘለላ አያለሁ” ትላለች።
ሌላኛዋ የሳንቲም ተማሪ ነጻነት ገብረሚካኤል “ሳንቲም ከአባቷ ጋር ያላትን ወዳጅነት ልትቀጥልበት የወደደችው ተምሳሌት ለእሳቸው ደብዳቤ መጻፍ ነው። የካንሰሯ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ፤ እና ኢትዮጵያ ላይ እየሆነ ያለውን ነገር ድሮ እንደሚጫወቱት ማለት ነው” ስትል ታብራራለች።
“መጽሐፉ ከዕለታዊ ዕውነታዋ ይነሳል” የምትለው ነጻነት፤ “ራሷን እና አስራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ሆኖ በእርስ በእርስ ጦርነቱ የሞተው ወጣት መካከል ያለውን ቅርበት ትጽፋለች” ትላለች።
ሳንቲም ለዚያ ለማታውቀው ልጅ ግን ደግሞ ለሚሞተው ራሷ ወደ ሞት እየሄደችበት ካለው ህመም ጋር እያያዘች በለጋ ዕድሜ መሞት ምን ማለት ነው? ወደ ሞት አፋፍ እየሄዱ መኖርስ ምን ትርጉም አለው? እያለች ታሰላስላለች፣ ትጽፋለች።
በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ካቀረበችው የመፅሃፏ ቅንጫቢ እንደተረዳሁት፤ ሳንቲም እየጻፈች ያለችው መጽሐፍ “ጦርነትን በጣም በቀለለ መንገድ ‘የተለመደ የአፍሪካውያን አባዜ’ ሳይሆን ጥልቅ በሆነ እና በደንብ ታሪክን እና ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ አሰላለፍን ባማከለ መንገድ፤ በሕይወት ያሉ ሰዎች የሚኖሩትን ትግል ማዕቀፍ በማድረግ እንዴት ልናስብ እንችላለን?” የሚሉ ጥያቄዎችን እንደምታነሳ እረዳለሁ ትላለች ሠራዊት።
ከዚህ በተጨማሪም፤ መጽሐፏ ስለ የእርስ በእርስ ጦርነት ማሰብ ምን ማለት ነው? አፍሪካን የምናይበት መንገድ ምን ይመስላል? የሚሉትን ጥያቄዎች ያነሳል።
ሳንቲም “ህመምን [እና] ጦርነትን አፍሪካን ይዘን ስናስብ ፈውስ ከየት ልናገኝ እንችላለን። ፈውስ በመሞት ሂደት ውስጥ እያለፍንም ማለት ነው” የሚሉ ሃሳቦችን እንደምታነሳ ሠራዊት ትናገራለች።
የራሷን ከሞት ጋር ያላትን መጋፈጥ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ ካለ አንድ ለጋ ወጣት ጋር ታመሳስለዋለች። ነጻነት “ሳንቲም በዚህ ምስስሎሽ በጦርነት ምክንያት ሕይወታቸውን እያጡ ላሉ ወጣቶች ድምጽ በመሆን ለራሷም ደግሞ ድምጽ በመሆን አንድ ላይ በደብዳቤ መልክ አወዳጅታ ሰንዳዋለች” ትላለች።
እንደ ነጻነት ገለጻ “የማኅበራዊ ሳይንስ እና አፍሪካ ጥናት ትንታኔዎች በየዕለቱ ከምናልፍበት ኑሮ ተፋትቷል የምትለው ሳንቲም፤ የትግራዩን ጦርነት ያየንበት፣ የተነተንበት አግባብ እና የካንሰር ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማንነቱን በትንታኔዋ ታወዳጀዋለች”።
የሳንቲም ዋና መከራከሪያ “ጦርነቶች እንዴት ጀመሩ?” ከሚለው ሙግት በዘለለ ደም አፋሳሽ ጦርነቶች እያስከተሉት ያለውን መቅሰፍት እና ውድመት በማኅበራዊ ሳይንስ ትንታኔዎች ውስጥ መካተት አለባቸው የሚል ነው።
የሳንቲም ሚና ስለጦርነቱ መጽሐፍ በመጻፍ ትንታኔዎችን ማቅረብ ብቻ አልነበረም።
ለሁለት ዓመታት በቆየው በትግራይ ተከስቶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተዛመተው ደም አፋሳሹ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት አደባባይ ምሁርነት ሚናም ነበራት። ሳንቲም በጦርነቱ ወቅት የነበራት አቋም “ከመርኅ የሚመነጭ” መሆኑን ሠራዊት በቀለ ታነሳለች።
የእርስ በእርስ ጦርነቱ ከተጀመረ ከጥቂት ወራት በኋላ ሳንቲም ከሌሎች ስልሳ አፍሪካውያን ምሁራን ጋር በመሆን የአፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ ተፋላሚዎችን እንዲያሸማግሉ ጥሪ አቅርባለች።
በዚህ ሁሉ ጩኸቷ እና ከጦርነት ተቃርና መቆሟ ሳቢያ ነቀፌታዎች እና ትችቶችን አስተናግዳለች። “የነበረው ነቀፌታ እና ትችት ግን ከአቋማ አላነቃነቃትም” የምትለው ሠራዊት፤ “ምሁራዊ ታማኝነት ምን ማለት እንደሆነ በደንብ የምናይበት ነው። ሁላችንም ራሳችንን እንድንፈትሽ አድርጋናለች” ትላለች።
ሳንቲም በቅርብ የሚያውቋት ወዳጆቿ “መርሆች ነበሯት በእነሱ ኖራለች” ይላሉ። ከግፍ እና ከጭቆና በተቃራኒ የቆመች ምሁር ናት።
ሙሉ ዘገባው የቢቢሲ ነው