ወደ ኤርትራ በረራ ባለማድረጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደማይጎዳ ይልቁኑም ተጎጂዎቹ ወደ ኤርትራ የሚጓዙ ተጓዦች ብቻ እንደሆኑ ተመለከተ። የኤርትራ ሲቪል አቬሽን ውሳኔውን መልሶ እንዲያጤነው እንደሚጠይቁ አቶ መስፍን ጣሰው አስታወቁ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው ዛሬ እንዳስታወቁት የኤርትራ ሲቪል አቬሽን ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሚያደርገው በረራ ከመስከረም 30 / 2024 ጀምሮ እንዲቆም የሚያሳውቅ ደብዳቤ መላኩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ነው።፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው “የሚጎዱት ወደ ኤርትራ የሚጓዙ ተጓዦች ናቸው” ሲሉ በውስጠ ታዋቂነት አየር መንገዱ ወደ ኤርትራ በረራ በማቆሙ የሚደርስበት አንዳችም ኪሳራም ሆነ ጉዳት እንደሌለበት አመልክተዋል። እሳቸው ባይናገሩትም አሰራሩን የሚያውቁ በአገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ፍላጎት በማደጉ አስቀድሞ አየር መንገዱ የሽግሽግ ስራ ማከናወኑን ጠቁመዋል። በዚሁ መሰረት የኤርትራ አቋም በዚሁ ከቀጠለ ወደ ኤርትራ ሲበሩ የነበሩ አውሮፕላኖች ለአገር ውስጥ ፋልጎት ማሟያ ይውላሉ። ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ ኤርትራዊያን የሚከፍሉት ብር በመሆኑ ለአየር መንገዱ ለውጥ የለውም።
ከቅርብ ወራት በፊት ከኤርትራ ሲቪል አቬሽን ቅሬታ ቀርቦላቸው እንደነበር ያልሸሸጉት አቶ መስፍን፣ ቅሬታውም ከተሳፉሪዎች ሻንጣ መዘግየት ጋር ተያይዞ የተነሳ ነበር። ተጓዟች ብዙ ሻንጣ ስለሚይዙ ከክብደቱ አንሳር በሌላ አውሮፕላን የመላክ አሰራር መከተላቸው ለሻንጣ መዘግየት ምክንያት እንደሆነም ዋና ስራ አስፈጻሚው በመግለጫቸው አመልክተዋል። በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ዱቄትና የሚበሉ ነገሮች ወደ ኤርትራ እንደሚጫን ይህም ክብደቱ ከፍተኛ እንደሆነ ቀደም ሲል ሲገለጽ እንደነበር የሚታወስ ቢሆንም ሃላፊው ይህን አስመልክቶ ያሉት ነገር የለም።
“ወደ ኤርትራ የሚጓዙ ተጓዦች ብዙ ሻንጣ ይሸከማሉ፤ ሁሉንም ማስተናገድ ባለመቻላችን በሚቀጥለው በረራ ሻንጣዎችን እንልክ ነበር “ሲሉ በደምሳሳው የክብደት ጉዳይ ሻንጣንና ባለቤትን እንደለየ ያመልከቱት አቶ መስፍን፣ ከዚህ በተጨማሪ በመጋቢት ወር የኤርትራ ሲቪል አቬሽን ከ737 አውሮፕላን ውጪ ከፍ ያለ የመንገደኞች ማመላለሻ መጠቀም እንዳይችሉ፣ በሳምንት ከ10 በረራ በላይ እንዳያከናውኑ እግድ ጥሎ እንደነበር አቶ መስፍን ገልጸዋል።
በዚህ የተነሳ የኤርትራ ተጓዦች ከሻንጣቸው ጋር እንዲጓዙ ለማስቻል የተሳፋሪዎችን ቁጥር ተቀንሶ እንደነበር በመግለጫው ተመልክቷል። ተጓዦች ከሻንጣዎቻቸው ጋር እንዲጓዙ ከተደረገ በኋላ ይህ ነው የሚባል ቅሬታ እንዳልተሰማም ተገልጿል።
ገደቡን በማንሳት ሰኔ መጀመሪያ ላይ ሌላ ደብዳቤ ለአየር መንገዱ መላኩን ያመለከቱት አቶ መስፍን፣ የቀርበውም ጥያቄ በረራዎችን ወደ አስራ አምስት ማሳደግና አየር መንገዱ ትልልቅ አውሮፕላኖች መጠቀም እንዲችል የሚፈቅድ ነበር። ይሁን እንጂ በጥያቄው መሰረት ወዲያውኑ ተግባራዊ ማድረግ አለመቻሉን፤ ይህም የህነው የአውሮፕላን እጥረቶች ሳቢያ መሆኑንን አመልክተዋል። አያይዘውም በዘረዘሯቸው ምክንያቶች ቀደም ሲል በነበረው አሰራር መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
ይህን ካሉ በሁዋላበመጨረሻ ለአየር መንገዱ ከመስከረም 30/2024 ዓም በተላከው ደብዳቤ አየር መንገዱ ማዘኑን አቶ መስፍን ተናግረዋል። ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ወደ ኤርትራ የሚደረገውን በረራ ያገደው ደብዳቤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ክስ ማቅረቡን ዘርዝረው “በጣም አዝነናል” ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ “ይህ ሁሉ ሲሆን እንደ ዓለም አቀፍ አሰራር ቅሬታዎቹ ላይ እንወያይ ተብሎ ጥያቄ አልቀረበልንም፤ የነበሩ ችግሮች ላይ ቀደም ብለን መፍትሔ ሰጥተናል” ሲሉ ሃዘኔታው ዓለም ዓቀፍ አሰራርንና ውይይትን ወደሁዋላ የገፋ በመሆኑም ጭምር እንደሆነ አመላክተዋል።
“አሁንም የኤርትራ ሲቪል አቬሽን ውሳኔውን እንዲያጤነው እንጠይቃለን፤ ይህን የማይሆን ከሆነ የሚጎዱት ግን ወደ ኤርትራ የሚጓዙ ተጓዦች ናቸው” ያሉት አቶ መስፍን ግልጽ ባይናገሩትም አየር መንገዱ የሚያጣው ምንም ነገር እንደሌለ ጠቁመዋል።
ኤርትራ ያላወራረደችው 2.5 ሚሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕዳ እንዳለባት ጠሰን መዘገባችን የሚታወስ ነው። 7.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የአውሮፕላን ችግር ስላለበት ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ ካቆመ በሌሎች የበረራ አውታሮች ለመተካት ቅድም ስራው መጠናቀቁን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አመልክተዋል።