የቃጠሎ አደጋ በሚነድ እሳት፣ በፈላ ውሃ፣ በእንፋሎት፣ በኬሚካል ወይም በጨረር አማካኝነት ሊፈጠር ይችላል። ነገር ግን በጣም የተለመደው የቃጠሎ ዓይነት በእሳት ቃጠሎ የሚደርሰው አደጋ ነው።
ቃጠሎው በሚያደርሰው ጉዳት ክብደትና ቅለት እንዲሁም በሚወሰደው የህክምና ዓይነት የእሳት ቃጠሎ አደጋ በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች የመጀመሪያ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ቃጠሎ ተብሎ ይመደባል፡፡
ሀ. የመጀመሪያ ደረጃ የቃጠሎ አደጋ ፡- ይህ የቃጠሎ አደጋ ቀላል የሚባለውና በቆዳችን የላይኛው ክፍል (ኢፒደርሚስ) ላይ የሚደርስ ነው። ቀላል ቃጠሎ ሰዎችን በቀን ተቀን ህይወታቸው በተደጋጋሚ የሚያጋጥማቸው ሲሆን በቆዳቸው የላይኛው ክፍል ላይ መጠነኛ ጉዳት ያደርሳል።
ይህ ቀላል ወይም የመጀመሪያ ደረጃ ቃጠሎ በአብዛኛው ህክምና የማያስፈልገው እና በራሱ የሚድንና ተጎጅው ላይ ትንሽ ህመም ከመሰማት ውጭ የከፋ ጉዳት አይኖረውም። ህመሙ ሲድንም በአብዛኛው ጠባሳና ምልክትም አይኖረውም።
የቃጠሎ ጉዳት የደረሰበት ቦታ ላይ ንፁህ ጨርቅ በቀዝቃዛ ውሃ ነክሮ መያዝ የመቃጠል አደጋ የደረሰበትን የሰውነት ክፍል ለማስታገስ ያግዛል። ከዚህ በተጨማሪ ጉዳቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች መቆጠብ ይመከራል።
ለ. ሁለተኛ ደረጃ የቃጠሎ አደጋ፡- ይህ የቃጠሎ አደጋ የመጀመሪያውንና መካከለኛውን የቆዳችንን ክፍል ጭምር የሚጎዳ ሲሆን ጉዳት የደረሰበት ቦታ ውሃ የመቋጠር፣ የቆዳ መላጥ ወይም መገሽለጥ፣ ከፍተኛ የሆነ የህመም ስሜት ወዘተ የሚያስከትል ነው።
ይህ የቃጠሎ ዓይነት በሚያደርሰው ጉዳት ከአንደኛ ደረጃው ከፍ ያለ በመሆኑ ተጎጂው ህክምና ቦታ እስኪደርስ ድረስ በርካታ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች መውሰድን ይጠይቃል። ከዳነ በኋላ ጠባሳና ምልክት ሊኖረው ይችላል።
ሐ. ሶስተኛ ደረጃ ቃጠሎ፡- ይህ የቃጠሎ አደጋ በሚያደርሰው ጉዳት ከሁለቱ እጅግ የከፋውና እስከ አጥንት የሚዘልቅ ጉዳት ያስከትላል። አለፍ ሲልም እስከሞት ያደርሳል። ቃጠሎው የቆዳ መንጣት፣ የቆዳ መጥቆርና መሻከር የሚያስከትል በመሆኑ ከሌላ የሰውነት ክፍል ቆዳ በመውሰድ ጉዳት በደረሰበት ቦታ ላይ እስከመለጠፍ (ስኪን ግራፍቲንግ) የሚደርስ ህክምና ይደረግለታል።
የአደጋው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የሚደረግለት ህክምናም ውስብስብና ቀዶ ጥገና ጭምር ሊያስፈልገው ይችላል። ከዳነም በኋላ ጉዳቱ በጉልህ የሚታይና የተጎጂውን ህይወት እስከመለወጥ ሊደርስ ይችላል።
የእሳት ቃጠሎ ጉዳት ለደረሰበት ሰው የሚደረግ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ
• እሳት አደጋው ከተከሰተበት ቦታ ማራቅ ወይም ማውጣት ቀዳሚው ተግባር ነው
• ከእሳት አደጋው በምንርቅበት ወቅት መሮጥና አብዝቶ ከመንቀሳስ መታቀብ (እሳቱ የበለጠ እንዳይባባስ)
• እሳቱን ለማጥፋት መሬት ላይ መንከባለል ወይም በብርድ ልብስ መጠቅለል
• ቃጠሎ የደረሰበትን አካል በቀዝቃዛ ውሃ በተነከረ ንጹህ ጨርቅ ለ30 ደቂቃ መያዝ
• ባዕድ ነገር (አፈር፣ ሊጥ፣ ወተት ወዘተ) በቁስሉ ላይ አለማድረግ
• በተቃጠለው አካል ላይ የተጣበቀ ልብስ ካለ አለማላቀቅ (መድማትና ቅስለቱ እንዳይባባስ)
• በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም መውሰድ ይገባል
ምንጭ፡- አሜሪካን አካዳሚ ኦፍ ደርማቶሎጂ አሶሴሽን፣ ናሽናል ላይብራሪ ኦፍ ሜዲሲን፣ ናሽናል ሄልዝ ሰርቪስ
በቴዎድሮስ ሳህለ walta