በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሥር የሚገኘው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይፋ ያደረገው የአፍሪካ የጤና ክብካቤና የኢኮኖሚ ዕድገት ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ውጭ በሕገወጥ መንገድ እንደሸሸባት አስታውቆ፣ ይህ ገንዘብ ለጤናው ዘርፍ የምታውለውን 87 በመቶ በጀት እንደሚሸፍን አመለከተ።
መንግስት በሌቦች ተጠልፏል በሚል መነሻ ለቀረበው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “በኢትዮጵያ ዉስጥ መንግስታዊ ሌብነት የለም፣ ይህ ማለት ግለሰቦች፣ አመራሮች አይሰርቁም ማለት አይደለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ይህንኑ ጥያቄና ምላሽ ያደመጡ ” እንዴት መንግስታዊ ሌብነት የለም” ይላሉ በሚል ትችት ሰንዝረዋል። በተቃራኒው ደግሞ መንግስታዊ ሌብነት እንደሌለ የሚገልጹ የራሳቸውን ማብራሪያ በመስጠት የጠቅላይ ሚኒስትሩን አገላለጽ ደግፈዋል።
በኢትዮጵያ ሃላፊነትን፣ ግንኙነትንና አደራን በመጠቀም መዝረፍ የተለመደ ነው። በኢትዮጵያ ሌብነት ስለመኖሩና አሳሳቢ ችግር እየሆነ መምጣቱን መንግስት፣ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በስሙ ጥሩት አታሽሞንሙኑት. ሌቦች ናቸው” እያሉ ሲያወግዙት ይሰማል። በዚሁ መነሻ ነው “እንዴት ራሳቸው በአደባባይ ሌብነት ብለው እየገለጹ ተመልሰው መንግስታዊ ሌብነት የለም የሚሉት” ሲሉ ነቃፊዎች የሚሞግቱት።
“በኢትዮጵያ ዉስጥ መንግስታዊ ሌብነት የለም፥ ይህ ማለት ግለሰቦች፣ አመራሮች አይሰርቁም ማለት አይደለም” ሲሉ በገሃድ መአገራቸውን የሚጠቅሱ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የመንግስትን መዋቅር፣ ስልጣንና ተቋማትን በመጠቀም የተዘረፈ ሃብትን ህጋዊ የማድረግ ስራ እንደማይሰራ ለማመላከት መሆኑን ይጠቁማሉ።
ከ2003 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ ከአገር መውጣቱን የተመድ መረጃ አስደግፎ አመልክቷል። የሪፖርተሩ ብርሃኑ ፈቃደ ዘገባ አዲስ አበባ ከተማ በተጠራ የተቋሙ ስብሰባ ላይ የቀረበው ሪፖርት አጣቅሶ ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ አመታት የተዘረፈችውን ያብራራል። ይህን እንደምሳሌ የሚያነሱ “መንግስታዊ ሌብነት ማለት ይህ ነው” ሲሉ እንደማሳያ ያቀርባሉ።
“መንግስት ያገኘውን ብድርና እርዳታ በመንግስታዊ መዋቅር፣ በመንግስታዊ ተቋማትና በፖለቲካ ሹመኞቹ አማካይነት ህጋዊ ሽፋን በመስጠት የሚፈጽመው ዝርፊያ መንግስታዊ ሌብነት ነው” ሲሉ አስተያየት የሚሰጡ ግሎባል ፋይናንሺያል ኢንተግሪቲ ላይ ያወጣቸውን ሪፖርቶች ማገላበጥ በቂ እነደሚሆን ያመለክታሉ።
ባለፉት ስድስት ዓመታት አስራ አንድ ቢሊዮን ዶላር ስራ ላይ ሳይውል መንግስታዊ ሌቦች የዘረፉትን የአገሪቱን ዕዳ የከፍለ መንግስት፣ የእዳ ደረጃዋንም 17.5 ከመቶ የቀነሰና አንድም የኮሜርሻል ብድር ያለወሰደ መንግስትን በልመናና በብድር የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ ሽፋን ሰጥቶ ይዘርፋል ማለት ሚዛን እንደማያነሳ እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ።
ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በ36ኛዉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሳበ ላይ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን በሚመለከት የተለያዩ ነጥቦችን ሲያነሱ “ሌብነት ነቀርሳ ነው፤” ሀገርን ይበላል፡፡ ትንሽም ሆነ ትልቅ ሌብነት መጥፋት አለበት፥ ለዚህም ነው መንግስት የህግ ማሻሻያዎችን እያደረገ ያለው” ብለዋል፡፡ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅም ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንን አመላክተዋል።
የሪፖርተሩ ብርሃኑ ፈቃደ ያቀናበረው በፌብሩዋሪ 13፣ 2019 ያጣቀሳቸው መረጃዎች በገሃድ ሲቀርቡ ተገኝቶ ያቀረበውን ሙሉ ሪፖርት ከስር ያንብቡ። በሪፖርቱ መንግስታዊ ሌብነት ምን ማለት እንደሆነ ይታያል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሥር የሚገኘው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይፋ ያደረገው የአፍሪካ የጤና ክብካቤና የኢኮኖሚ ዕድገት ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ውጭ በሕገወጥ መንገድ እንደሸሸባት አስታውቆ፣ ይህ ገንዘብ ለጤናው ዘርፍ የምታውለውን 87 በመቶ በጀት እንደሚሸፍን አመለከተ።
ማክሰኞ የካቲት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይፋ የተደረገው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2003 እስከ 2012 ባሉት ዘጠኝ ዓመታት በየዓመቱ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሕገወጥ ገንዘብ በሚያሸሹ አካላት ሳቢያ ተጎጂ ሆናለች ብሏል። በዚህ ሳቢያም ለጤናው ዘርፍ የምትመድበው ዝቅተኛ በጀትም በሚሸሸው ገንዘብ ምክንያት ከባድ ተፅዕኖ ውስጥ እንደቆየ አመላክቷል።
ኢትዮጵያ ከጠቅላላ ኢኮኖሚዋ (ከአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት አኳያ) አንድ በመቶ ለጤናው ዘርፍ ትመድባለች ያለው ሪፖርቱ፣ በአንፃሩ በየዓመቱ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ እየሸሸባት በመሆኑ 87 በመቶውን የጤናውን ዘርፍ በጀት ወደ ውጭ የሚሸሸው ገንዘብ እንደሚሸፍነው ሪፖርቱ አሥፍሯል።
ከዚህም በተጓዳኝ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ ከሚያወጣው ወጪና ለዕዳ ክፍያ ከሚያውለው ገንዘብ ተቀናንሶ ሲሰላም፣ አገሪቱ በየዓመቱ የ2.5 ቢሊዮን ዶላር የበጀት ክፍተት እንደሚገጥማት ታውቋል።
እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2017 ባለው ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት አማካይ ጠቅላላ የዕዳ ክምችት መጠን 55 ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰ ተመድ አውስቶ፣ ከሕገወጥ ገንዘብ የማሸሽ ተግባር ባሻገር ለዕዳ ክፍያ የሚውለው ከፍተኛ ገንዘብም እንደ ጤናው መስክ ባሉት መሠረታዊ ዘርፎች ላይ ጫና ማሳደሩን አስታውቋል።
እንዲህ ያሉትን እውነታዎች ያጎላው የተመድ ሪፖርት፣ እ.ኤ.አ. ከ2003 እስከ 2012 ባለው ጊዜ ውስጥ አፍሪካ በጠቅላላው ከ300 እስከ 600 ቢሊዮን ዶላር በሕገወጦች ገንዘብ የማሸሽ ድርጊት ሳቢያ ማጣቷትን አመልክቷል። ከጤናው መስክ አኳያም አገሮች ከዓመታዊ በጀታቸው አምስት በመቶ ለጤና ዘርፍ ይመድባሉ ተብሎ ቢገመት፣ በአፍሪካ ለጤናው መስክ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ የ66 ቢሊዮን ዶላር ክፍት እንደሚታይ ይፋ አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበትና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከዳንጎቴ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ባሰናዳው የ“አፍሪካ ቢዝነስ ሔልዝ ፎረም 2019” በተሰኘው መድረክ ላይ የናይጄሪያ ቢሊየነር ሐጂ አሊኮ ዳንጎቴ ልጅ ሐሊማ ዳንጎቴ ይፋ እንዳደረገችው፣ የዳንጎቴ ግሩፕ ኩባንያዎች ከታክስ ተቀናሽ በኋላ ከሚያስገቡት ትርፍ ውስጥ በአፍሪካ ጤናው ዘርፍ እንዲውል የአንድ በመቶ ገቢያቸውን ያውላሉ።
እ.ኤ.አ. በ1994 የተመሠረተው የዳንጎቴ ፋውንዴሽን ከምሥረታው ጀምሮ፣ ለጤናና መሰል የበጎ ተግባራት የሚውል የ1.5 ቢሊዮን ዶላር በጀት በመመደብ ድጋፍ ሲያደረግ መቆየቱን የፋውንዴሽኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የአፍሪካ መንግሥታት ብቻቸውን ከፍተኛ የጤና ክብካቤ ችግሮች በሚስተዋሉባት አፍሪካ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ እንደማይችሉ በማመን፣ ድጋፍ ለማድረግ በዳንጎቴ ፋውንዴሽን አማካይነት መሰባሰብ የጀመሩት የአፍሪካ ባለሀብቶች፣ ለጤናው ዘርፍ የአፍሪካ የቢዝነስ ጥምረት የተሰኘ መድረክም በአዲስ አበባው ፎረም ይፋ አድርገዋል።
የዓለም እግር ኳስ ኮከቡ ኮትዲቯራዊ ዲዲዬር ድሮግባ፣ በጤናና በትምህርት መስክ ለአፍሪካውያን ድጋፍ የሚያደርግበትን የዲዲዬር ድሮግባ ፋውንዴሽንን እንቅስቃሴዎች በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥቷል።
በዚሁ መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ጨምሮ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ፣ የቦትስዋና ፕሬዚዳንት ሞክዊትሲ ማሲሲአ፣ እንዲሁም የኬንያ፣ የግብፅና የሌሎች አገሮች የጤና ሚኒስትሮች ስለአገሮቻቸው የጤና ዘርፍ እንቅስቃሴዎች ገለጻ አቅርበዋል።