ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአረንጓዴ ሌጋሲ እያስመዘገበች ያለው ታሪክና ክብረወሰን በዓለም ደረጃ እውቅና የተሰጠው ስለመሆኑ በተከታታይ ሲዘገብ ቆይቷል። ይህ ዓመቱን ሳያዛንፍ የሚተገበረው የችግኝ ተከላ ዘመቻ ዘንድሮም ተጀምሯል። የዘንድሮ እቅድ 7.5 ቢሊዮን ቸግኝ መተከል ነው።
ለውጭ አገር ኤክስፖርት የሚሆኑ ሰብሎችን፣ ለምግብ ፣ ለከብቶች መኖ እንዲሆም የተፈጥሮ ደኖችን ለማስፋት ታስቦ የተጀመረው የችግኝ ተከላ በኢትዮጵያ በአይን የሚታይ ለውጥ ማምጣቱን መረጃዎች ብቻ ሳይሆኑ ዜጎች በአንደበታቸው እየመሰከሩ ነው።
የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ወርዶ በመቶኛ ሶስትና አራት በመቶ ወደ 17.2 በመቶ ያሳደገው የአረንጓዴ ሌጋሲ ምክንያቱ ባይታወቅም “የውድቀት” ዜና አድርገው በመቃወም የሚዘግቡና ማስተባበያ የሚያዘጋጁ ሚዲያዎች ዓላማቸው ምን እንደሆነ ቀና ልቦና ላላቸው ሊገባ የማይችል እንደሆነ እየተገለጸ ነው።
በችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ ቀን ሆን ብለው የክፋት ዜማ አልበም ከሚያሰራጩ፣ የማጥላላት ዘመቻ ከሚያስተላለፉ፣ በማህበራዊ አውዶች የሃሰት መረጃ የሚያሰራጩ በብዛት ተግባሩን በቅብብል ለማንቋሸሽ ቢጥሩም የኢትዮጵያ አረንጓዴ ሌጋሲ ለአፍሪካ ሞዴል ከመሆን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝቷል። በአገር ደረጃም ሽልማት አሰጥቷል።
የልማት ተግባራትን ከጥላቻ ፖለቲካ ጋር በመቀላቀል መቃወም የተለመደ በሆነባት ኢትዮጵያ ችግኝ ብቻ ሳይሆን የስንዴ፣ የሩዝ፣ የአቡካዶ፣ የቡና፣ የፓፓዬ፣ የአትክልት ወዘተ ስራዎችም ይኮነናሉ።
ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የተፈጥሮ ሃብት መመናመንና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ በመከላከል የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና ዘላቂነት ያለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም የራሱ የሆነ ትልቅ ድርሻ እንዳለው መንግስት ደጋግሞ ይገልጻል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከት ታቅዶ ከሰኔ ወር ጀምሮ ተከላ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
ለመትከል ከታቀደው 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ እስካሁን ድረስ በመላ ሀገሪቱ 4 ቢሊዮን ችግኞች መትከል እንደተቻለ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በዕቅድ የተያዘውን ችግኞች በቀጣይ ጊዜያቶች ሙሉ በሙሉ መትከል እንሚገባ ያሳሰቡት ሚኒስትሩ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር መጠበቅና መንከባከብ እንደሚያስፈልግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን በበኩላቸው በችግኝ ተከላው ወቅት እንደተናገሩት በቀጣይ ዓመታት የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ ብሎም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን አደጋ ለመከላከል የሚያስችል የአረንጓዴ ሽፋን ለማሳደግ በታቀደና በተቀናጀ መንገድ የልማት ስራው በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ከተተከሉ ችግኞች መካከል የወይራ፣ የኮሶ፣ የአፕል፣ የብርቱካን፣ የሎሚ፣ የጥድ፣ ዝግባና ዘይቱ መሆናቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።