“ሻዕቢያ እናቴን ገድሏል” ስትል የምትናገረው የአውሮፓ ነዋሪ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው። “ኤርትራዊ ነሽ” ምላሿ “አዱ ገነትስ”የሚል ነው። “እኔ አዲሳ አበባ ያደኩ፣ የኢትዮጵያን ጡቷን የጠባሁ፣ እንዳሻኝ ቦርቄ ያደኩ፣ ፖለቲካ የማይገባኝ ልጅ ነኝ” ትላለች። ከትህነግ ጋር በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ኤርትራዊያን በጅምላ ሲጋዙ እሷ አውሮፓ ነበረች። እናቷ አስመራ እየኖሩ ሳለ ታመው ወደ አውሮፓ ለህክምና እንዳይመጡ ሻዕቢያ ከልክሏቸው ህይወታቸው አልፏል። ሃኪም የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ መክሮ የነበረ ቢሆንም ሻዕቢያ “አይሆንም” በማለቱ አልተቻለም። ብዙ ተሞከረ አልሆነም። እናት ሞቱ።
ሻዕቢያ እናቷ ላይ ክልከላ የጣለበት ቁልፍ ጉዳይ እንዲህ ነው ” ሻዕቢያ በረሃ እያለ አዲስ አበባና በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ንብረት በደጋፊዎቹ ስም ይገዛ ነበር። በተለይም የጭነት መኪና ገዝቶ መነገድ የተለመደ ነበር። በዚሁ ሂሳብ አባቴ ሁለት ኤኔትሬ የጭነት መኪና ከአምቼ አወጣ። ክፍያው የተፈጸመው ከሻዕቢያ ኪስ ቢሆንም ንብረትነቱ የሚታወቀው በአባቴ እንደሆነ ነበር። የሰፈራችን ሰዎች ሁለት የጭነት መኪና እንዳለን እንጂ አባቴ ለሻቢያ እንደሚሰራ ሚስጢር ነበር” ትላለች መነሻውን ስታስረዳ።
” ምክንያቱን በማላውቀው ወይም ለእኔ ሚስጢር በሆነ መልኩ አባቴ ለሻዕቢያ ማስገባት የነበረውን ሃብት እንዳላስገባ እናቴ አስመራ እንደደረሰች ተነገራት። አባቴ ህይወቱ ያለፈው አዲስ አበባ ስለነበር፣ እሷም ምንም እንደማታውቅ ብታስረዳም ሻዕቢያ ሊቀበል አልቻለም። በዚህ ሳቢያ ቀጧት። አስረው ፈቷት። ባልሽ ገንዘብ በሚፈለገው መጠን ገቢ አላደረገም ብለው ከአስመራ እንዳትወጣ የቁም እስረኛ አደረጓት። በዚያው ህመሟ ጠንቶባት ህይወቷ አለፈ። ሻዕቢያ ማለት እንዲህ ነው። በነገራችን ላይ አብዛኞቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩት ከባድ መኪናዎች ታሪካቸው ተመሳሳይ ነው። ንግድ ቤቶችና …”
“አብረን በጉርብትና እየኖርን፣ አብረን መንፈሳዊ ጽዋና ዝክር እየጠጣን ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢ ናት ብለው እንደፈረዱባት፣ እንደፈረዱብን ሳስበው መፈጠሬ ያስጠላኛል። ወያኔና ሻዕቢያ በጋራ አዲስ አበባ ሲገቡ መትረየስና ክላሽ ከጓዳቸው እየመዘዙ ከበሮ የመቱባችሁ ጎረቤቶቻቸሁን አስቡ” ሲል ከዓመታት በፊት ከትቦ የነበር አንድ ዜጋ እንዳለው ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሻዕቢያ የሚመራው የኮንትሮባንዲስቶች ቡድን በገፍ ናቸው። ኢትዮጵያን እንዲያተራምሱ የሚታጠቁና የሚሰለጥኑ እልፍ ናቸው። ይህን ድርጊት ኤርትራዊያን አስመራም ሆነ አዲስ አበባ ያላችሁ ታውቁታላችሁ። በኮንትሮባንድና ጽንፈኞችን በማደራጀት ሚሽን የተቀበላችሁ ደግሞ ይበልጥ ትረዱታላችሁ። ኢትዮጵያዊያንም ያውቁታል። ይረዱታል። እያዩዋችሁ ነው። እንደቀድሞ የሚሸወዱበት ጊዜ አይኖርም።
የሻዕቢያም ሆነ አፍቃሪዎቹ ” ኤርትራ የግል፣ ኢትዮጵያ የጋራ የምትታለብ ላማችን” የሚል ያረጀና ያፈጀ እሳቤ አላቸው። ይህ አቅምን ያለማገናዘብ እሳቤ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያዊያንን አማሯል። ሲፈጠር ጀምሮ ኢትዮጵያ ላይ አማጺ ሲያደረጃና ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ኮንትሮባንድና ዝርፊያ ሲፈጽምባት የኖረው ሻዕቢያ፣ አሁን ላይ “መስመር ያዝ” በመባሉ ለሶሶት አስርት ዓመታት ተዘግቶ የተከፈተውን የአየር በረራ ዳግም ዘግቶ ህዝቡ ላይ ቆልፏል። ቀርቅሯል። ከርችሟል። ህዝብን ለማወናበድ ስመ ጥር አየር መንገዳችንን በስልቻ፣ በተራ የሽሮና በርበሬ፣ የቂጣ ቦርሳ ጠፋ ስም ከሷል።
በኤርትራ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ያለ ምርጫ፣ ህገመንግስትና ነጻ ፕሬስ፣ እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲ በአፈና ስልጣን ላይ ያለው የኢሳስያስ አገዛዝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያቆም ማዘዙን ሰሰማ “ለምን?” ስል ጠየኩ። ከዛም በገደምዳሜ ህዝብ ሲያማ፣ አንዳንድ አመራሮችም በጓሮ ሲናገሩ የሰማሁትና አሁን ላይ ሻዕቢያ እየጠጉመጠመጠ ያለውን መርዝ ወዴት ሊተፋው እንዳሰበ ስረዳ የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳት ወደድኩ።
“የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ በረራ ጀመረ” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቋርጦት የነበረው የአስመራ በረራ መጀመሩን ተከትሎ ይፋ በሆኑ የቪዲዮ መረጃዎች የተለያዩ ቤተሰቦች ከሁለት አስርት ዓመታት በሁዋላ ተገናኝተው ሲላቀሱ ማየት ስሜትን ይነዝር ነበር። ልጅና አባት ከረጀም አመታት በሁዋላ በአካል እንዲገናኙ ያደርገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈንዲሻ እየተረጨለት፣ እንደ ታቦት ዕልልታ የዘነበለት፣ የዘንባባ ዝንጣፊ ተይዞለት እንዳልተዘመረለት ኢሳያስ ለምን “በቃ” ብለው ዳግም ህዝባቸው ላይ ቆለፉ?
እንቅጩን ስንነጋገር ከኤርትራ በኩል የተነሳው ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምክንያታዊ ያልህነ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ፣ የተደራጀ እና ስልታዊ የሻንጣ ስርቆት፣ የሻንጣ ማዘግየትና ካሳ አለመክፈል የሚሉ ናቸዎው። በዚህ ሳቢያ ከመስከረም 20/2017 ዓ.ም. በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርጋቸው በረራዎችን በሙሉ ማገዱን አስታውቋል።
አየር መንገዱ በበኩሉ “በረራ እንድናቆም የሚጠይቀው ደብባቤ ከመድረሱ ከሁለት ሳምንት በፊት የምናደርገውን በረራ ከ10 ወደ 15 እንድናሳድግ፣ የምንጠቀመውን መለስተኛ አውሮፕላን ወደ ከፍተኛ አውሮፕላን እንድናሳድግ ፣ በቀን ሁለት በረራ እንዲሁም በየሳምንቱ ዓርብ ሦስት በረራ እንድናደርግ ጠይቀውን ነበር” ሲል ባሰራጨው መረጃ የተጠቀሰው ክስ በተላከለት ደብዳቤ አለመገለጹን አመልክቷል። በቢዝነስ ቋንቋ ” ግቅሬታ ካለ ተነጋግረን እንፈታለን” ሲል ግንኙነት ለማድረግ ሙከራ እያደረገ መሆኑን አመልክቷል።
ውስን ነጥቦች
- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ ለሚያደርገው በረራ ልክ እንደ ኬንያዊያን፣ ታይላንድ ፣ ጅቡቲ፣ የመን ወይም ሶማሊያ በዶላር ክፈሉ ሲል ኤርትራዊያንን አላስጨነቀም። በሌላ አነጋገር የውጭ ዜጋ ናችሁ አላላቸውም።
- ከኤርትራ ወደ አዲስ አበባ የሚጫን ኮንትሮባንድም ሆነ ጥሬ ዕቃ እንደሌለ ይታወቃል። ስለዚህ የሚጫነው ከኢትዮጵያ ነው። ከኢትዮጵያ የሚጫኑ ማናቸውም ጭነቶች ደግሞ ህግና ደንብ ተዘጋጅቶላቸው የሚከናወኑን ናቸው። እንደሚሰማው ከሆነ ማጋዝ ቆሟል።
- በዚህ መነሻ በተደራጀ መልኩ ይዘረፋል የተባለው ሻንጣና ንብረት ምንድን ነው? ከአስመራ ወደ ኢትዮጵያ ሲቻን ሊዘርፈ የሚችለውና ዋጋ የሚያወታው ንብረት ምን ይሆን? ከኢትዮጵያስ? የምታውቁ ዝርዝር ብታቀርቡ
- የዋጋ መናር የንግድ ጉዳይ በመሆኑ አማራጭ መፈለግ ወይም ተወዳዳሪ አየር መንገድ ማጎልበት ሲቻል በተልካሻ ምክንያት በረራ የታገደው እውን ለኤርትራውያን በመቆርቆር ነው? ወይስ በሌላ? በመቆርቆር ከሆነ አንድ አጭር ታሪክ ላንሳና ፍርዱን ራሳቸው ይስጡ
አውሮፓ በስደት የመኖሪያ ፈቃድ ያገነች አንድ የኤርትራ ተወላጅ ሁለት ልጆቿ እንዲመጡላት ፈቃድ ብታገኝም ሻዕቢያ ከልክሏቸዋል። የአስራ አንድና የሰባት ዓመት ልጆቿ ያለ እናት አስመራ ይኖራሉ። በሱዳንና በትግራይ አስቀድመው በመውጣት ልጆቻቸውን ለመሳም የበቁ እንዳደረጉት እሷም ወደ ልጆቿ በሱዳን፣ በትግራይ ወይም በሌላ አማራጭ ከአስመራ ለማስወጣት ብትሞክርም የጸጥታው ሁኔታ አላስቻላትም።አዲስ አበባ ሄደው ጉዳያቸውን በውክልና እንዳስፈጽሙ በነሱ እድሜ ላሉ የሻዕቢያ መንግስት ፓስፖርትና የመውጫ ፈቃድ አይሰጥም። እንግዲህ ይህ ለዜጎቹ ነቀርሳ የሆነ ድርጅት ነው “ዋጋ ተወደደ፣ ስልቻ ጠፋ” በሚል የሚዘምረው። ፍርዱን ስጡ!!
ከላይ ያሉትን ጉዳዮች ያነሳሁት የአየር መንገድ ጉዞ መሰረዘ ሌላ ምክንያት እንዳለው ለማሳየት ነው። ሻዕቢያ ከሽልነት ዘመኑ ጀምሮ እስካረጀበት ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ላይ አሸባሪና ተቃዋሚ ሲያደራጅ መኖሩን አንድም ኤርትራዊ አይክድም። ኢትዮጵያ ውስጥ የምትኖሩ ኤርትራዊያን በምን ያክል ደረጃ ሻዕቢያን ስትረዱና እየረዳችሁ እንደሆነ አንካካድም።(ንጽሃንና በሚዛን ነገሮችን የሚመረምሩትን አይመለከትም) እንደ ህዝብ አይከብደንም? እስከመቼና ምን እስክንሆን ድረስ ሻዕቢያን እንታገስ? ኤርትራዊያን ይህን ልክ ነው ብላችሁ ታስባላችሁ? ታምናላችሁ? እናም ከሻዕቢያ ጋር ታብራላችሁ? መልሱን ለምስኪኖች ኢትዮጵያዊያን አድርሱ። አንድ ግልጽ ጉዳይ ቢኖር ግን ኢትዮጵያ ሻዕቢያን ከነሴራው መሸከም ታክቷታል። በባድመ ጦርነት ወቅት እንዳንጨርሰው መለስ ዘጋው። አሁን ግን ጊዜው ነው። ምክንያቱም ድክሞናል።
የተቋረጠው ወዳጅነት ሲጀመር ነገሮችን በውልና በህግ አጅቦ በጊዜ ሂደት ወደ ላቀ ወንድማማችነት ለመሸጋገር ቢሆንም በሻዕቢያ በኩል የተመረጠው በግርግር ወዳጅነት መቀጠልን ነው። አስራ ስምንት የንግድ፣ የጸጥታና የማህበራዊ ውሎችን አካቶ ለሻዕቢያ የቀረበው የፕሮቶኮል ስምምነት ምላሽ ሳያገኝ ሸረሪት አድርቶበት አስመራ የተዘጋበት ህጋዊ ግንኙነትን የመሸሽ ልማድ ነው።
ሻዕቢያ በትግራይ ጦርነት ከጣሳና ጭልፋ ዝርፊያ ጀምሮ ከባድ መሳሪያዎችንና የፋብሪካ ማሽኖችን፣ የህክምና ቁሶችን ወዘተ በመዝረፍ አትርፏ። ሰሊጥና ዕህል አግዟል። አልተሳካለትም እንጂ ወልቃይት ላይ ለመስፈር ብዙ ጥሯል። ይህ በጦርነት ውስጥ የሚገኝ ጥቅም ያሳበደው ሻዕቢያ በትግራይ እንዴት ሰላም ይሰፍናል በሚል አበደ። የትግራይ ህዝብ እስኪያልቅ ጦርነቱ መቀጠል እንዳለበት ስለሚያምን የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ለንቦጩን ጣለ። ቀድሞ የተዘጋጀበትን ሴራውን ቆስቁሶ አማራ ክልልን አነደደ። ከብዙ ትዕግስት በሁዋላ ኢትዮጵያ የባህር በር ፍለጋ ኢሳያስ የገፉትን ውል ይዛ ፊቷን ወደ ሶማሊላንድ ስታዞር ሻዕቢያ ቢጫ ወባው ተነሳና የለኮሰውን ዕሳት ይበልጥ እንዲቀጣጠል ከኦሮሚያ እስከ አማራ ክልል ነዳጅ መድፋቱን ቀጠለ።
ተቆልፎባቸውና በማዕቀብ እግር ከቶርች ተጠፍረው የነበሩትን ኢሳያስ ነጻ ያወጣች አገር ላይ ኢሳያስ ከታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር አብረው በገሃድ መግለጫና ተቃውሞ ያሰሙ ጀመር። እንደ ውሃ ቀጂ ግብጽና ሶማሊያ እየሮጡ ኢትዮጵያ ላይ የሚደፉትን ሴራ አመረቱ። አሁንም እያመረቱ ነው። ወደፊትም ያቀጥላሉ። ያለፉትን ስድስትና ሰባት ወራት መንግስት ታግሶ እንጂ ሲፈጸምብን የነበረው ሁሉ ብዙ ነገር የሚያማዝዝ ነበር።
ዛሬ በየጥጋ ጥጉ ” ውሳኔው ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት እንደሚጀመሩ ማሳያ ነው” የሚል ትንታኔ የሚሰጡና ብሄራዊ እይታቸው በዘርና በሻዕቢያ ተላላኪነት የተዘጋባቸው አካላት እንደ አዲስ ግኝት ይህን ቢሉም ” ሻዕቢያ እያለ ኢትዮጵያ ንጹህ አትጠጣም” የሚል አቋም ከተያዘ ቆይቷል። ብዙ ምልክቶችም አሉ። የሚባላ ግዙፍና ዘመናዊ ጦር የተገነባው ለውስጥ ተላላኪና የሴራ አስፈሳሚ ሽፍታ እንዳልሆነ መንግስት በተደጋጋሚ አስታውቋል። ህዝብም ድጋፉን የሚሰጥ ለመሆኑ የባድመን ወቅት የህዝብ ምላሽ ማስታወሱ በቂ ነው።
ሻዕቢያም ሆነ ወዳጆቹ በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ወይም አንዱ በሌላው ጣልቃ ሳይገባ የመኖርን ዘዬ ሊከተሉ ይገባል። “እኛ ስንሰልል ትክክል ነው። እኛ አገራችንን ስንወድ ትክክል ነው። እኛ ኮንትሮባንድ ስንነግድና ገንዘብ ምንዛሬ በጨላእማ ስንሰራ ጽድቅ ነው። እናነት አገራችሁን ስትወዱ ስህተት ነው” የሚለው የድሮው ጮሌነት ዛሬ ላይ ሰለማይሰራ በጋራ እናስብበት። “ሲበዛ ማርም ይመራል” እንደሚባለው እንዳይሆን፣ ኤርትራዊያን ለኢትዮጵያም ለህዝቧም እዘኑ፤ ደክሞናል፣ ስልችት ብሎናል። ተከፍሎት በየማህበራዊ ሚዲያ የሚንጣጣውን መመዘኛ አድርጋችሁ ሚዛናችሁን አትሳቱ። ህዝብ ሁሉን ያውቃል። ችሎ እንጂ ሞኝ ሆኖ አይደለምና ይህ ህዝብ ተረዱት። ኢትዮጵያ ያለ አንዳች ልዩነት አቅፋ ይዛችኋለችና አክብሯት።
ሰለሞን ተክሉ ነጻ አስተያየት – አዘጋጁ – ለጸሃፊው ማላሽ ለመስጠት የዝግጅቱን አድራሻ ይጠቀሙ። ጽሁፉ የጸሃፊው ብቻ አስተያየት ነው