አንድ በኢትዮጵያ ምድር የተወለደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ ምን ያህል እምነቱ ከውስጡ ቢሟጠጥበት ነው ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በአሁኑ ወቅት የሚጠይቀው? በማለት መብሰልሰልም ክፋት የለውም፡፡ አንድ ዜጋ ለኢትዮጵያ ጥቅም ለመቆም በኢትዮጵያዊነቱና በአገሩ ኢትዮጵያ ላይ የኢትዮጵያዊነት እምነት ሊኖረው የሚገባ መሆኑ አሌ የሚባል ነገር የለውም፡፡ ደምስ (ዶ/ር) ያንን አጢኖ፣ በአገራዊ ምክክሩ ወቅት ጥያቄዎቹ እንደ ቀዳሚ አጀንዳ ተደርገው ቢቀርቡ ተገቢ መሆኑን ማንሳቱ የሚደገፍ ሐሳብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበርም ይህንኑ ጥያቄ ለይቶ ለምክክር ኮሚሽኑ ለምክክር እንዲቀርብ ማድረጉ አገራዊ የሙያ ግዴታውን እንደተወጣ ተደርጎ የሚያስመሠግነው ዕርምጃ ነው፡፡ በተለያዩ ወቅቶች፣ በተለያዩ መድረኮች፣ ስለአንድ ጉዳይ ምንም ሳይነጋገሩ አንድ ዓይነት ጥያቄዎችን (ሐሳቦችን) ማንሳት አይደንቅም?
በስንታየሁ ገብረ ጊዮርጊስ
‹‹ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩ መግባባት አለን?›› በሚል ርዕስ በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) በሪፖርተር ዕትም ቅጽ 29 ቁጥር 2528 ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. የተጻፈውን ጽሑፍ አነበብኩት፡፡ የኢትዮጵያዊነት ጠንካራ መለኪያ ሊሆኑ ከሚችሉ ስሜቶች መካከል ብዙዎች የተንፀባረቁበት ጽሑፍ ነው፡፡
ደምስ (ዶ/ር) በጽሑፉ ውስጥ የገለጻቸውን በርካታ ነጥቦች ሳነብ ለውስጤ የተሰማኝ ነገር ቢኖር፣ ኢትዮጵያዊነት ሰዎች ለአፍአዊ ፈሊጥ ሲባል የሚያነሱትና የሚጥሉት የማንነት መገለጫ መሆን እንደሌለበት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከውስጥ እምነታችን መንጭቶ፣ በተለያዩ መገለጫዎች ወደ ውጪ የሚገነፍል የአገር እምነት/ስሜት ነው፡፡ ከኢትዮጵየዊ/ት ወላጆች ኢትዮጵያ ውስጥ በመወለድም ይሁን በዜግነት እናግኘው፣ ኢትዮጵያዊነት የአገርንና የዜግነትን እምነት ልብ ውስጥ ማስረፅን ይጠይቃል፡፡
‹‹የአዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ማኅበር›› የአንደኛ ዓመት ምሥረታውንና የመጽሔት ምረቃ ለማክበር፣ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል አንድ በዓል አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚሁ በዓል ላይ እኔም በተጋባዥነት ተገኝቼ ነበር፡፡ የ‹‹አዎንታዊ አስተሳሰብ ለሕዝባዊ ዕድገት›› በሚል ርዕስ የተካሄደው ጥሩ የፓናል ውይይት የተመራው በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) አመቻችነት (ሞደሬተርነት) ነበር፡፡ በውይይት ወቅት ከተሳታፊዎች መካከል ከተነሱ ጥያቄዎች፣ ‹‹ኢትዮጵያ የምንላት የቷን ነው?›› ‹‹ኢትዮጵያዊስ ማነው?›› የሚሉ ሐሳቦች እንደነበሩ አድምጫለሁ፡፡ በወቅቱ ጥያቄው አስገርሞኝ እንደነበር አልሸሽግም፡፡ ዛሬም እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ይጠየቃል? በማለት ምክንያቶቹን በውስጤ ሳወጣና ሳወርድ እንደነበር አልዋሽም፡፡
ጥያቄዎቹ የገረሙኝ፣ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሲጠየቁ የነበሩ መሆናቸውን ሳስብ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን የመጠየቂያ ጊዜው ያለፈ ይመስለኝ ነበር፡፡ የተሳሳትኩት እኔ ነኝ፡፡ አሁንም ጥያቄዎቹ ሕይወት ዘርተው አሉ፡፡ ይሁን እንጂ በውይይቱ ወቅት ጥያቄዎቹን ያነሳቸውን ተሳታፊ በየትኛውም መለኪያ ካለፉ ጊዜያትና በወቅቱ ከሚገኙ ማናቸውም ቡድን ጋር የመፈረጅ ዓላማ በውስጤ የለም፡፡ ጥያቄዎቹን መጠየቁ አግባብ አልነበረም የሚል አቋምም የለኝም፡፡ እንኳንም ጥያቄዎቹን ለውይይት አቀረባቸው፡፡ የወቅቱን እውነት አጥርተን ለማየት እንድንችል ጥያቄዎቹን በውይይቱ ወቅት ማንሳቱ ያስመሠግነዋል፡፡ ብዙዎቻችን ልንረሳቸው የተቃረቡትን ጥያቄዎች ነበር ተሳታፊው ያነሳው፡፡ ጥያቄዎቹን አስመልክቶ፣ ወደኋላ መለስ ብዬ ታሪካዊ አነሳሳቸውን እንድዳስስ ውስጤን የኮረኮሩብኝ መሆናቸውን ግን መግለጽ እወዳለሁ፡፡
ስብሰባው የአዎንታዊ አስተሳሰብን ለአገርና ሕዝብ ዕድገት ለማዋል ያለመ ስለነበር፣ አዎንታዊነትን ለመገንባት አሉታዊ የሆኑ መነሻዎችን ሳይሸሹ አብሮ ማየት አስፈላጊ መሆኑን ማመን ይጠይቃል፡፡ አሉታዊነትን ወደ አዎንታዊ አስተሳሰብ መለወጥ ተገቢ መሆኑንም ማጤን አንድ ዕርምጃ ወደ ፊት ለመራመድ መቻል ነው፡፡ አዎንታዊ የአስተሳሰብ መስመርን መገንባት ለአገር ዕድገት፣ ብልፅግናና ሰላም ይጠቅማል፡፡ ለዚህ ሲባል ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄ ማስተናገድና መወያየት መልካም ነው፡፡ ጉዳዩን የማየው ከዚያ አመለካከት አኳያ ብቻ መሆኑ ይታወቅልኝ፡፡
ከላይ የገለጽኳቸው ጥያቄዎች ጉዳይ በውስጤ በመብላላት ላይ እንዳለ፣ ሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢሳት ቴሌቪዥን የማታ ዜና ዕወጃ ላይ በኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ምክትል ሊቀመንበር ሽመልስ አበበ የተሰጠ አጭር መግለጫን አደመጥኩ፡፡ መግለጫው የመምህራን ማኅበሩ መሠረታዊ ያላቸውን 13 አጀንዳዎች በቅደም ተከተል ለይቶ፣ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ያስረከበ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ከአጀንዳዎቹ በመጀመርያ ተርታ ከተሠለፉት መካከል ዋና በመሆን የተቀመጠው ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት›› የሚለው ዕሳቤ እንደሆነ አጽንኦት ተሰጥቶበታል፡፡ የአጀንዳው ግንባር ቀደም ሆኖ መቅረብ ለምን እንደሆነም በአጭሩ ተገልጿል፡፡ በመግለጫው ውስጥ የተነሱትን ሌሎች አጀንዳዎች ማንሳት ለጊዜው አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡
ቀደም ሲል በሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ‹‹የአዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ማኅበር›› የአንደኛ ዓመት ምሥረታና የመጽሔት ምረቃ በዓል ውይይት ወቅት ‹‹ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን›› አስመልክቶ ከተሳታፊ ተነስቶ የነበረው ጥያቄ በደምስ (ዶ/ር) ‹‹ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩ መግባባት አለን?›› በሚል ርዕስ በሪፖርተር ጋዜጣ የቀረበው ጽሑፍና ሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ደግሞ በኢሳት ቴሌቪዥን የማታ ዜና ዕወጃ ላይ በኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር የአጀንዳ መለየት ሒደት ላይ ‹‹ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን›› ተንተርሶ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በአንደኛ ደረጃ የቀረበው ጥያቄ ተመሳሳይነት ያላቸው መሆኑ አስደንቆኛል፡፡ ይህ ማለት ‹‹ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት›› በአገራዊ ምክክሩ ወቅት በአጀንዳነት ቀርበው፣ ሕገ መንግሥታዊ ትኩረት የተቸረውን ግልጽነት ማስረፅ ወይም የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ የሚያስፈልግ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይታመንበታል ማለት ነው፡፡ ለእኔም ጽሑፍ መነሻና ማጠናከሪያ የሆኑኝ እነኚሁ ግጥምጥሞሽ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን አስመልክቶ ጥያቄዎቹ ዛሬ ላይ ለምን ሊነሱ ቻሉ? በማለት ሳሰላስል፣ አንዳንድ የታሪክ ዳራዎችን ማንሳት ተገቢ መሆኑ ተሰማኝ፡፡ ሁሉም ነገር መነሻና መድረሻ አለው፡፡
ኢትዮጵያ አሁን በምናውቃት ይዘቷ (ስፋትና ርዝመቷ) ከመታወቋ በፊት ሰፊና ትልቅ አገር እንደነበረች በታሪክ ተገልጻ አንብበናል፣ ኖረንባታል፡፡ በተለያዩ ዘመናት ያየናቸው ዳር ድንበሯን ገላጭ የሆኑ ካርታዎቿም ምስክሮች ናቸው፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ቀደም ባሉ ዓመታት የኢትዮጵያ ድንበር በሰሜን ቀይ ባህር፣ በምሥራቅ ጂቡቲና ሶማሊያ፣ በደቡብ ኬንያና በምዕራብ ደግሞ ሱዳን እንደነበሩ ሁላችንም አምነን የተቀበልነው የአገራችን ካርታ ነበር፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ኤርትራ ስትገነጠል፣ አሁን የሚታየው የአገሪቱ ካርታ ሰሜናዊ ድንበሯን ኤርትራ ድረስ በመገደብ ከቁመቷ (ከአጠቃላይ ስፋቷ) ቀንሶ ወስኗታል፡፡ ያንንም አምነን በመቀበል ዛሬን በአንድነት እየኖርን ነው፡፡ አንድ አገር ይሠራል ይሰፋል፣ ይጠባል፣…፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ማናት?›› ለሚለው ጥያቄ መልስ ከሚሆናት ማስረጃ አንዱ መልክዓ ምድራዊ ገጽታዋ ነው፡፡ መልክዓ ምድራዊ ገጽታ ብቻውን የአንድ አገር መታወቂያ ላይሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹ኢትዮጵያ ማን ናት?›› ለሚለው ጥያቄ መጀመርያ መልስን የሚሰጡት በውጫዊ ገጽታዋ የምትገለጥበት መልከዓ ምድሯ፣ ሕዝቧና በውስጧ አቅፋ የያዘቻቸው የልማት ፀጋዎቿ ጭምር ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን በተለያዩ ገጽታዎቿ መግለጽ ይቻላል፡፡ ያም የውስጥ እምነትን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ኢትዮጵያዊነት የሚታዩ፣ የሚጨበጡና በልብ ውስጥ ጎልተው የሚቀረፁ እምነቶች ናቸው፡፡ ካለ እምነት የሚታየው አይታይም፡፡
ኢትዮጵያ በውስጧ ብዙ ብሔረሰቦችን አቅፋ የያዘች አገር/ብሔር ናት፡፡ አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ሲል፣ የአገሩን መልከዓ ምድራዊ ገጽታዋን በአዕምሮው ስሎ የኢትዮጵያዊነት ባህሪዎቹን (እሴቶቹን) በልቡ በመጻፍ በአፉ አጉልቶ ይመሰክርላታል፣ እምነቱን ይገልጥበታል፡፡ ያንን ይዞ ነው ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ እምነቱን በራሱና በሌሎች ውስጥ የሚያሰርፀው፣ ወይም አይደለሁም በማለት ራሱንና ሌሎችን የሚያገልበት/የሚያርቅበት፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው ደግሞ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው፡፡ ብዙ የተወሳሰበ ነገር የለውም፡፡
በዜግነት ለመኩራት በርካታ ጉዳዮች አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ዕሙን ነው፡፡ የኢትዮጵያዊ የልቦና ውቅሩ በአዕምሮው ከሳላት ኢትዮጵያ ምንነትና እሱን ከመሰሉ ሌሎች ዜጎች ባህሪያት ጋር (ከባህሉ፣ ቋንቋው፣ ሃይማኖቱ፣… ካደገበት ቀዬው፣…) የተሳሰረ ማንነት አለው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ያንን ሁሉ ይይዛል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያዊ ማንነት ነው፡፡ ያንን ሳያምኑ መልከዓ ምድራዊ ገጽታዋን ብቻ ዓይቶ ወይም በታሪኳ ተማርኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት የይስሙላ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ የሁሉም ሕዝብ ፀባያት ከነባህላቸው/ልማዳቸውና ቋንቋዎቻቸው ጋር የሚገለጹባት ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሔረሰቦች የሚገኙባት አገር (ብሔር) ናት፡፡ ኢትዮጵያ ብዝኃነት (Diversity) ያላቸው ብሔረሰቦች ያሉባት አንድ አገር (ብሔር) ናት፡፡ የዓድዋን ድል የተጎናፀፈችው በብዝኃነቷ ውስጥ ነው፡፡ በአገሪቱ የነበሩትና ያሉት የሁሉም ብሔረሰብ ትውልዶች አንዱ የሌላው አካል የሆነና አብሮ በመኖር የቀጠለ፣ አዳጊ፣ ተለዋዋጭና ተከታታይ የሆኑ ኅብር ያላቸው የአንድ አገር ዜጎች በመሆን የሚገለጡ ናቸው፡፡ ይህም እምነትን ይጠይቃል፡፡
ኢትዮጵያን በተሻለ ማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ፣ በሕዝቧ ብዝኃነት (Diversity) ውስጥ የሚገኙትን እንደ አበባ የፈኩ ባህሪያት (አንድነትና ልዩነት) በማየት ብቻ መደነቅ ይችላሉ፡፡ አንድ አያትና ቅም አያት (Ancestors) ያሏቸው ሕዝብ እንኳን በብዝኃነት ውስጥ ተዋውጠው የዘር ግንዳቸውን ማንነት እስከሚያጡት ድረስ የተዋሀዱባት አገር ናት፡፡ በመዋሀድ ሒደት ውስጥ ለሺሕ ዓመታት የዘለቀች አገር መሆኗ ይሆን ኢትዮጵያዊ ማነው? ኢትዮጵያስ ማን ናት የሚያሰኛት?
ኢትዮጵያ ውስጥ ለብዙ ሺሕ ዓመታት የተለያዩ ብሔረሰቦች በራሳቸው ቋንቋ ሲጠቀሙና ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓትንም ሲከተሉ የኖሩ ናቸው፡፡ ቋንቋና ባህላቸውን ጠብቀው የኖሩት አንዱ ለሌላው በማሰብ፣ በመደጋገፍና በመተዛዘን (Compassion) መልካም የግንኙነቶች እሴቶችን አዳብረው በመኖራቸው ነው፡፡ ይህንን በማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ብሔረሰቦች አኗኗር ውስጥ ማየት የሚቻል ነው (ሲዳማ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ትግሬ፣ አፋርና ሶማሌ…)፡፡ አገሪቱ በምዕተ ዓመታት የሚቆጠሩ፣ የተለያዩ ባህላዊ የአስተዳደር ልምዶችና ሥነ ልቦናዊ ውቅር ባላቸው ብሔረሰቦች የተሞላች ናት፡፡ ይህ ይሆን ኢትዮጵያዊ ማነው? ኢትዮጵያስ ማን ናት የሚያሰኛት?
ከነበሩትና ካሉት በርካታ የብሔረሰቦች ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ የአስተዳደራዊ አወቃቀር (ፖለቲካዊ) እና መልክዓ ምድራዊ ግንኙነቶች አንፃር የአገሪቱ አንድነት ታሪክ የተወሳሰበ ነው፡፡ ታሪኩ የአስተዳደር (ፖለቲካ) ሥልጣንን በመረከብ ተፅዕኖን ለመፍጠር፣ አካባቢን ለማስፋት፣ ለሀብት ክፍፍል (ግብር በመሰብሰብ ጭምር) እና ለባህል የበላይነት በተደረጉ ግጭቶች የተሞላ ነው ሊባል የሚችል ነው፡፡ ግጭቶቹ በአንድ ወገን እርስ በርስ የሚፎካከሩና እንደባላንጣ የሚተያዩ (የአንድ ብሔረሰብ አባላት ጭምር) የጦር አበጋዞች/አለቆች (Warlords) የያዙትን መሬት፣ ሀብትና የሰው ኃይል በመቀማማት (አንዱ ሌላውን በማስገበር) የሚገለጡ ነበሩ፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ አገሪቱ በምሥራቅ አፍሪካ ባላት ስትራቴጂካዊ የመሬት አቀማመጥና የተፈጥሮ ሀብት (ለምሳሌ ግብፅ የዓባይን ውኃ በመሻት፣ ቱርክና ጣሊያን የቀይ ባህርን በመሻት) የተነሳ፣ ከውጭ ኃይሎች የሚሰነዘሩ ወረራዎችን ለመቀልበስ በሚደረጉ በርካታ ጦርነቶች በጋራ የመዋደቅና የአገርን ሉዓላዊነት በማስከበር የሚገለጡ ነበሩ፡፡ ይህ ሁኔታ ጎልቶ መታየቱ ይሆን ኢትዮጵያዊ ማነው? ኢትዮጵያስ ማን ናት የሚያሰኛት?
ሁሉም ዓይነት ግጭቶች (የውስጥና የውጭ) የአገሪቱን ሀብት በጦርነት በማመናመን ድህነት ጠንክሮ እንዲቆይና፣ በኢኮኖሚ ደካማ አገር ሆና እንድትኖር አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አገሪቱ ሀብቴን ላልማ/ልጠቀም ብላ ተባብራ ስትነሳ ደግሞ፣ ጥቅማቸው የሚቀርባቸው የመሰላቸው የውጭ ጠላቶቿ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ የጦርነት ድግስ እየደገሱላት በሰላም ዕጦት ሲያምሷት ምዕተ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዛሬም የእርስ በርስ የግጭት ታሪኳን ለመቀየር ገና እየዳኸች የምትገኝ አገር ናት፡፡ ይህ ይሆን ኢትዮጵያዊ ማነው? ኢትዮጵያስ ማን ናት የሚያሰኛት?
በየትኛውም የመልከዓ ምድር ገጽታዋ ተሥላ ብትቀርብም፣ ኢትዮጵያ አገር ሆና ከተመሠረተች በርካታ ምዕተ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዓለም ደረጃ ከምትታወቅበት የዘመናት የአገርነት እውነታ በኋላ፣ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ የቷ ነች? ኢትዮጵያዊስ ማነው? በማለት ትርጉምን የመፈለግ ሒደት ስለደነቀኝ ነው በሪፖርተር ጋዜጣ የቀረበውን የደምስን (ዶ/ር) ጽሑፍና በኢሳት ቴሌቪዥን ላይ የተላለፈውን የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበርን የአጀንዳ ይዘት መግለጫ መነሻ አድርጌ በጥያቄዎቹ ላይ ሐሳቤን ለማስፈር የተነሳሳሁት፡፡ ያቀረብኩት ሐሳብ የእኔ እምነት ነው፡፡
እነዚህ ጥያቄዎች ለምን ዛሬ ሊነሱ ቻሉ? ጥያቄዎቹን ሲያነሷቸው የነበሩት እነማን ነበሩ? ጥያቄዎቹን ለምን ዓላማ ያነሷቸው ነበር? የሚሉትን ሳስብ፣ 50 እና 60 ዓመታት በትዝታ ወደ ኋላ ለማጠንጠን ተነሳሁ፡፡
እነዚህ ጥያቄዎች ጎልተው መነሳት የጀመሩት ‹‹የራስን ዕድል በራስ መወሰን›› በሚል የሶሻሊስት መርሆ መቀንቀን ከተጀመረበትና አንዳንድ ‹‹ብሔረሰቦች›› ራሳቸውን እንደ ‹‹ብሔር›› (አገር) በመቁጠር ኢትዮጵያን እንደ ‹‹ቅኝ ገዥ›› መድበው ‹‹የብሔር ንቅናቄ›› ከጀመሩ በኋላ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በዚህ ረገድ በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ የነፃ አውጪነት ትግልን የጀመሩት የኤርትራ ነፃ አውጪ ድርጅትና ኦነግ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ በወቅቱ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች (እንደ ኦብነግ የመሳሰሉ ሌሎችን መጥቀስ ሳያስፈልግ) ኢትዮጵያን እንደ ‹‹ቅኝ ገዥ›› በመመልከት፣ ኢትዮጵያዊ አለመሆናቸውንና ከኢትዮጵያ ተገንጥለው አገር ለመሆን ትግልን የጀመሩ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ዛሬ ስለኢትዮጵያ ያላቸውን አቋም ከተግባራቸው ከመለየት በስተቀር፣ ሌላ የማወቂያ መንገዱ የለኝም፡፡
እነዚህ ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› አራማጆች ራሳቸውን የቻሉ ‹‹ብሔሮች›› (አገሮች) እንደነበሩና ኢትዮጵያ በምትባል ‹‹ቅኝ ገዥ አገር›› የተዋጡ/የተጠቀለሉ መሆናቸውን ከማመን ተነስተው ጥያቄዎቹን ይጠይቁ ነበር፡፡ ዓላማቸው ራሳቸው አገር (ብሔር) እንዲሆኑ መሥራት/መታገል ስለነበር፣ ያ እንዳይሆን ከሚታገሏቸው መንግሥታት (የዘውድ፣ የደርግና የኢሕአዴግ) ጋር በትጥቅ ታግለዋል፡፡ ወቅቱም (በተለይ የዘውዱና የደርግ) ያንን ያበረታታ ነበር፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን እንደ አገር (ብሔር)፣ እነሱን ደግሞ የአገሪቱ አንድ አካል (ብሔረሰብ) ወይም ዜጋ አድርገው መመልከት አልፈለጉም፡፡ ጥያቄዎቹ የተነሱት ከመገንጠል (‹‹የራስን ዕድል በራስ መወሰን››) ፍላጎት ነበር፡፡ ኤርትራ የመገንጠል ሐሳቧን አሳክታ አሁን አገር (ብሔር ብሔረ ኤርትራ) ሆናለች፡፡ ሌሎች ደግሞ አገር ሆኖ የመዋቀር ፍላጎታቸውን በጥያቄዎቻቸው አማካይነት፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በሚያምኑ ዜጎች ውስጥ ለማስረፅ ሠርተዋል፡፡ ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› ከግቦቹ አንዱ ራስን የቻለ አገር መሆን፣ መፍጠርና ማዋቀር ነው፡፡
ሁሉም ራሱን የቻለ አገር ቢሆንና በሰላም ተከባብሮ መኖር ቢቻል ምንኛ መታደል ነበር? እውነቴን ነው፡፡ ግን ሰላም መሆን አይቻልም፡፡ ሰላምና ብልፅግና አገር በመሆን ብቻ አይመጣም፡፡ ኤርትራ አገር ሆናለች፡፡ ግን ከጎረቤቶቿ ጋር ሰላም ናት? ውስጣዊ ሰላምስ አላት? በይፋ ባይነገርም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ራሷን የቻለች አገር በመሆኗ በውስጣቸው ቅሬታን ያዘሉ (ባልተገነጠልን ነበር የሚሉ) ሚሊዮኖች እንዳሉባት ይሰማል፡፡ ኢትዮጵያ ሚስጥር ናት፡፡ አንዳንዶች ዛሬም ባትገባቸው አይደንቅም፡፡
አገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ ልዩነቶችን አጥብቦ፣ በውይይት ስምምምት (Consensus) ላይ ተደርሶ፣ የአገርን ሰላምና አንድነት ማስፈንና የሕዝብን አንድነት መጠበቅ ዓላማው ከሆነ፣ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ጥያቄዎች ላይ በቅድሚያ አቋም መያዝ ወሳኝ መሆኑን ከደምስ (ዶ/ር) ጫንያለው ጽሑፍና ከኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አጀንዳ አቀራረብ ጭብጥ ላይ ተረድቻለሁ፡፡
በሪፖርተር ጋዜጣ ዕትም ውስጥ በደምስ (ዶ/ር) እንደተገለጠው፣ ሕገ መንግሥቱ ስለዜግነት እንጂ ኢትዮጵያ ማን ናት? ኢትዮጵያዊስ ማነው? ለሚሉት ጥያቄዎች የማያሻማ መልስ ያለው አይመስልም፡፡ አለው? ካለው ለመታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጠያቂዎች ከሕገ መንግሥቱ ይዘትና ባህሪ ብቻ እንኳን ተነስተው (ሌሎች ፖለቲካዊ እንደምታ ያሏቸውን ትንታኔዎች በመተው) ጥያቄዎቹን ቢጠይቁ አይፈረድባቸውም፡፡ ማንም ቢሆን ግልጽ ያልሆነለትን የራሱን እምነት እንኳን ይጠይቃል፡፡ ምርምር ከጥያቄ ይነሳል፡፡ ምን ጊዜም ጥያቄ ጥሩ ነው፡፡
አንድ በኢትዮጵያ ምድር የተወለደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ ምን ያህል እምነቱ ከውስጡ ቢሟጠጥበት ነው ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በአሁኑ ወቅት የሚጠይቀው? በማለት መብሰልሰልም ክፋት የለውም፡፡ አንድ ዜጋ ለኢትዮጵያ ጥቅም ለመቆም በኢትዮጵያዊነቱና በአገሩ ኢትዮጵያ ላይ የኢትዮጵያዊነት እምነት ሊኖረው የሚገባ መሆኑ አሌ የሚባል ነገር የለውም፡፡ ደምስ (ዶ/ር) ያንን አጢኖ፣ በአገራዊ ምክክሩ ወቅት ጥያቄዎቹ እንደ ቀዳሚ አጀንዳ ተደርገው ቢቀርቡ ተገቢ መሆኑን ማንሳቱ የሚደገፍ ሐሳብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበርም ይህንኑ ጥያቄ ለይቶ ለምክክር ኮሚሽኑ ለምክክር እንዲቀርብ ማድረጉ አገራዊ የሙያ ግዴታውን እንደተወጣ ተደርጎ የሚያስመሠግነው ዕርምጃ ነው፡፡ በተለያዩ ወቅቶች፣ በተለያዩ መድረኮች፣ ስለአንድ ጉዳይ ምንም ሳይነጋገሩ አንድ ዓይነት ጥያቄዎችን (ሐሳቦችን) ማንሳት አይደንቅም?
ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አስመልክቶ ትውልዱ ጥያቄዎች አሉት፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች አሉታዊ ናቸው በማለት ወደ ጎን መግፋት አይቻልም፡፡ በመረጃዎች ላይ ተመሥርቶ፣ ምክንያታዊነት በጎላበት መድረክ በመወያየትና በመመካከር አዎንታዊ ስምምነት ላይ መድረስ ለአገር ልማት፣ ዕድገትና አንድነት ይበጃል፡፡
ደምስ (ዶ/ር) በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ፣ ‹‹ኢዮጵያዊ ማን ነው/ናት? በምክክሩ መግባባት አለን?›› በማለት ጠይቆ ካቀረበው ጽሑፍና የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ለምክክር ኮሚሽኑ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን አስመልክቶ በምክክሩ ወቅት ትኩረት እንዲያገኝ በኢሳት ቴሌቪዥን መግለጫው በአጀንዳነት ቀርፆ ካስረከበው ግብዓት የተረዳኋቸው ዓበይት ቁምነገሮች አሉኝ፡፡ ከሁለቱም ጠንካራ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲፈጠር፣ እንዲሁም አገራዊ ምክክሩ አሉታዊ አመለካከቶችን ወደ አዎንታዊ እሴቶች በመቀየር የተሳኩ ውጤቶችን እንዲያስመዘግብ ያላቸውን መልካም ምኞት ተገንዝቤአለሁ፡፡ ያንን ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ ለእኛም፣ ለኢትዮጵያም ሰላም!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በእርሻ ኢኮኖሚክስ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኤኮኖሚ ፖሊሲና ፕላኒንግ፣ እንዲሁም በባህሪያዊ ኢኮኖሚክስ (Behavioral Economics) የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርት በጅምር የተቋረጠ፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ከ25 ዓመታት በላይ በተለያዩ ኃላፊነቶች ከማገልገላቸውም በላይ፣ የተለያዩ መጻሕፍት ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው abune5234@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡
ከሪፖርተር የተወሰደ