ኢህአዴግ ወደሥልጣን ከመጣ ጀምሮ 30 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከኢትዮጵያ በሕገ ወጥ መንገድ መሸሸቱን እና ገንዘቡንም ለማስመለስ መንግሥት ከባድ ሥራ ከፊቱ እንደሚጠብቀው ምሁራን ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) ከሀገር የሸሸውን ገንዘብ ለማስመለስ ከፍተኛ ጥረት ቢጠይቅም መንግሥት ጉዳዩን እንደሚከታተለው አሳውቀው የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዳልታዬ ምሁራኑ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ እንደገለጹት በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ከኢትዮጵያ ወደተለያዩ ሀገራት በሙስና እና ማጭበርበር የሸሸው ገንዘብ 30 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚደርስ በጥናት ተረጋግጧል፤ ገንዘቡም በወቅቱ የኢትዮጵያን የስድስት ዓመት ተኩል በጀት መሸፈን የሚችል ወይም አሁን ያለውን የውጭ አገር የመንግሥት ብድር በአንድ ቀን ከፍሎ መጨረስ የሚያስችል ነው።
ጥናቱ ሲሰራ በሀሰት ደረሰኝ የወጪ ንግዱ ላይ በማጭበርበር፣ ከዕርዳታ የተገኘውን እና ጥቅም ላይ የዋለውን ልዩነት በመመርመር እንዲሁም በቀጥታ በሙስና የወጡ ገንዘቦችን ተመርኩዞ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ በተለይ በዕርዳታ የሚገባው ገንዘብና ተግባር ላይ የሚውለው መጠን ከፍተኛ ልዩነት እንደነበረውና ለሌብነት የተጋለጠ እንደነበር አስረድተዋል።
‹‹የሸሸው ገንዘብም በግለሰቦች ሒሳብ (አካውንት) እና በባለሥልጣናት የባንክ አድራሻ ነው ወደውጭ የወጣው›› ያሉት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ደግሞ የግለሰቦችን አካውንት የመመርመር ሥልጣን ስለሌለ የማስመለሱ ጉዳይ ከባድ መሆኑን አመልክተዋል፤ ቢሆንም ግን በመርህ ደረጃ መብት ባይኖርም በፖለቲካ ጥያቄ ተጽእኖ ማድረግ እንደሚቻል መክረዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ማብራሪያ ሕጉ ባይፈቅድም አሜሪካ፣ ዐረብ አገራት እና አውሮፓውያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን በጥሩ መልኩ ስለሚቀበሉ የመንግሥትን የመርምሩልኝ ጥያቄ ሊቀበሉ ይችላሉ። በመሆኑም ጉዳዩ የፖለቲካ ጥያቄ ነው የሚሆነው። አሜሪካን እና የተለያዩ ሀገራትን ስለሸሸው ገንዘብ መገኛ እና መረጃ አጣሩልኝ በማለት ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል። ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ‹‹የሸሸውን ገንዘብ የማስመለስ ጥረት ይደረጋል›› ቢሉም እስካሁን ግን ተጨባጭ እና ተግባራዊ ጉዳይ አለመታዬቱን ፕሮፌሰር ዓለማየሁ አስታውቀዋል።
አሁንም በርካታ ገንዘብ ከሀገር እየሸሸ በመሆኑ በእጅ ያለውንም መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ መክረዋል። የፋይናንስ አሠራር ቁጥጥር እና ምርመራን በማጠናከር በማጭበርበርም ሆነ በሙስና ግለሰቦች ወደ አካውንት እንዳይገባ ካልተሠሰራ ትርፉ ድካም ነው የሚሆነው።
በፋይናንስ እና ታክስ ጉዳዮች ለ50 ዓመታት የሰሩት ፕሮፌሰር ፍሰሐጽዮን መንግሥቱ እንደተናገሩት ደግሞ በአፍሪካ በየዓመቱ ካደጉ አገራት ከሚደርሰው ዕርዳታ ይልቅ በሕገ ወጥ መንገድ የሚወጣው ገንዘብ በቢሊዮኖች የአሜሪካ ዶላር ብልጫ አለው። በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው።
ሀገር ወዳድነት በመቀነሱ እና በታማኝነት የሚያገለግሉ ባለሥልጣናት ጥቂት በመሆናቸው በርካታ ገንዘብ ከሀገር ሸሽቷል፤ አሁንም እየሸሸ ነው። በመሆኑም ገንዘቡ እንዳይወጣ ከፍተኛ ቁጥጥር ከማድረግ በተጨማሪ የእስካሁኑ የት ደረሰ፣ በማን ስም እና እንዴት ወጣ የሚለው በመረጃ ላይ የተመሠረተ ሰነድ ያስፈልገዋል።
ፕሮፌሰር ፍሰሐጽዮንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ገንዘቡን የማስመለስ ጥረት እንደሚደረግ ቢገልጹም የታየ ግልጽ ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል። በሌላ በኩል የውጭ ባንኮች ገንዘቡ ከየትም ይምጣ ከየትም ተቀብለው ለብድር እና ለተለያዩ ሥራዎች እየተጠቀሙበት ነው።
የባንኮች የሕግ፣ አሠራር እና መብት የማንንም ገንዘብ ማንኛውም መንግሥታት እንዲወስድ አይፈቅድም። በመሆኑም ገንዘቡን ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት ቀላል አይሆንም። ይሁንና በቅድሚያ ጠንካራ የፋይናንስ ደኅንነት ተቋማትን በማጠናከር እና ሀገር ወዳድነቱን በማሳደግ ገንዘቡ እንዳይወጣ ከወጣም አካሄዱን በመረጃ ብቻ ሳይሆን በማስረጃ ጭምር አስደግፎ መከታተል ያስፈልጋል።
መንግሥት የወጣውን ገንዘብ ለማስመለስ ከመሞከር ባሻገር ማን፣ ምን ያህል፣ መቼ እና እንዴት ባለ መንገድ ገንዘብ ከሀገር አሸሸ የሚለውን በዝርዝር አጥንቶ ለቀጣዩ እርምጃ መዘጋጀት እንዳለበትም አሳስበዋል።
የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ እንዳለ አሰፋ እንደተናገሩት ደግሞ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ግሩፕ (ኤግሞንት) አባል ከሆነች ሦስት ወራት በመቆጠሩ በዚህ ወቅት በየሀገራቱ ከሚገኙ 164 የፋይናንስ ደኅንነት ተቋማት ያለምንም ክልከላ መረጃ የማግኘት መብት ይኖራታል።
በመሆኑም በአገር ደረጃ የሸሹ ገንዘቦችን መገኛ እና ተጨባጭ መረጃ የሚያሰባብስ ጥናት ተጀምሯል። ከሀገር የሸሸ ተብሎ በየሚመገናኛ ብዙኃኑ የሚገለጸው የተለያየ ቢሆንም ማጣራቱ ሲደረግ መጠኑን በተጨባጭ ማወቅ ይቻላል። በጉዳዩ ተጠርጥረው መረጃ እየተሰበሰበባቸው የሚገኙ ሰዎችንም በተመለከተ ምርመራ እየተካሄደ በመሆኑ ጊዜው ሲደርስ ይፋ እንደሚሆን መግለጻቸውንም አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዛሬ ዕትሙ አስነብቧል።
እንደ አቶ እንዳለ ገለጻ ተጨባጭ ምንጭ እና መረጃ ላይ ሲደረስ የትኛውንም ሀገር ስለሸሸው ገንዘብ መገኛ እና በማን ስም እንዳለ ያለከልካይ መረጃ ማግኘት ይቻላል። የግል ዓለም አቀፍ ባንኮች ውስጥ ገንዘቡ ቢኖር እንኳን በዚያው አገር ያለው የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል መረጃ የመስጠት ግዴታ ስላለበት መተባበሩ አይቀርም። በጉዳዩ ላይም በመንግሥት ደረጃ የሠላም ሚኒስቴር የሚሳተፍበት ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ዘገባው ጥቅምት 15/2012 ዓ ም የቀረበ የአብመድ ዘገባ ነው ለዛሬው የመንግስት ሌብነት አለ የለም ንትርክ አቅርበነዋል። መረጃ ላይ የሚያተኩር ወቀሳና ትችት አገር ስለሚያቀና፣ በዚሁ ሪፖርት ላይ የተጠቀሱት ወገኖች በማቅርብ ሙያዊና መረጃ ላይ የተደገፈ ሪፖርት ማቅርብ ከሚዲያ ይጠበቃል።