እርጅና የተጫናቸው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በቀጣይ ምርጫ ዴሞክራቶችን ወክለው እንዳይቀርቡ ከፓርቲ አባሎቻቸው ተደጋጋሚ ጥሪዎች እየቀረበላቸው ነው።
ቃላቶችን በአግባቡ ሰካክተው ሃሳባቸውን ለመግለጽ ሲቸገሩ የሚታዩት ጆ ባይደን ምንም እንኳ ከምርጫው እራሳቸውን እንዲያገሉ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብላቸው ኅዳር 2017 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ የፓርቲያቸው ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ሆነው ከመሳተፍ ወደኋላ እንደማይሉ እየገለጹ ይገኛሉ።
ረቡዕ ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም. ከቬርሞንት ግዛት የሆኑት ዴሞክራቱ ሴናተር ፒተር ዌልች ፕሬዝዳንቱ ከምርጫው እራሳቸውን እንዲያገሉ ጥሪ ያቀረቡ ሰዎች ዝርዝርን ተቀላቅለዋል።
ለዴሞክራቶች ከፍተኛ ገንዘብ ከሚለግሱት መካከል አንዱ የሆነው ዕውቁ የሆሊዉድ ተዋናይ ጆርጅ ክሎኒ እንዲሁ ባይደንን “ምርጫው ይቅርብዎት” ብሏል።
ባይደን ግን በአቋማቸው የጸኑ ይመስላሉ።
ከዚህ ቀደም ለባይደን ሙሉ ሊባል የሚችለውን ድጋፋቸውን የሰጡት ዴሞክራቶች ነሐሴ 2016 ዓ.ም. አጠቃላይ ስብሰባ ያደርጋሉ።
ባይደን በምርጫ ተሳታፊነታቸው የማይቀጥሉ ከሆነ የፓርቲ አባላቱ ድምጽ ሰጥተው አብላጫውን ይሁንታ ያገኘ ፖለቲከኛ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ሆኖ ይቀርባል።
ለመሆኑ ባይደን ከምርጫ እራሳቸውን ለማግለል ቢስማሙ ፓርቲው ትራምፕን ለመጋፈጥ ወደፊት ሊመጣ የሚችለው የዴሞክራቶች ዕጩ ማን ነው?

ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ
በዴሞክራቶች ውስጥ ባይደንን ተክተው ሊቀርቡ ይችላሉ የሚል ትልቅ ግምት ከተሰጣቸው ፖለቲከኞች መካከል ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ቀዳሚዋ ናቸው።
የባይደን ምክትል የሆኑት ካማላ ለፕሬዝዳንቱ ባላቸው ታማኝነት እንዲሁም በምርጫ ቅስቀሳው ያላቸውን ላቅ ያለ ተሳትፎን ከግምት በማስገባት ባይደንን ሊተኩ የሚችሉ ዕጩ ተደርገው እየቀረቡ ነው።
ካማላ ሃሪስ ብዙ ባነጋገረው ፕሬዝዳንታዊ ክርክር ላይ ባይደን “አጀማመራቸው ደካማ” የነበረ ቢሆንም ከትራምፕ በተሻለ ሁኔታ ሃሳባቸውን ገልጸዋል ሲሉ ፕሬዝዳንቱን ተከላክለው ነበር።
“ዕጩ አድርገን ያቀረብነው ባይደን ነው። ትራምፕን ከዚህ ቀደም አሸንፈናል። አሁንም መልሰን እናሸንፋለን” ብለዋል።
ካማላ ምንም እንኳ ላለፉት አራት ዓመታት የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ይቆዩ እንጂ በአሜሪካውያን ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እጅግ አናሳ እንደሆነ ይታመናል። ከሕዝብ የተሰበሰቡ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት 51 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን ካማላ ሃሪስን አይቀበሉም።

የሚሺጋን ገዢ ግሬቸን ዊትመር
ለሁለት የሥልጣን ዘመናት የሚሺጋን ግዛትን ያስተዳደሩት ግሬቸን ዊትመር የዴሞክራቶች ዕጩ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
እአአ 2028 በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መወዳደራቸው አይቀሬ ነው የሚባሉት የሚሺጋን ግዛት አስተዳዳሪ ግሬቸን ዊትመር፤ ለባይደን ባላቸው ያልተቋረጠ ድጋፍ ይታወቃሉ።
ግሬቸን በፖለቲካ ሕይወታቸው ማሳካት የሚፈልጉትን በግልጽ በመናገር ጭምር ይታወቃሉ።
ፖለቲከኛዋ እአአ 2028 ላይ የእርሳቸው ትውልድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንዲሆን ምኞታቸው እንደሆነ በአንድ ወቅት ለኒው ዮርክ ታይምስ ተናግረው ነበር።

የካሊፎርኒያ ገዢ ጋቪን ኒውሰም
ጋቪን ኒውሰም ለባይደን አስተዳደር ባለቸው ጠንካራ ድጋፍ ይታወቃሉ።
ይሁን እንጂ የካሊፎርኒያው ገዢ አጋጣሚውን ቢያገኙ የግል ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን እውን ከማድረግ ወደኋላ እንደማይሉ ተንታኞች ይገልጻሉ።
ጋቪን ኒውስም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ በመሰጠት እና ከሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካዮች ጋር በመፋጠጥ የዴሞክራቶች ምልክት ተደርገው እየተወሰዱ ነው።
የካሊፎርኒው ገዢ አሁን ላይ በአደባባይ የባይደን ደጋፊ እንደሆኑ ነው የሚገልጹት። ከፕሬዝዳንቱ ጋር ለመገናኘትም በቅርቡ ወደ ዋሸንግተን ተጉዘው ነበር።

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ፒት ቡቴጄጅ
የአሜሪካን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አንድ ቀን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የመሆን ህልም እንዳላቸው የአደባባይ ሐቅ ነው ይላሉ።
ቡቴጄጅ በባይደን አስተዳደር ውስጥ ያሉ አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪ ፖለቲከኛ ናቸው።
የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ በዘረፉ ለተከሰቱ በርካታ ችግሮች አግባብ የሆኑ ፈጣን ምላሾችን ሰጥተዋል ተብለው ይወደሳሉ።

የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ
ባይደንን ሊተኩ ይችላሉ ተብሎ ስማቸው ከሚጠራው መካከል የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ ይገኙበታል።
በአሜሪካውያን ዘንድ ዶናልድ ትራምፕን ሊያሸንፉ ይችላሉ የሚል እምነት እንዳለ የሕዝብ አስተያየት አሳይቷል።
ከጥቂት ቀናት በፊት ሮይተርስ የዜና ወኪል ይፋ ያደረገው የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ በቀጣዩ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን ሊያሸንፉ የሚችሉት ብቸኛዋ ግለሰብ ሚሼል ኦባማ ናቸው።
የሕዝብ አስተያየቱ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ ሰዎች ተመራጭ የሆኑት ሚሼል ኦባማ መሆናቸውን ከማሳየቱ በተጨማሪ አስተያየታቸውን ከሰጡ አምስት ሰዎች መካከል ሦስቱ ባይደንም ሆነ ትራምፕ በቀጣዩ ምርጫ ባይሳተፉ እንደሚመርጡ ገልጸዋል።
የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ባለቤት ግን ከዚህ ቀደም በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ ፕሬዝዳንት የመሆን ህልም እንደሌላቸው ተናግረው ነበር።

የፔንስልቬኒያ ገዢ ጆሽ ሻፒሮ
ጆሽ እአአ 2022 ላይ ከተመረጡ ወዲህ በአሜሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙ ፖለቲከኛ ናቸው።
የፔንስልቪኒያ ገዢ ከዚህ ቀደም ዐቃቤ ሕግ ነበሩ። በፓርቲያቸው ውስጥ በርካታ ኃላፊነቶች ነበሯቸው።
ባለፈው ዓመት በፊላዴልፊያ አውራ ጎዳና ላይ የነበረ ድልድይ ከፈረሰ በኋላ ጆሽ ሻፒሮ ድልድዩ በፍጥነት ተጠግኖ ሥራ እንዲጀምር ያደረጉበት ቅልጥፍና ትልቅ አድናቆትን አስገኝቶላቸዋል።
ምስጋና ቢቢሲ አማርኛ