መግቢያ
በአገራችን በግልም ይሁን በሽርክና ማህበራት ተደራጅተው የድለላ ሥራን የሚሰሩ ደላሎችን ማየት የተለመደ ነው። እነዚህ ደላሎች በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በተለይም በንግድ እንቅስቃሴው ውስጥ ሻጭ እና ገዥን፣ ቀጣሪና ተቀጣሪን፣ አምራች እና አከፋፋይን፣ አከራይና ተከራይን ወዘተ ድልድይ ሆኖ በማገናኘት አጠቃላይ እንቅስቃሴውን በማሳለጥ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ በዚህ ጽሁፍ የድለላ ሥራን ምንነት፣ የድለላ ሥራ የሚሰሩ ሰዎች ያላቸውን መብትና ግዴታ እንዲሁም በህግ የተቀመጡ ቅድመ-ሁኔታዎችን አክብሮ አለመስራት የሚያስከትለውን ተጠያቂነት እንዳስሳለን።
የድለላ ምንነት
ደላሎች ማለት ውል የሚዋዋሉ ሰዎችን በተለይም እንደ ሽያጭ፣ ኪራይ፣ ኢንሹራንስ፣ የማመላለሻ ውል የመሳሰሉ ውሎች የሚዋዋሉ ሰዎች ፈልገው ማገናኘትና ማዋዋልን ራሱን የቻለ የሙያ ተግባራቸው አድርገው ጥቅም ለማግኘት የሚሰሩ ሰዎች ወይም ይህንኑ የደላላነት ሥራ የሚሰራ የንግድ ማህበራት እንደሆኑ በአዲሱ የንግድ ህግ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 አንቀጽ 54(1) ትርጓሜ ተሰጥቶታል። በተጨማሪም የህጉ አንቀጽ 54/2 ስር ደላሎች አስማሚ ሆነው የሚያስፈጽሟቸው ውሎች ዓይነትና ግብ ወይም የሚያገናኟቸው ሰዎች ማንነት ወይም ሁኔታ ሳይታይ ደላሎች ነጋዴዎች እንደሆኑ ደንግጓል፡፡ ደላሎች ነጋዴ ተብለው እስከተቆጠሩ ድረስ ደግሞ አንድ ነጋዴ ሊያሟላቸው የሚገቡ በህግ የተመለከቱ መስፈርቶችን ማሟላት ይኖርባቸዋል ማለት ነው።
በአጠቃላይ በበርካታ ጉዳዮች ፈላጊና ተፈላጊን የማገናኘት ሥራን የሚሰሩና ይህንኑ ሥራ የመተዳደሪያ ሙያ አድርገው የሚቆጥሩ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ደላላ ተብለው በነጋዴነት እንደሚቆጠሩ ከህጉ አጠቃላይ መንፈስ መረዳት ይቻላል።
ህጉ ይህን ይበል እንጂ በተግባር አንዳንድ ግለሰቦች “የኮሚሽን ሥራ” በሚል ፈቃድ አውጥተው ነገር ግን በህጉ የድለላ ሥራን አስመልክቶ የተዘረዘሩትን ተግባራት ሁሉ የሚሰሩ ስለመኖራቸው የሚታወቅ ነው። ይሁንና በህጉ አንቀጽ 58 እና ተከታዮቹ አንቀጾች ከሰፈረው እንደምንረዳው “ኮሚሽን ተወካዮች” አገልግሎታቸው ስለ ወካይ ሆኖ በራሱ ስም ሸቀጦችን ወይም ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን የሚገዛ ወይም የሚሸጥ ወይም ስለ ወካይ ሆኖ በስሙ የመጓጓዣ ውሎችን የሚዋዋልን ሰው ወይም የንግድ ማህበር የሚመለከት እንጂ የድለላ ሥራን የሚመለከት አይደለም።
ለደላላ በህግ ስለተሰጡ መብቶች
ደላሎች በዋናነት የደንበኞቻቸውን የንግድ እንቅስቃሴ ችግሮች ገንዘብ እየተከፈላቸው የማቃለል ተግባር የሚያከናውኑ ባለሙያዎች ሲሆኑ ይህም ሙያቸው የራሱ የሆነ ህጋዊ መብትንና ግዴታን የሚያስከትል ይሆናል። ከነዚህ በህግ ከተቀመጡት መብቶች በዋናነት የሚጠቀሰው ደላላው ለሰጠው አገልግሎት የሚከፈለው ክፍያ ሲሆን በንግድ ህጉ አንቀፅ 57(2) መሰረት በልምድ የታወቀ ካልሆነ ወይም ሌላ ስምምነት ካልተደረገ በስተቀር የደላላውን አገልግሎት የጠየቀው ወገን አበሉን የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ይህ አበል በስምምነቱ የሚወሰን ወይም ባልተወሰነበት ጊዜ በልምድ መሠረት የሚቆረጥ ሲሆን ደላላው በተዋዋዮች መካከል አስማሚ ሆኖ ውሉን ካስጨረሰ ወይም ካዋዋለ በኋላ ውሉ ቢፈፀምም ባይፈፀምም ሊከፈለው እንደሚገባ በንግድ ህጉ አንቀፅ 57(1) ደንግጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከላይ እንደተብራራው ደላሎች በህጉ እንደ ነጋዴ የተቆጠሩ ስለሆነ ማንኛውም ነጋዴ ያለው መብቶችን የሚጠበቁላቸው ይሆናል።
የደላሎች ህጋዊ ሀላፊነቶች
የድለላ ሥራ የሚሰሩ ሰዎች በህጉ የተጣሉባቸው ግዴታዎች አሉ፡፡ ይኸውም፡-
• በንግድ ህጉ አንቀፅ 54(3) መሰረት በተለየ ሁኔታ በውላቸው ካልተገለፀ በቀር ተዋዋየችን ተክቶ ገንዘብ መቀበል ወይንም ማንኛውንም ወደ ተግባር የሚያስገባ እንቅስቃሴ ማድረግ የለበትም። ደላላው ለደንበኛው ወይም አገልግሎቱን ለጠየቀው ወገን ያሉበትን ግዴታዎች ተላልፎና ይልቁንም የደምበኛውን ጥቅም በሚጎዳ አኳኋን ለሌላ ሦስተኛ ወገን ጥቅም የሠራ እንደ ሆነ ወይም ደምበኛው ሳያውቅ ከሦስተኛው ወገን ክፍያ የተቀበለ እንደሆነ በንግድ ህጉ አንቀፅ 57(4) መሰረት አበል የማግኘት መብቱን ያጣል።
• በንግድ ህጉ አንቀፅ 55(1) መሰረት በልምድ የታወቀ ካልሆነ ወይም ሌላ ስምምነት ካልተደረገ በስተቀር ተዋዋዮቹ በጉዳዩ ውል ለማደረግ የተስማሙ እንደሆነ ደላላው ውሉ የሚደረግበትን ሁኔታ ለተዋዋዮች ሁሉ ወዲያውኑ ማስታወቅ አለበት፡፡
• በንግድ ህጉ አንቀፅ 56 መሰረት ደላላው በሁለቱም ወገኖች ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ኃላፊ ይሆናል።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ በአዲሱ የንግድ ህግ ደላሎች እንደ ነጋዴ የሚታዩ ሲሆን የሚያከናውኑት ሥራ ምንነትና ይህንን በማከናወን ሂደት ያላቸውን መብትና የተጣለባቸውን ግዴታ ያመላከተ እንደመሆኑ የድለላ ሥራ የሚያከናውኑ ሰዎች በህጉ መሰረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በየፍትህ ሚኒስቴር ንቃተ-ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ