ይኽን መሰል የፖሊሲ አማራጮች በቂ የሆነ የውጪ ምንዛሬ ክምችት የሚፈልጉ ከመሆናቸውም በላይ ይኽ ማሻሻያ ሊያስከትለው የሚችለው ከፍተኛ የዋጋ ንረትን መቋቋም የሚያስችል ምርትና ምርታማነት በሀገር ውስጥ ማደግ ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ዋነኛ የዋጋ ንረት መንስኤ የሆነው የምግብ ሰብል ምርት በበቂ ሁኔታ ማምረትና ማቅረብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ይኽ ደግሞ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ብዙ ያልተሠሩ የቤት ሥራዎች ያሉባት ሀገር በመሆኗ የፖሊሲ ማሻሻያው ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ የሚገባው ጉዳይ መሠራቱ ሳይረጋገጥ ጊዜያዊ የውጭ ምንዛሬ ችግርን በመፍታት ላይ ብቻ ትኩረት መደረጉ መዘዙ ከፍተኛ ነው፡፡
ፖሊሲ የማውጣት ሉዓላዊነትን የሚገድብ ማሻሻያ ውጤቱ ቀውስ ጋባዥ ትርፉም ሀገራዊ ዕዳ ነው!
ሀገራት የሚከተሉትን የገንዘብ ፖሊሲን በሚመለከት በዓለም ላይ በርካታ አመለካከቶች ቢኖሩም በዋናነት በዚህ ጉዳይ ላይ የመንግሥት ሚና ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ ያለውን አመለካከት ግን በሁለት መክፈል ይቻላል። በአንድ በኩል በጥቅሉ ገበያውን እንደ ወሳኝ እና ራሱን የሚያርም መሣሪያ የሚያዩ ባለሙያዎች የገንዘብ ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ለገበያው መተው አለበት ችግሮች ሲፈጠሩ እንኳን ገበያው ራሱን በራሱ እያረመ ያስተካክለዋል ሲሉ በሌላ በኩል ደግሞ የገንዘብ ፖሊሲን በሚመለከት የማዕከላዊ ባንኮች ቀጥተኛና ንቁ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ የሚከራከሩ ባለሙያዎች አሉ።
በመርሕ ደረጃ የውጪ ምንዛሬ በገበያ ወይም በማዕከላዊ ባንኮች እንዲተመን ማድረግ በራሱ እንደተሳሳተ የፖሊሲ አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ እንደዚህ አይነት ፖሊሲዎች መለካት የሚችሉት አንድን ሀገር ወደየት ነው መውሰድ የምንፈልገው? እና ምን አይነት እድገት ነው የሚያስፈልገን በሚሉት ቁልፍ ጥያቄዎች ላይ ይመሠረታል።
እንደ ኢዜማ ላለ በኢትዮጵያ ውስጥ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ለሚሞግት እና እድገት ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ያካተተ መሆን አለበት ብሎ ለሚያምን ፓርቲ ምርጫው ብዙ ከባድ አይሆንም። የገንዘብ ፖሊሲን ጨምሮ አጠቃላይ ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገትን በሚመለከቱ ጉዳዮች መንግሥት በቀጥታ እና በንቁ ሁኔታ ጣልቃ መግባት ካልቻለ ከጥልቅ ድኅነት መውጣትም ሆነ ማኅበራዊ ፍትሕን ማረጋገጥ እንደማይቻል ፓርቲያችን በፅኑ ያምናል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በገንዘብ ፖሊሲው ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃም በሚመለከት ፓርቲያችን አስቀድሞ በሰጣቸው መግለጫዎች በጥድፊያ የሚወሰዱ እርምጃዎች አደጋ እንደሚኖራቸው አሳውቋል፡፡ መንግሥት ያለበትን ስር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመፍታት ሲል በውጭ አበዳሪዎች የፖሊሲ ጫና ስር እንዳይወድቅ ስናሳስብ ብንቆይም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ መንግሥት የብርን የመግዛት አቅም በገበያ እንዲወሰን ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህም ውሳኔ ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ድጋፍ እና ብድር ከዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት ማግኘቱን አሳውቋል፡፡
ምንም እንኳን እንደፓርቲ መንግሥት የገባበትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና አጠቃላይ የምጣኔሀብት አጣብቂኝ የምንረዳ ቢሆንም አሁን እንደመፍትሄ ያስቀመጠው የገንዘብ የመግዛት አቅምን በገበያ የመወሰን አማራጭ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላለ የአምራች ዘርፉ እንጭጭ በሆነ እና ከውጭ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ ጥገኛ ለሆነ ሀገር ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪን በማስከተል የዋጋ ንረትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያባብስ መሆኑ ተገማች ነው፡፡ ምንም እንኳን መንግሥት የደሞዝ ጭማሪን፣ ድጎማዎችን፣ የሴፍቲኔት መርኃግብሮችን ጨምሮ በርካታ ይኽን ሊያስታምሙ የሚችሉ እርምጃዎችን በተጓዳኝ እንደሚወስድ የገለፀ ቢሆንም ለጊዜው ማስታገሻ ከመሆን ባለፈ ችግሩን በዘላቂነት ሊፈታ የሚችል የመፍትሄ ሐሳብ አይደለም።
አሁን መንግሥት የወሰደው እርምጃ የኑሮ ውድነትን በማባባስ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይከተናል የሚለው ስጋት እንዲሁ ከንድፈ ሐሳባዊ አመክንዮ ብቻ የሚነሳ ስጋት እንዳልሆነ ተመሳሳይ እርምጃዎችን ከወሰዱ በኋላ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከገቡ ከእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ሁኔታ ውስጥ ካሉ ሀገራት ተሞክሮ በግልፅ መመልከት ይቻላል።
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ‹‹ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የዓብይ ምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መግባቷን›› በማስመልከት የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያው እንዲወሰን በተደረገ ማግስት ምጣኔሀብቱ ያለበትን ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በአንዳች ምትሀታዊ ኃይል ብን ብሎ የሚያጠፋ ይመስል አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የሕዝብ ብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን ያሳዩት ፈንጠዝያና እልልታ የሚያስተዛዝብ ነው፡፡
በእርግጥ በዚህ ምክንያት አሁን ሀገራችን ያላት በጣም ዝቅተኛ የውጪ ምንዛሬ ክምችት መጠን ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት በሚለቁት (በለቀቁት) የውጭ ምንዛሬ ለጊዜው እፎታ ይገኝ ይሆናል፡፡ ይሁንና በተለይ መሠረታዊ የሆነው በሀገር ውስጥ ምርት ራስን መቻል ባልተረጋገጠበት፣ ምርታማነትን የሚያበረታታ የፀጥታ ሁኔታ በሌለበት፣ በውጭ ግብአት ላይ ከፍተኛ ጥገኛ የሆነ የምጣኔ ሀብት ባለቤት በሆንበት ብሎም ይህን ፖሊሲ በማስፈፀም ሒደት ሊመጡ የሚችሉ ከፍተኛ ህፀፆችን ለማስተናገድ አቅም ያላቸው ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ አሁን የሚታየው ችግር ተመልሶ መምጣቱን አይቀሬ ያደርገውና አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ይሆናል፡፡
ይኽን መሰል የፖሊሲ አማራጮች በቂ የሆነ የውጪ ምንዛሬ ክምችት የሚፈልጉ ከመሆናቸውም በላይ ይኽ ማሻሻያ ሊያስከትለው የሚችለው ከፍተኛ የዋጋ ንረትን መቋቋም የሚያስችል ምርትና ምርታማነት በሀገር ውስጥ ማደግ ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ዋነኛ የዋጋ ንረት መንስኤ የሆነው የምግብ ሰብል ምርት በበቂ ሁኔታ ማምረትና ማቅረብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ይኽ ደግሞ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ብዙ ያልተሠሩ የቤት ሥራዎች ያሉባት ሀገር በመሆኗ የፖሊሲ ማሻሻያው ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ የሚገባው ጉዳይ መሠራቱ ሳይረጋገጥ ጊዜያዊ የውጭ ምንዛሬ ችግርን በመፍታት ላይ ብቻ ትኩረት መደረጉ መዘዙ ከፍተኛ ነው፡፡
እንደ ኢዜማ እምነት ለመፍትሔው ወሳኙ ጉዳይ ምርታማነትን ማሳደግ ከመሆኑ አንፃር እንደሀገር ትኩረታችን የምርት ኃይሎች ሁሉ ወደሥራ እንዲገቡ እንቅፋት የሆነውን የሰላም ዕጦት፣ ሀገሪቱን ቀፍድዶ የያዘው የዘውጌ ፌደራሊዝም እና መሰል እድገታችንን አንቀው የያዙ የፖለቲካ ሥንክሳሮች መፍታት ላይ ማተኮር እና ወደተለያዩ የምጣኔሀብት ክፍሎች ሚዛን የጠበቀ የሀብት ፍሰት እንዲኖር ማድረግ ላይ መሆን አለበት፡፡ በተለይም ግብርና ለአጠቃላዩ ጥቅል ሀገራዊ ምርት እና የሥራ ፈጠራ ከሚያበረክተው አስተዋፅዖ አንፃር የሚገባውን በጀት እስካልተመደበለት፣ ዘርፉን ብቃት ባላቸው ግለሰቦች እንዲመራ እስካልተደረገ እና መሠረታዊው የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ እልባት እስካላገኘ ድረስ፣ የውጪ ምንዛሬ ተመን በገበያ መወሰኑ የዋጋ ንረትን ከማባባስ ያለፈ ዘላቂ እና መሠረታዊ ችግሮቻችንን የመፍታት ፋይዳ አይኖረውም፡፡
ከዚህ አንፃር ስንመዝነው ማሻሻያው ከመደረጉ አስቀድሞ ሚያዘዝያ 12/2016 ዓ.ም. የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም የኢትዮያን የኢኮኖሚ ሥብራት አይጠግንም ስንል እንዳሳሰብነው የተደረገው ማሻሻያም በየትኛውም መለኪያ ወቅቱን ያልጠበቀ ነው ብለን እናምናለን።
ኢዜማ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም በተደጋጋሚ ጊዜ ለመንግሥት እና ለሕዝብ ሲያሳውቅ ቢቆይም ሰሚ ጆሮ አላገኘም። ስለሆነም ከዚህ የውጭ ምንዛሬን በገበያ መወሰንን በሚመለከት በተወሰነው ውሳኔ የሚመጣውን ማንኛውም በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚደርስ የምጣኔ ሀብት፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ውሳኔውን ያሳለፈው መንግሥት ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን እንገልፃለን።
የመንግስት መገናኛ ብዙኃንም የአንድን ወገን ሀሳብ ብቻ ወደ ሕዝብ ከማድረስ አልፈው ይኽን ከፍተኛ የዋጋ ንረትን ሊያስከትል የሚችል ውሳኔ እንደ ምስራች በእንኳን ደስ አላችሁ አጅበው ማቅረባቸው ለሕዝብ ያላቸውን ንቀት ያሳዩበት፣ አሁንም ከገዢው ፓርቲ ጥገኝነት ወጥተው ሙያቸውን የሚያስከብሩ የመረጃ ብዝሃነትን እና ፍትሃዊነት የሚያረጋግጡ ዘገባዎችን ለመሥራት ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላቸው ያረጋገጡበት ነው። ኢዜማ በተለይ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ለሀገር እድገት ያላቸውን ከፍተኛ ሚና እንደሚረዳ ፓርቲ ይኽን አካሄዳቸውን በማረም ለእውነት እና ለሙያ ክብር እንዲቆሙ ከዚህ ቀደም በተዳጋጋሚ አንዳሳሰብው ሁሉ አሁንም በድጋሚ ጥሪያችንን ማቅረብ እንፈልጋለን፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (#ኢዜማ)
ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም.