አቶ ጌታቸው ረዳ በድምጸ ወያኔ በርካታ ሚስጥር ይፋ አድርገዋል። ዶክተር ደብረጽዮንን ጨምሮ የተለያዩ አመራሮች የፕሪቶሪያውን ስምምነት “አድነን ፈርም” እያሉ ይገፏቸው እንደነበር ገልጸዋል። ይህን ባደረጉ ማግስት “ከጀግና ወደ ባንዳ” መወርዳቸውንም አመልክተዋል።
በትህነግና በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር መካከል የተፈጠረውን ልዩነትና ልዩነት መካረሩን ተከትሎ ይፋ እንዳደረጉት ከሆነ ከፍተኛ በጀት ተመድቦ ስማቸው እንዲጠፋ ዘመቻ እየተካሄደባቸው መሆኑንን አመልክተዋል።
ዳግም ጦርነትን አብዝተው እየተቃወሙ ያሉት አቶ ጌታቸው የትግራይ ህዝብና ካድሬው እንዲያውቀው የሰጡት ከሁለት ሰዓት የዘለቀ መግለጫ አሁን ላይ ያለው ልዩነት የስልጣን ሽኩቻ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ከሃያ አራት ሺህ በላይ ቁስለኛ ይዘው እንደነበር ያመለከቱት አቶ ጌታቸው፣ የተደርገው የሰላም አማራጭ ስምምነት ትጥቅ መፍታት፣ ትግራይን ሙሉ በሙሉ ለመከላከያ መልቀቅ፣ ሁሉም የትግራይ ተፎካካሪ ሃይሎች ያሉበት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም፣ እንደነበር አስታውሰዋል። ይህን ንግግራቸው አሁን ላይ የተቋቋመው የክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር በውሉ መሰረት እንዳልሆነና የፈደራሉ መንግስት በሆደ ሰፊነት አውቆ ዝም ማለቱን ሲናገር ለነበረው ማረጋገጫ ሆኗል።
“የተደራደርከውን የተቀመጥከው ከጥቁሮች ጋር ነው” በሚል የትግራይን ህዝብ የታደገውን፣ አድነን በማለት ሲማጸኑ የነበሩትን ሁሉ ነብስ ያተረፈውን ስምምነት የማራከስ ተግባራት ሲፈጸሙ መቆየታቸውን አቶ ጌታቸው አስረድተዋል።
ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ሳለ አስተያየት እንዳይሰጡ የተከለከሉበትን የትህነግ ግምገማ “ሃሳብ የነጠፈበት” ሲሉ የተቹት አቶ ጌታቸው የፕሪቶሪያው ስምምነት ባይፈረም ኖሮ ምን ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል። በወቅቱ ኤአመራሮቹን አግኝቻለሁ። ጦሩ ፈርሷል ብለውኛል። ተመልሰው ማገገም አይችሉም። ነገሮች አብቆቶላቸዋል” ሲል በወቅቱ የጻፉትን የውጭ ሚዲያዎች ያስታወሰው የአቶ ጌታቸው ንግግር፣ ዛሬ “ባንዳ” የተባሉት ይህን አደጋ ከቀለበሱ በሁዋላ መሆኑንን አመልክተዋል። ከላይ የጻፍነው ወዲ ሻምበል ከተረጎመው ላይ የወሰድነው ሲሆን፣ ከስር ቢቢሲ መርጦ በስፋት የዘገበውን ያንብቡ። ቢቢሲ ” ትግራይ ተጀምሮ ወደ አማራና አፋር ክልል እየተስፋፋ የሄደው” ሲል የሚገልጸው፣ ትህነግ በወረራ አፋርና አማራ ክልል ድረስ በመዝለቁ በሚል ተስተካክሎ እንዲነበብ እንጠይቃለን።
ደም አፋሳሹን የእርስ በርስ ጦርነት ለመቋጨት በተካሄደው የፕሪቶሪያ ድርድር የትግራይ ተወካይ የነበሩትን አቶ ጌታቸው ረዳን “መንግሥትን የሚያፈርስ ስምምነት ፈርመሃል” ሲል ህወሓት እንደወቀሳቸው ተናገሩ።
የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የመቋጨት ስምምነት የክልሉን መንግሥት እንዲያፈርስ እንዳደረገው እና ይሄንንም ተግባራዊ አድርገዋል ተብለው በፓርቲያቸው መተቸታቸውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ በህወሓት እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር መካከል ቅራኔዎች እየታዩ ባሉበት ወቅት ነው አቶ ጌታቸው ሰኞ ሐምሌ 22/ 2016 ዓ.ም. ከድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለተለያዩ ጉዳዮች ተናገረዋል።
ህወሓት “የተደራጀ ስም የማጥፋት ሥራዎች” ሲያካሂድብኝ ቆይቷል ሲሉት አቶ ጌታቸው “በውስጣዊ አለመግባባቶች፣ በፖለቲካዊ ሽኩቻዎች ምክንያት፣ አንዱ የጀመረውን እንቅስቀሴ ሌላው ስም ስለሚሰጠው” ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን መሥራት አልተቻለውም ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው ለሁለት ሰዓት ከሩብ ያህል ባደረጉት ዘለግ ያለ ቃለ ምልልስ በፕሪቶሪያው ስምምነት፣ በህወሓት ሕጋዊነት እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፋፊ ልዩነቶች ተከስተው አለመግባባት መፈጠሩን ግልጽ አድርገዋል።
በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተዛመተው እና ለመቶ ሺዎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነው ጦርነትን የቋጨውን የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ አፈሙዞች ጸጥ ብለዋል።
የጦርነቱን መቋጨት አስመልክቶ የትግራይ አመራሮች ወደ “ከተማ በመመለስ” ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ትግል እንድናካሂድ ዕድል ሰጥቶናል ብለዋል።
ህወሓትን በመወከል የፕሪቶሪያውን ስምምነት ከፈረሙት የትግራይ ክልል ልዑካን አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው፣ በአሁኑ ወቅት “መንግሥትን [የክልሉን] የሚያፈርስ ስምምነት ፈርመህ መጥተሃል” ተብለው በከፍተኛ የድርጅቱ አመራሮች እየተወቀስኩ ነው ብለዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ጦርነቱን ተከትሎ በትግራይ ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ፣ የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ ማስፈታት፣ መበተን እና ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ ማዋሃድ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግን ያካትታል።
በተጨማሪም የመከላከያ ሠራዊት የክልሉ መዲናን እንዲቆጣጠር እና የትግራይ አመራሮች እራሳቸውን ‘የተመረጠ መንግሥት’ ብለው መጥራት እንዲያቆሙ እንዲሁም ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚመሠረት የሚያደርግ ነበር።
- “በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል አለመተማመን አለ” አቶ ጌታቸው ረዳ13 የካቲት 2024
- የትግራይ ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ ማን ናቸው?24 መጋቢት 2023
- የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም ሁለተኛ ዙር ግምገማ በአዲስ አበባ ተካሄደ10 ሀምሌ 2024
አቶ ጌታቸው ረዳ በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በህወሓት መካከል የሻከረውን ግንኙነት ይፋ ባደረጉበት በዚህ ከድምጺ ወያነ ጋር ባደረጉት ቆይታቸው ስለቀረቡባቸው ወቀሳዎች ተናግረዋል።
“አሁን መንግሥት አፍርሰው ነው የመጡት እየተባልን ነው። ያኔ ጉዳዩ የመንግሥትነት አልነበረም፤ የትግራይ ሕዝብ በሙሉ በፌደራል ሠራዊት ስር እንዲገባ እጃችሁን ስጡ ስንባል ነው የነበረው። በወቅቱ የህወሓት ሊቀመንበር [ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል] ‘ዛሬ ካልፈረማችሁ ወደ በረሃ መውጣታችን ነው’ ብሎኛል” የሚሉት አቶ ጌታቸው አሁን የሚወቅሷቸው አካላት ስምምነቱን እንዲፈርሙ እንደነገሯቸው ገልጸዋል።
አክለውም “የፕሪቶሪያን ስምምነት በምንፈርምበት ሰዓት ምን ዓይነት ጭንቅ ውስጥ እንደነበርን አስታውሰዋለሁ።አሁን ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በኋላ ያኔ ስምምነቱ ካልተፈረመ አደጋ ላይ እንወድቃለን ሲል የነበረው አካል ‘መንግሥት እንድታፈርሱ ሥልጣን አልሰጠናችሁም – ስህተት ነው’ ሲል ከጅምሩ አልተቀበለውም ነበር ማለት ነው” ብለዋል።
ይህም ጊዜያዊ አስተዳደሩ የስምምነቱ አተገባበር የሚጠይቃቸውን ሥራዎች እንዳይሠራ እክል እንደሆነበት በማንሳትም ወቅሰዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት በትግራይ ክልል ምርጫ እስኪካሄድ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሠረት የሚያዝ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቶ ጌታቸው ረዳን የክልሉ ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር አድርገው እንደሾሟቸው ይታወሳል።
በወቅቱም በህወሓት አመራሮች መካከል የሥልጣን ፍትጊያ እንደነበርና ኃላፊነቱን ከመቀበላቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ “በእኔ ላይ ያነጣጠሩ” ያሏቸው የስም ማጥፋት ዘመቻዎች መካሄድ መጀመራቸውን እና እርሳቸው የሚመረጧቸው የካቢኔ አባላትን የማቋቋም ዕድል እንዳላገኙ ተናግረዋል።
“በአመራሩ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚያውቁት ጽሑፍ ተዘጋጅቶ በአንድ ቀን ከጀግና ወደ ባንዳ ወረድኩኝ።በዚህ ጽሑፍ ቤት ለቤት ቅስቀሳ ተደርጎበታል” በማለት የህወሓትን ጽህፈት ቤት በሚመሩ ግለሰቦች እና በድርጅቱ ውስጥ በሚገኙ አመራሮች የተቀነባባረ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደተካሄደባቸው በመግለጽ ከሰዋል።
“በመሆኑም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከጅምሩ አንስቶ ካቢኔ ከመምረጥ ጀምሮ እስከ ታች ወርዶ እንዲንቀሳቀስ እንዳያስችለው በችግር የተተበተበ ሆኗል” በማለት የአስተዳደሩ ዋነኛ ትኩረት መሆን የሚገባው ያሉት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ እና ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች መልስ እንዲያገኙ ማድረግ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ባለፈው መስከረም ወር በሰጡት ተመሳሳይ መግለጫ አስተዳደራቸው በዞኖች እና በወረዳዎች መንቀሳቀስ አለመቻሉን እንዲሁም ተቀባይነት እንዳያገኝ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ ሲሉ መውቀሳቸው ይታወሳል።
በተጨማሪ አቶ ጌታቸው ህወሓት በቅርቡ ያካሂደዋል ተብሎ ስለሚጠበቀው የድርጅቱ ጉባኤን የሚመለከት አስተያየት ሰጥተዋል።
ድርጅቱ ጉባኤ መካሄድ አለበት እንዲሁም ‘መሟላት ያለባቸው’ ሕጋዊ አሠራሮች ሳይሟሉ መካሄድ የለበትም የሚል አቋም ባላቸው አባላቶቹ ተከፋፍሎ ይገኛል።
በዚህ ከፍተኛ ክፍፍል ውስጥ ባለበት ወቅት ህወሓት በምርጫ ቦርድ እውቅና ከማግኘቱ በፊት ሊያካሂደው እንደማይገባ የተገለጸውን ጉባኤ ለማካሄድ ዝግጅት ላይ መሆኑን ተገልጿል።
የጉባኤው አላማ በድርጅቱ ውስጥ ‘በተሰባሰቡ ከፍተኛ አመራሮች ተጠልፏል’ ያለው የህወሓት ቁጥጥር ኮሚሽን አባላቶቹ ከአዘጋጅ ኮሚቴ ራሳቸውን እንዲያገሉ ማድረጉ ይታወሳል።
ድርጅቱ እስከአሁን ባካሄዳቸው ረጃጅም ስብሰባዎች “ወሳኝ የሕዝብ አጀንዳ ሲያነሳ አይተን አናውቅም። የሥልጣን ሽኩቻ ነው ያለው። ማን ስለምን ወደ ሥልጣን መጣ? በምን አጋጣሚስ መውረድ አለበት” በሚል ችግር ውስጥ ወድቋል ሲሉ አቶ ጌታቸው በቃለ መጠይቃቸው ላይ ጠቅሰዋል።
አሁን ያለው የድርጅቱ መሠረታዊ ችግር ሥልጣን እንደሆነ በመግለጽ ከዚህ ጋር በተያያዘ “ሁሉም የነበረውን ለማስቀጠል፣ በሥልጣን ላይ እያሉ በተፈጸሙ ስህተቶች ከተጠያቂነት ለማምለጥ እየተሯሯጡ ነው” በማለት ‘ያጡትን ሥልጣን ለማስመለስ፣ ሥልጣን ቀምቶኛል የሚለውን ደግሞ ለማስወገድ’ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር ጉባኤው በአመራሩ ውስጥ ያሉ ፖለቲካዊ ችግሮች የሚታረሙበት መሆን አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ ድርጅቱ “ጊዜው የሚጠይቀውን ሃሳብ ማመንጨት የማይችልበት ሁኔታ ላይ ነው” ሲሉ ተችተዋል።
“ሃሳብ በሌለበት የሚደረገው ጉባኤ ላይ የሚመረጠው ኃይል ምን ላይ ተመሥርቶ ነው ትግራይን የሚያስተዳድረው? የተቀሩት የፕሪቶሪያ ጉዳዮች በምንድን ነው የሚያስፈጽማቸው?” በማለትም ጊዜያዊ ፕሬዚዳንቱ ይጠይቃሉ።
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጉባኤ ከማካሄዱ በፊት “በሕጋዊ መንገድ መመዝገብ እንዳለበት” ማሳሰባቸው ይታወሳል።
አክለውም የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ መንግሥታቸው ያከናወናቸውን ሥራዎች ለተቃዋሚዎቻቸው በመጥቀስ “ሕግ ያሻሻልነው ህወሓት እና መሰል ፓርቲዎች በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ሕጋዊ ፓርቲ እንዲሆኑ [ነው]” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት የሕግ ማሻሻያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ነበረ።
የምርጫ ሕጉን ያሻሻለው ይህ የአዋጅ ማሻሻያ ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጽ ተግባር ተሳትፎ የነበረ የፖለቲካ ቡድን በፓርቲነት የሚመዘገብበትን ሂደት በዝርዝር ያስቀመጠ ነው።
ማሻሻያው የፖለቲካ ቡድኑ “ሕገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል” ሲል ይደነግጋል።
ከማሻሻያ አዋጁ መጽደቅ በኋላ ንግግሮች መደረጋቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ምርጫ ቦርድ ሥራውን ሠርቶ፣ የሚያጣራውን አጣርቶ በተሟላ መንገድ እንዲፈቅድላቸው።ዐቃቤ ሕግ ለምርጫ ቦርድ [ደብዳቤ] መጻፍ ነበረበት ጽፈናል” ብለዋል።
ዐቢይ ይህን ቢሉም ግን የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ አማኑኤል አሰፋ፤ “ይህ የአዋጅ ማሻሻያ የተሰረዘውን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል ሳይሆን እንደ አዲስ ለመመዝገብ የሚያስችል” መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ አማኑኤል አክለውም፤ “ወደ ምርጫ ቦርድ አመልክተን በዚያ አዋጅ መሠረት እንድንስተናገድ ነው የሚፈልጉት። እኛ ወደ ምርጫ ቦርድ ቴክኒካል ወደ ሆነው ጉዳይ እንደ አዲስ ለመመዝገብ ማመልከት ሳይሆን ፖለቲካሊ የተሰረዘውን ሕጋዊ ሰውነት ለማስመለስ የሚያስችል ፖለቲካዊ ውሳኔ በሚመለከተው የመንግሥት አካል እንዲሰጠን ነው የምንፈልገው” ሲሉ የፓርቲያቸው ውሳኔ አስረድተዋል።
የድርጅቱ ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በቅርቡ ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በአዋጁ መሠረት ለመመዝገብ ወደ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ማስገባታቸውን በመግለጽ በ15 ቀናት ውስጥ መልስ እንጠብቃለን ብለዋል።
ሆኖም በጠቀሱት ጊዜ ውስጥ ፍቃድ ካልተሰጣቸው ‘ፍቃድ አልሰጣችሁንም’ የሚል መልስ ይዘው ጉባኤውን እንደሚያካሂዱ ተናግረዋል።