በደቡብ ኢትዮጵያና አጎራባች ክልሎች ለሚገኙ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዜጎች በስፔሻሊቲ ደረጃ አገልግሎት መስጠት የሚችል፣ ስድስት መቶ የህሙማን መተኛ አልጋ እንዳለው የተነገረለት፣ በኢትዮጵያ ደረጃ እጅግ ዘመናዊ የተባለ ሆስፒታ የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገነባ። ሆስፒታሉ ዘመኑን በዋጁ የህክምና ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተመልክቷል። ነገ ይመረቃል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በጤናው ዘርፍ የተሻሉ ባለሙያዎችን በማፍራት ለአገሪቷ የጤና ስርዓት መሻሻል ከፍተኛ ድርሻን እንደሚያበረክት ተገለፀ።
የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ ዘመኑን በዋጁ የህክምና ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ተገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ጤና ቢሮ በበኩሉ የሆስፒታሉ መመረቅ “በክልሉ የጤና አገልግሎትን ከማሳደግ ባለፈ የጤና ቱሪዝምን ለማጠናከር ጉልህ ሚና ይጫወታል” ብሏል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ በድሩ ሂሪጎ ለኢዜአ እንዳስታወቁትም፤ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በጤናው ዘርፍ የተሻሉ ባለሙያዎችን በማፍራት ለአገሪቷ ጤና ስርዓት መሻሻል ድርሻው ከፍተኛ ነው።
ሆስፒታሉ በደቡብ ኢትዮጵያና አጎራባች ክልሎች ለሚገኙ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዜጎች በስፔሻሊቲ ደረጃ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል አስረድተዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ በ25 ሺህ ካሬ ላይ የተገነባው ሆስፒታል ከ600 በላይ የህሙማን አልጋዎችን የያዘ ሲሆን፤ “ዘመኑን በዋጁ የህክምና ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል” ብለዋል።
ሆስፒታሉ የሲቲ ስካን፣ የዲጅታል ኤክስ ሬይ፣ የአልትራሳውንድ፣ የከፍተኛ የደም መመርመሪያ ማሽኖችና ቤተ ሙከራዎችን የያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
ማሽኖቹ የውስጥ ደዌ፣ የቀዶ ሕክምና፣ የአጥንት፣ የማህፀንና ጽንስ፣ የህፃናት፣ የእናቶች፣ የአንገት በላይ፣ የስነ አዕምሮና ሌሎች ህክምናዎችን ለመስጠት እንደሚያገለግሉም ጠቁመዋል።
ሆስፒታሉ መጋቢት 29 ቀን 2007 ዓ/ም የመሠረት ድንጋይ እንደተቀመጠለት ገልፀው፤ ግንባታው ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ተጠናቆ ነገ እንደሚመረቅ ጠቁመዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ በበኩላቸው፤ የሆስፒታሉ መመረቅ ለክልሉና ለአጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች ዘመናዊ ህክምና እንዲያገኙ የሚያስችል አደረጃጀት የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ዘመኑን የዋጁ የተለያዩ የህክምና አገልግሎት ማሽኖች የያዘ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም እንደ አገር የጤና ቱሪዝምን በማጠናከር ተመራጭነትን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።
የህክምና አገልግሎትን ጥራት ዲጂታላይዝና ዘመኑን የዋጁ እንዲሆኑ የተጀመሩ ተግባራት እንዳሉ አንስተው፤ የሆስፒታሉ ይህንን ከማጠናከር ባለፈ ልምዱን ለማስፋት የሚያስችል ትልቅ ማሳያ እንደሆነም ገልፀዋል።
በቀጣይም ሆስፒታሉ ላይ የሚሰጡ አገልግሎቶች የማህበረሰቡን ጥያቄ በአግባቡ የሚፈቱ እንዲሆኑ ቢሮው በቅርበት እንደሚሰራም አቶ ናፍቆት ተናግረዋል።
ኢዜአ