በአሁኑ ወቅት ምርምሮች እንደሚያሳዩት የሆድ እቃችን የአጠቃላይ ጤናችን ማዕከል መሆኑን ነው።
የሆድ እቃ ወይም በእንግሊዝኛው ገት የሚባለው የሰውነታችን ክፍል ጤና በሰውነታችን ካለው የስብ መጠን (ኮሌስትሮል) እስከ አዕምሮ ጤና ድረስ ሰፋ ያለ ግንኙነት አለው።
የሰው ልጅ የፊት ቆዳ ችግር ራሱ ከሆድ እቃ ጤና ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ጥናቶች አሳይተዋል።
የሆድ እቃ በአጠቃላይ በጤናችን ላይ የሚኖረውን ሚናን በተመለከተ ያለው እውቀት እያደገ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ የሆድ እቃ ጤናችንን ለመጠበቅ ምን ዓይነት ምግቦች መመገብ እንዳለብን የሚመክሩ ጥናቶች እንዲሁ በርክተዋል።
የሆድ እቃ የሚባለው ምግብ ተፈጭቶ የሚወገድበትን ሥርዓት የሚያካትት ሲሆን፣ ይህም ጨጓራ፣ አንጀት እና ትልቁ አንጀትን ይይዛል።
የሆድ እቃ ጤናችንን ለመጠበቅ በአሰር (ፋይበር) እና እርሾ (ይስት) የበለጸጉ እንደ እንጀራ ያሉ ምግቦች ጠቃሚ መሆናቸውን ምርምሮች ያሳያሉ።
በዓለም ላይ ለሰውነታችን ጠቃሚ የሆኑ ባክቴሪያዎች እና እርሾዎችን የያዙ (ፕሮባዮቲክ) በሚባሉ ንጥረ ነገሮች የበለጸጉ ምግቦች በከፍተኛ ሁኔታ እውቅና እያገኙ ነው። ፕሮባዮቲክስ ከምናገኝባቸው ምግቦች መካከል እርጎ ወይንም ለቀናት ተቀምጠው የተብላሉ (ፈርመንትድ) የሆኑ ምግቦች ይጠቀሳሉ።
ከሦስት ዓመት በፊት የነበረውን የአሜሪካ የፕሮባዮቲክስ ገበያ ስንመለከት 60 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ባለውም በየዓመቱ 7 በመቶ እንደሚያድግ ፖላሪስ ከተሰኘው የገበያ ጥናት ተቋም መረጃ ያሳያል።
የሆድ እቃ ጤና ለምን ይህን ያህል መሠረታዊ ሆነ? እንዴትስ የሆድ እቃ ጤናችንን ማሻሻል እንችላለን?
ውስብስብ በሆነው አወቃቀሩ ምክንያት ጤናማ የሆድ እቃ ምንድን ነው? የሚለውን እንደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎቻችን በቀላሉ መለየት አይቻልም።
የጤናማ የሆድ እቃን ለመለየት የሚያስችለን አንድ ዓይነት መለኪያ መሳሪያ የለም።
የሆድ እቃችን ባክቴሪያዎች፣ አልጌ፣ እርሾ፣ ፈንገስ እና ሌሎች በዐይን የማይታዩ ጥቃቅን ነገሮችን የያዘ ሲሆን፣ እነዚህ ማይክሮብስ ይሰኛሉ።
እነዚህን ማይክሮብስ ቢለኩ ክብደታቸው ከ1.8 ኪሎ ግራም ይበልጣል። በእያንዳንዱ የአንጀት ክፍል 100 ቢሊዮን የሚሆኑ ጤናማ ባክቴሪያዎች አሉ።
ጤናማ የሆድ እቃ እነዚህን ብዝኃነት ያላቸውን የተለያዩ ማይክሮቦችን በበለጠ የያዘ እንደሆነ በሆድ እቃ እና በአዕምሮ መካከል ያለውን ግንኙነት ላይ በኦክስፎርድ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ካትሪና ጆንሰን ያስረዳሉ።
ሆኖም እሳቸው እንደሚሉት “የማይክሮቦም ሳይንስ በአንጻራዊነት አዲስ መሆኑ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ዝርያዎች እና በእነዚህ ዝርያዎችም ውስጥ ንዑስ ዝርያዎች በመኖራቸው የአብዛኞቹን ተግባር አናውቀውም” ይላሉ።

ጤናማ የሆድ እቃ አስፈላጊነቱ ለምንድን ነው?
የሆድ እቃችን ጤና መታወክ ማለት “የትኛውም የሰውነት ክፍላችን ላይ ችግር እንዲፈጠር ያደርጋል” ይላሉ ተመራማሪዋ ዶክተር ካትሪን።
የሆድ እቃ እና አዕምሮ ጠንካራ የኮሚዩኒኬሽን ሥርዓት ያላቸው ሲሆን፣ ይህም ‘ገት ብሬይን አክሲስ’ (የአንጎል እና የሆድ እቃ ትስስር እንደማለት ነው) ይሰኛል።
አንዳቸው ለሌላኛው ዕድገት መሠረታዊ ሲሆን፣ ጥናቶች እንደሚያሳዩትም ጤናማ ማይክሮቦም የሌላቸው ሰዎች የአዕምሮ እድገት ያልተለመደ ወይም ውስን እንደሚሆን ነው።
የሆድ እቃችን ሁለተኛው አዕምሮ የሚባል ሲሆን፣ ባክቴሪያዎችም በመቶ ሚሊዮን በሚቆጠሩ የነርቭ ህዋሳት (ኒውሮንስ) ላይ ተጽእኖ በማሳደር ባህሪያችን ላይ ተጽእኖ ያደርሳሉ።
ኒውሮንስ (የነርቭ ህዋሳት) የሚሰኙት በአዕምሯችንን እና በማዕከላዊ ነርቭ ሥርዓታችን ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ የሰው ልጅ ባህሪይን የሚቆጣጠሩም ናቸው።
የሆድ እቃችን በአዕምሮ ውስጥ የሚገኙ ባህሪይን የሚቆጣጠሩ ሴሮቲኒን የሚባሉ የነርቭ አስተላላፊዎች (ኒውሮትራንስሚተርስ) በማምረት የሚኖረንን ስሜት ሊቆጣጠር ይችላል።
የሆድ እቃችን ዋነኛው ሚና ከምግብ የሚገኙ ንጥረ ነገሮችን መውሰድ ነው።
“በሰገራ ውሃ እና ንጥረ ነገሮችን ልናጣ አይገባም” የሚሉት ደግሞ በሕንድ የምግብ አፈጫጨት ሥርዓትን የሚያጠኑት ቬንካትራማን ክሪሽና ናቸው።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሆድ እቃ ጤና (ገት) ዶክተር የሚል ስያሜ ያገኙት ዶክተር ሜጋን ሮዚ በበኩላቸው በሆድ እቃችን ውስጥ ያሉ ማይክሮቦች አለመመጣጠን 70 በመቶ ከስር ሰደድ የጤና እክሎች ጋር እንደሚያያዝ ነው።
ከእነዚህም መካከል የልብ ህመም፣ የመተንፈሻ አካላት ህመሞች እና በተለምዶ ቁርጥማት ወይም የአንጓ ብግነት የሚሰኘው (ሪውማቶይድ አርታራይተስ) ይጠቀሳሉ።
ወደ 70 በመቶ የሚሆነው የሰውነታችን በሽታ የሚከላከሉ ህዋሳት በሆድ እቃችን ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ለዚያም ነው “የተሻለ የሆድ እቃ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ጠንካራ በሽታን የመከላከል ሥርዓት እንዳላቸው የሚያሳየው” ይላሉ።
እንዴት የሆድ እቃችንን ጤንነት ማሻሻል እንችላለን?
በሆድ እቃችን ያሉ ማይክሮቦችን ዓይነታቸውን ለመጨመር ቢያንስ 30 ዓይነት እጽዋትን (አትክልቶችን) በየሳምንቱ ልንመገብ እንደሚገባ በአውሮፓውያኑ 2018 በአሜሪካው ‘ገት ፕሮጀክት’ የተሠራውን ምርምር ተከትሎ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ብቻ ሳይሆን አዝርዕቶችን፣ ቅመማ ቅመሞችን እንዲሁም የለውዝ አይነቶችንም ልንመገብ ይገባል።
ወደ መገበያያ መደብሮች ስንሄድም የተለያዩ ዓይነት ፍራፍሬዎች እንዲሁም አትክልቶችን መግዛት ልብ ማለት እንዳለብን ነው ባለሙያዋ የሚመክሩት ነው።
በሳምንት ውስጥ የምንመገበውን ሥጋ ለምሳሌ በአሰር (ፋይበር) በበለጸገው ምስር ብንቀይረው በሆድ እቃችን ጤና ላይ ለውጥ እንደምናይም ዶክተር ሜጋን ምክራቸውን ይለግሳሉ።
በአሰር (ፋይበር) የበለጸጉ ምግቦች ሆዳችንን ቶሎ ይሞላሉ፣ ምግብ እንዲፈጭ እና የሆድ ድርቀትንም ይከላከላሉ ። የዩኬ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት አዋቂዎች በቀን 30 ግራም አሰር (ፋይበር) እንዲመገቡ ይመክራል።
ከሌሎች አዝርዕቶች በበለጠ ጤፍ በአሰር (ፋይበር) በከፍተኛ ሁኔታ የበለጸገ ሲሆን፣ አሰርን ለማግኘት እንጀራ አንዱ ተመራጭ ምግብ ነው።
እንዲሁም ገብስም ሆነ ሌሎች ጥራጥሬዎችን ሳንፈትግ አሰሩ ሳይወጣ መመገብ ሌላኛው አማራጭ ነው።
ከፉርኖ ዱቄት ከተሰራ ዳቦ ይልቅ በርካታ አዝርዕቶች ያላቸውን ዳቦዎች መመገብ፣ ቡናማ ሩዝ ተመራጭ ነው ይላሉ።
ድንች ሳይላጥ በመጋገር መመገብ፣ እንደ ባቄላ፣ ሽምብራ፣ ምስር፣ ወይም ሽምብራ ያሉ ጥራጥሬዎችም አሰር የምናገኝባቸው ምግቦች ናቸው።
በአሰር የበለጸጉ እና ካርቦሃይድሬት የያዙት (ፕሪቢዮቲክ) የተሰኙም የምግብ አይነቶች በሆድ እቃ ውስጥ ጤናማ ባክቴሪያ እንዲያድጉ በማድረግ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
በፕሪቢዮቲክ የበለጸጉ የሚባሉት ምግቦች መካከል ሙዝ፣ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ጎመን፣ አጃ፣ ብሉቤሪ፣ የወይን ፍሬ ይጠቀሳሉ።
በፓኪስታን የምግብ አፈጫጨት ሥርዓት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሃኒሻ ኬማኒ “በሃያዎቹ ዕድሜያችን የተመጣጠነ፣ በንጥረ ነገር የበለጸጉ ምግቦችን አመጋገብ ሥርዓት ቢኖረን ለረጅም ጊዜ ጤና ጠቃሚ ነው” ይላሉ።
በዚህ ዕድሜ ውስጥ የሚኖረው የምግብ ምርጫ ስር የሰደዱ ህመሞችን በመከላከል እንዲሁም ከአዕምሮ ጤና ጋር በአጠቃላይ ከሙሉ ደኅንነታችን ጋር ይገናኛል ይላሉ።
መጾም ወይም ደግሞ በየ12 ሰዓቱ ልዩነት መመገብ በሆድ እቃችን ያሉ ማይክሮቦችን በበለጠ እንደሚጠቅም ከምግብ ጋር የተያያዘ መጽሐፍ ያላቸው እና በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት ቲም ስፔክተር ያስረዳሉ።
የትኞቹ ምግቦችስ የሆድ እቃ ጤናችንን ይጎዳሉ?
በፋብሪካ የተቀነባበሩ እና የታሸጉ ምግቦች፣ አልኮል እና የትምባሆ ምርቶች ለሆድ እቃ ጤና ጎጂ እንደሆኑ ዶክተር ክሪሽና ያስረዳሉ።
በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች በሆድ እቃችን ውስጥ ያሉ ጥሩ ባክቴሪያዎችን የሚያጠፉ ወይንም መጥፎ ባክቴሪያዎችን የሚጨምሩ ንጥረ ነገሮችን ይዘዋል።
በተጨማሪ በየመንገዱ የሚሸጡ ንጽህና የጎደላቸውን ምግቦች ማስወገድ፣ አደገኛ ቫይረሶችን እና ባክቴሪያዎችን ለማስወገድ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ማጠብም ዶክተር ክሪሽና ለሆድ ጤናችን ጠቃሚ ነው በማለት ይመክራሉ።
ጭንቀት ራሱ በጨጓራችን ላይ አሲድ እንዲመነጭ እና ቁስለትን በመፍጠር እንዲሁም የሆድ እቃ ጤናችን ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል።
ከፍተኛ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች የማይክሮባዮምስ ዓይነታቸው ያነሰ እንደሚሆን ዶክተር ካትሪና ይገልጻሉ።

የሚሸጡ ፕሮባዮቲክስ እና የሆድ እቃ ምርመራ
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የሚሸጡ የፕሮባዮቲክስ ምርቶች ለተወሰኑ ጉዳዮች ጥቅም ላይ ሲውል ሊሠሩ አንደሚችሉ ነው።
“ፕሮባዮቲክሱን ስትወስዱ የትኛውን ሁኔታ ለማስተካከል ነው፣ የትኛውን ዝርያ እንዲሁም ለምን ያህል ጊዜ ነው የሚለው መታወቅ አለበት” በማለት ዶክተር ሜጋን ያስረዳሉ።
“በየመደብሮቹ ላይ የሚታዩት የፕሮባዮቲክ ምርቶች የሆድ እቃ ጤናን ምን ያህል እንደሚረዱም ሆነ በየቀኑ መውሰድ እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም” ይላሉ።
በአንዳንድ አገራት ኩባንያዎች የሰገራ ምርመራ በላብራቶሪያቸው በማድረግ የአንድን ሰው የሆድ እቃ ጤና ውጤትን ያሳውቃሉ።
ዶክተር ሜጋን እንደሚሉት ኩባንያዎቹ እንደሚሉት ሳይሆን በተወሰነ መልኩ ስላሉ የማይክሮቦች ዓይነት ግንዛቤ ሊሰጡ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
የሆድ እቃ ጤና ችግር ካለ የጤና ባለሙያዎችን ማናገር ተገቢ እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ የዩኬው ዶክተር እና የቴሌቪዥን አቅራቢው ዶክተር ኤክስ ናቸው።
