በቱርኪዬ ሪፐብሊክ አገናኝነት የኢትዮጵያና ሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የመጀመሪያ ንግግራቸውን ካደረጉ በሁዋላ ሁለተኛ ዙር ውይይታቸውን ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም በአንካራ ለመቀጠል መስማማታቸውን የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይፋ አደረገ። የኢትዮጵያ የየውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ተመሳሳይ መገለጫ አውጥቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንካራ የተካሄደውን የመጀመሪያ ውይይት አመልክቶ ባወጣዉ መግለጫ በቱርኪዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊዳን ጋባዥነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር አህመድ ሞአሊም ፊቂ በአንካራ ተገናኝተው ተወይተዋል።
የተካሄደው ውይይት በሁለቱ አገራት መካከል ላሉ አለመግባባቶች መፍትሄ ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ግልፅና ወዳጅነት የተሞላበት የሀሳብ ልውውጥ የተደረገበት እንደነበር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አመልክቷል። ሁለቱ ሚኒስትሮች አሉ የሚባሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን መግለጻቸውን በመግለጫው ተመልክቷል
ሁለቱ ሚኒስትሮች መልካም ጉርብትናን እና ቀጠናዊ መረጋጋትን ከግምት በማስገባት መፍትሄዎችን ለማመላከት ያለሙ ምክክሮችን ለመቀጠልም እንደተስማሙ አረጋግጧል። ሚኒስቴሩ ሁለቱም ሚኒስትሮች የቱርኪዬ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ምክክሩን አገራቸው ለማስተናገድ የወሰዱትን ተነሳሽነት አድንቋል፡፡
ሶማሊያ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ ያደረጉትን የባህር በር የመግባባ ስምምነት ተከትሎ ሶማሊያ ተቃውሞ ማሰማቷ ይታወሳል። ኢትዮጵያ በበኩሏ ስምምነቱ የሶማሊያን ህዝብም ሆነ መንግስት የሚጎዳ እንዳልሆነ በመጥቀስ ስምምነቱን ዳር ከማድረስ ወደ ሁዋላ እንደማትል በይፋ ማስታወቋ አይዘነጋም። ይህንኑ ተከትሎ ሶማሊያ በሰላም ማስከበር ሶማሊያ ውስጥ የህይወት ዋጋ ሲከፍል የኖረውን የኢትዮጵያ መከላከያ እንዲወጣ ፍላጎት እንዳላት ስታስታውቅ ቆይታ ነበር። ስላሳ ከመቶ የሚሆነውን ሶማሌያን እየተበቀ ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንደሆነ ይታውሳል።
