“ከተማዋ ድንዛዜ የሰፈነባት፣ ጎስት ታውን (ghost town) ትመስል ነበር፤ ባጃጆች አንድ ሰው ሲያዩ ሥጋ እንዳየ አሞራ ነው ሰው የሚከብ ቡት፤ ወደ ዘጌ ደሴቶች ለሚደረገው ጣናን አቋርጦ የመሄድ ጉዞ ቢዚ ሆነው ይውሉ የነበሩት ጀልባዎች አሁን ላይ የውሃውን ዳርቻ በሙሉ ሸፍነውት የሥራ ማቆም ዓድማ የመቱ ነው የሚመስለው፤ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ አውሮጵላኑ ሞልቶ የነበረ ቢሆንም ከተሳፋሪ ውስጥ የነበሩት የውጭ ዜጎች ሁለት ብቻ ነበሩ”
- እስከ 2 ቢሊዮን የሚጠጋ ብርም ከዘርፉ ይገኝ ነበር
የአማራ ክልል ቱሪዝም በግጭቱ ምክንያት ሥራ ለማቆም መቃረቡን የክልሉ የባህልና የቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ’
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የዐማራ ክልልን ይጎበኛሉ ተብለው ከታቀዱት የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ቁጥር የመጡት 20 በመቶ ብቻ መኾናቸውን የገለጸው የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ፣ የክልሉ ቱሪዝም በእጅጉ በመዳከሙ ሥራ ለማቆም መቃረቡን አስታውቋል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር አየለ አናውጤ ትናንት ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ በክልሉ ተለዋዋጭ ገጽታ እያሳየ የቀጠለው የትጥቅ ግጭት፣ “ዘርፉን ጨርሶ ለማስቆም እየተቃረበ ነው፤” ብለዋል፡፡
በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶችም፣ በግጭቱ ሳቢያ ከሥራ ገበታ ውጭ መኾናቸውን አመልክተዋል፡፡ (VOA)
ጥር 7 2016 የታተመው የጀርመን ድምጽ ዘገባ ችግሩ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን ዶ/ር አየለ አናውጤ ጠቅሶ ዘግቦ መዘገቡ ይታወሳል። በአማራ ክልል በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ክስተቶች የክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በእጅጉ ማሽቆልቆሉን ነዋሪዎችና በክልሉ ተደጋጋሚ ጦርነት ከመከሰቱ ቀደም ብሎ በ2010 ዓ.ም 210 ሺህ የወጪ ቱሪስች አማራ ክልልን የጎበኙት መሆኑ ተጠቅሷል ።
በክልሉ በነበሩና ባሉ ችግሮች ምክንያት በ2016 ዓ.ም ግማሽ ዓመት ክልሉን የጎበኙ የውጪ ጎብኝዎች ቁጥር ከ3ሺህ 500 ብዙም እንደማይበልጡ ጽ/ቤቱ አመልክቷል። ከዘርፉ የተገኘው ገቢም በእጅጉ ቀንሷል ተብሏል።
በዓለም ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ በሽታ ምክንት ተጎድቶ የነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ያገግማል ተብሎ ሲጠበቅ እንደገና በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ቱሪዝሙን ከድጥ ወደ ማጡ ከትቶት ቆይቷል፣ ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት የባሰ ቱሪዝሙንና በአስጎብኝነት የተሰማሩ ወጣቶችን በከፍተኛ ሁኔታ እንደጎዳ አንድ በጎንደር ከተማ በአስጎብኝነት የተሰማሩ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
ድምፃቸው እንዲቀየር የፈለጉ የላሊበላ ከተማ ነዋሪና አስጎብኝም በክልሉ የተከሰቱ ተደጋጋሚ ችግሮች በቱሪዝም እንዳስትሪው ላይ የፈጠሩትን ጫና አስረድተዋል፡፡ ለውጪ ጎብኝዎችን በተለያየ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ አስጎብኝዎች ያለሥራ መቀመጣቸውን ደግሞ አንድ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ነግሮናል፡፡
“… አሁን ቱሪስት የለም፣ ላሊበላ ሲከበር ቱሪስቶቹ ከላሊበላ ወደ ባህር ዳር፣ ከላሊበላ ወደ ጎንደር ይመጡ ነበር። መንገዱ፣ የሰላሙ ሁኔታ ያን አላደረገም፣ አሁን ጥምቀት እየመጣ ነው፣ ግን እንቅስቃሴ የለም፣ ቤት ቁጭ ብለን ነው ያለነው፣ ያለው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ የሞተ ነው፣ የምንሰጠው አገልግሎት ቱሪስቱን ወደ ገዳማት መውሰድና መመለስ፣ እንግዶቹን ከአየር ማረፊያ መቀበል፣ ወደ ቱሪስት መዳራሻ መውስድ፣ ባለው ሁኔታ ግን አሁን ቱሪስትም አይመጣም ስራችንም ቆሟል፡፡ ቱሪስቶችን ወደ ጣና ገዳማት የሚወስዱ ወደ 150 ጀልባዎች ነበሩ፣ ወደ 80 ለቱሪዝም አገልግሎት የተዘጋጁ ተሸከርካሪዎች ነበሩ ሌሎችም፣ ይህ ሁሉ ሥራ አሁን አቁመዋል” ብለዋል።
“ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከመግባታችን በፊት የነበረው የቱሪስት ቁጥር ካለው እምቅ ሀብት አኳያ ዝቅተኛ ነው ቢባልም ጥሩ የሚባል ነበር፣ ከጦርነቱ በኋላ ባሉት ጊዜዎች ግን ቁጥሩ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ ነው የመጣው፣ ከጦርነቱ በፊት በዓመት እስከ 270ሺህ የውጪ ቱሪስት አማራ ክልልን ይጎበኝ ነበር፣ እስከ 2 ቢሊዮን የሚጠጋ ብርም ከዘርፉ ይገኝ ነበር፣ ወደ 2016 ዓ ም ስንመጣ በ2016 ዓም ግማሽ ዓመት 84ሺህ የዉጪ ጎብኚ ወደ ክልሉ ይመጣል ተብሎ ታቅዶ ነበር፣ ግን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ባለፉት 6 ወራት 10ሺህ 500 ያህል ብቻ ናቸው ወደ ክልሉ የመጡ የውጪ አገር ቱሪስቶች፡፡ በገቢ ደረጃ 238 ሚሊዮን ብር ነበር በግማሽ ዓመቱ የታቀደው፣ በግማሽ ዓመቱ ከውጪ አገር ጎብኝዎች የተገኘው ገቢ ግን ከ40 ሚሊዮን ብር የበለጠ አይደለም” ብለዋል፡፡
እንደ ዶ/ር አየለ ባለፉት 6 ወራት 11 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ጎብኝዎች የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ ታቅዶ የነበረ ሲሆን 4 ሚሊዮን ያህል የአገር ውስጥ ጎብኝዎች ወደ ቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች መድረሳቸውን አመልክተዋል፡፡ ከአገር ውስጥ ጎብኝዎች በ6 ወሩ ወደ 8 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ሲሆን አፈፃፀሙ ግን 1.6 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ከጦርነቱ በፊት ከአገር ውስጥ ጎብኝዎች ብቻ በዓመት እስከ 5 ቢሊዮን ብር ይሰበሰብ እንደነበርም ኃላፊው በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡
በርካታ ወጣቶች በአስጎብኝነትና ተያያዥ ሥራዎች ተሰማርተው እንደነበር ኃላፊው አመልክተው መልሶ ለማደራጀት እንቅስቃሴ እየተደረገ ባለበት ወቅት በክልሉ ተፈጠረው የሰላም እጦት ስራዎችን እንዳናከናውን አድርጎናል ብለዋል፡፡
“በማህበር ተደራጅተው፣ አንዳንዶቹ የማህበረሰብ ኢኮ ቱሪዝም አቋቁመው፣ ሎጂዎችንም ገንብተው፣ እየሰሩ የነበሩ ነበሩ በብዙ ቦታዎች በጎብኝ እጦት ምክንያት ተበትነው ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አንዳንዶቹ የሚሰሩባቸው ኢኮ-ሎጂዎች በጦርነት ምክንያት ፈርሶባቸው ሥራ ያቆሙ ናቸው፣ አንዳንዶቹ እስከ ስደት ደረጃ የደረሱ እንዳሉ መረጃዎች አሉን፡፡”

ከወራት በፊት ከአውሮጳ ዘመዶቿን ለመጠየቅ በባሕር ዳር አካባቢ ጉብኝት አድርጋ የነበረ አንዲት የክልሉ ነዋሪን በመጥቀስ የጎልጉል መረጃ አቀባይ እንዳለው ግለሰቧ ባሕር ዳር ስትሔድ ያየችው ሁሉ አስደንግጧታል። ከቦሌ አውሮጵላን ተሳፍራ ስትሄድ ለወትሮው ባንድ በረራ ውስጥ እስከ ግማሽ ያህል የውጭ አገር ሰዎች ይሳፈሩ ነበር፤ እሷ በሄደችበት ጊዜ ግን አንድም የውጪ ዜጋ ተሳፋሪ አላየችም።
እዚያ በቆየችበት ጊዜም የተመለከተችውን ስትናገር፤ “ከተማዋ ድንዛዜ የሰፈነባት፣ ጎስት ታውን (ghost town) ትመስል ነበር፤ ባጃጆች አንድ ሰው ሲያዩ ሥጋ እንዳየ አሞራ ነው ሰው የሚከብ ቡት፤ ወደ ዘጌ ደሴቶች ለሚደረገው ጣናን አቋርጦ የመሄድ ጉዞ ቢዚ ሆነው ይውሉ የነበሩት ጀልባዎች አሁን ላይ የውሃውን ዳርቻ በሙሉ ሸፍነውት የሥራ ማቆም ዓድማ የመቱ ነው የሚመስለው፤ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ አውሮጵላኑ ሞልቶ የነበረ ቢሆንም ከተሳፋሪ ውስጥ የነበሩት የውጭ ዜጎች ሁለት ብቻ ነበሩ” በማለት ትዝብቷን አጋርታለች። ስትቀጥልም “ይህንን ያየሁት ኅዳር እና ታኅሣሥ አካባቢ ነበር፤ ያኔ ለጓደኞቼ የነገርኳቸው አማራ ክልል ቱሪዝም ይቆማል ብዬ ነበር፤ ዛሬ ይህንን እንደ ትንቢት ተፈጽሞ ስሰማ ምንም አልደነቀኝም” ብላለች።
ራሱን ፋኖ ብሎ በሚጠራው ብረት ባነሳ ኃይልና በመንግሥት መካከል የተከሰተው ግጭት በጦርነትና በትህነግ ወረራ ወድሞ የነበረውን ክልል ሳያገግም አከርካሪውን ብሎ ያሽመደመደው ሆኗል። የትህነግ ዘረፋ ክልሉን 14 ዓመት ወደኋላ የወሰደው ሲሆን እስካሁን ቀጥሎ ያለው መሪና ዓላማ ዓልባ ግጭት እጅግ ብዙ ዓመታት ክልሉን ወደኋላ እየወሰደው መሆኑ በገሃድ የሚታይ ሆኗል። ጉዳዩ በቶሎ ካልተቋጨ በአማራና በሌሎች ክልሎች መካከል የሚኖረው ሁሉን ዓቀፍ ልዩነት “ተበደልን” በሚል ሰበብ እንደገና ክልሉን ለማያባራ መከራ ውስጥ እንዳያስገባው አስተያየት ሰጪዎች ሥጋታቸውን ይናገራሉ።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ