“ፕሬዚዳንት ሩቶ ረፍዶባቸዋል” የሚሉት ኬንያውያን ለጠየቁት ጥያቄ መልስ ቢሰጣቸውም ጨዋታ ቀይረው “ሩቶ ይውረዱ” እያሉ ነው። ኬንያውያኑ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣት ሲጀምሩ የተቃወሙት አገሪቱ ልትተገብረው ያቀደችው የግብር ጭማሪ ብቻ ስለ ነበር ” ህጉ እንዲጸድቅ ፊርማዬን አላኖርም” በሚል ሩቶ በይፋ ሽንፈታቸውን ሲያውጁ ረብሻው ቀጥሏል። ዝርፊያና ውንብድና ያስመረራቸውና የአገራቸው መተራመስ ያሰጋቸው ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በጸደቀው ህግ ላይ ፊርማቸውን እንደማያኖሩ፣ ከዚያም አልፈው አዋጁን እንደሚሰርዙት ቢገልጹም ሰሚ አላገኙም። አክቲቪስቶች እንደሚሉት ሩቶ ተቃውሞ እንደተሰማ ህጉ ሳይጸድቅ ማገድ ነበረባቸው። ይህን ባለማድረጋቸው፣ ሲመረጡም ስራ አጥነትን፣ የኑሮ ውድነትንና ሌብነትን ለመቅረፍ ቃል ቢገቡም ይህን ባለመፈጸማቸው ” አንድ ላይ ተዳምሮ ጊዜው አልፎባቸዋል” ሲሉ ተደምጠዋል። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት ፕሬዚዳንቱ መውረድ አለባቸው።
“ወጣቶች” እየተባሉ የሚጠሩት የአመጹ የፊት መስመር ተሰላፊዎች፣ ፕሬዝዳንቱ ስልጣን እንዲለቁ በሚጮሁበት ልክ ውንብድናና ዘረፋ ያሰጋቸው ዜጎች ድምጽ እየጎላ ነው። የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ካቢኔ ፀሃፊ ኪቱሬ ኪንዲኪ “በሃገሪቱ የበለጠ ትርምስ ታቅዷል” ሲሉ መረጃ መገኘቱን ገልጸው አስጠንቅቀዋል።
በኬንያ የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ካቢኔ ፀሃፊ ኪቱሬ ኪንዲኪ ተቃዋሚዎች በቀጣይ ቀናት የበለጠ ትርምስ እና ዘረፋ እያቀዱ መሆኑን ገልፀው ለድርጊቱ ጠንካራ የአፀፋ እርምጃ መንግስታቸው እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል።
እንደ አገሪቱ ሚዲያዎች ዘገባ ከሆነ ሁለተኛ ሳምንቱን ባገባደደው ተቃውሞ አርባ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከሶስት መቶ ሃምሳ በላይ የተለያየ መጠን ጉዳት ደርሶባቸዋል። የታሰሩትም በርካታ ናቸው።
አመጹ ሲጀመር ዝም ብለው የነበሩ የኬንያ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ከየአቅጣጫው መግለጫ በማውጣት በኬንያ የመንግስት ለውጥ እንዲደረገ ወጣቶቹ ያነሱትን ጥያቄ በማጉላት ላይ ናቸው።
በኬንያ ለፕሬዝዳንትነት ነሐሴ 9 ቀን በተካደው ምርጫ ዊልያም ሩቶ አሸናፊ በተደረጉበት ውጤት ቅር የተሰኙት ተቀናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋ አሁን ሩቶ ይውረዱ ካሉት ወገን መሆናቸውን ካስታወቁት መካከል ቀዳሚው ናቸው። በምርጫ ሲሸነፉ ኦዲንጋ ቅሬታቸውን ለፍርድ ቤት አቅርበው እንደነበር ይታወሳል። የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን የዊሊያም ሩቶን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ አሸናፊነት አጽንቶ ጉዳዩ በዛው መቋጨቱ ይታወሳል። የዛኔ ሚና የለዩ ደጋፊዎች ወደ ከፋ ግጭት እንዳያመሩና በኡሁሩ ዘመን እንደሆነው አይነት መገዳደል እንዳይፈጸም ስጋት የገባቸው ዛሬም በኬንያ የተጀመረው ትርምስ አድጎና ሰፍቶ አገሪቱን ወደ ጎበዝ አለቆች አገዛዝ እንዳያመራት እየገለጹ ነው።
በኬንያ የፋይናንስ ረቂቅ ህጉን ተከትሎ በመካሄድ ላይ ባለው ተቃውሞ በበርካታ ሱቆች እና የንግድ ተቋማት ላይ ጥቃት እና ዘረፋ እንደተፈመ በስፋት መረጃ እየወጣ ነው። ይህ ዘረፍና ውንብድና በስራ አጥነትና በኑሮ ውድነት ተቸግረናል ለሚሉ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፖሊስ በወንጀል የጠረጠራቸውን 270 ሰዎች ማሰሩን መገናኛ ብዙሃኑ በዘገባቸው አስታውቀዋል፤ 204 የሚሆኑት የታሰሩት በዋና ከተማዋ ናይሮቢነው። የዘርፋውና ውንብድናው መጠን ፖሊስ አሰርኳቸው ከሚላቸው ጋር የሰማይና ምድር ልዩነት እንዳላቸው ጠቅሰው ስጋታቸውን የሚገልጹ ኬንያውያን ፖሊስ ስራውን እንዲሰራ እያሳሰቡ ነው።
ይህ ኢትዮጵያም እንዲስፋፋ እየተቀሰቀሰበት ያለው የኬንያ የተቃውሞ እንቅስቃሴ “የዝርፊያ እና ውንብድና እንቅስቃሴዎችን ፖለቲካዊ ለማድረግ ተሞክሯል” ሲሉ ኪንዲኪ የሀገሪቱ መንግሥት ወንጀለኞችን ለማስቆም እና የኬንያውያንን ደህንነት ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅሰው ለህዝብ ስጋት ምላሽ ሰጥተዋል።
“ለብጥብጡ ተጠያቂ የሆኑት ወንጀለኞች የፋይናንስ ረቂቅ ህጉን በመቃወም ሽፋን ሰላማዊ ተቃውሞን የተጠቀሙ ወንጀለኞች ናቸው” ያሉት ፕሬዝዳንት ሩቶ አጥፊዎች ከህግ አያመልጡም ሲሉ ዝተዋል። ዛቻውና ማስጠንቀቂያው ቢበዛም በኬንያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ያስከተለውን ዝርፊያና ጥቃት ተከትሎ በርካቶች ስጋት ላይ መሆናቸው ታውቋል።
በኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ በየሰፈሩ እየቆጠቆጠ የመጣውን ዝርፊያና ውንብድና ህዝብ ራሱን አደራጅቶ ሰፈሩን በመጠብቅ እንዴት እንደቀለበሰው ያስታወሱ፣ አሁን ላይ ለኢትዮጵያ አመጽ እየጠመቁ ያሉ ረጋ ብለው እንዲያስቡና ወደ ሰለጠነ የተቃውሞ ትግል እንዲያመሩ ያሳሰቡ ጥቂት አይደሉም። ነውጥን ከኬንያ ከመግዛት፣ የአዲስ አበባ ነዋሪ ራሱን በየሰፈሩ አደራጅቶ ውንብድናንና ዘረፋን እንዴት እንዳስቆመ ለኬንያን ህዝብ ልምድ ማካፈሉ እንደሚበጅ አመልክተዋል።