በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚተላለፉት የአመጽ ጥሪዎች አነጋጋሪ ናቸ። ጥሪዎቹን ተከትሎ አስተያየት ለመስጠት የሚሞክሩ ጥሪውን ያስተላለፉትን አካላት ማንነት ለሚያውቁ ጭራሽ ግራ እንደሚጋባቸው በተደጋጋሚ ይገልጻሉ። የፈጠራ መረጃ በማሰራጨት ለዓመጽ ጥሪው ማገዶ የሚያቀብሉ ሚዲያዎችና በርካታ ተከታይ ያላቸው አካላት ጉዳይ ቀና ለሚያስቡ ዜጎች የዘወትር ግርምት እንደሆነባቸው የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም።
በኬንያ የታክስ አመጽ ተከትሎ ለኢትዮጵያዊያን ጥሪ በዚሁ ከላይ በተገለጸው አግባብ እየታየ ነው። በስልትና በገሃድ ተናበው ኢትዮጵያ ውስጥም ተመሳሳይ ዓመጽ እንዲካሄድ ቅስቀሳ እየተካሄደ ነው። የቀሰቀሳ ጥሪው ደግሞ “አውድም፣ አቃጥል፣ አተራምስ” እንጂ መሰረት ያለውና የተደራጀ ፖለቲካዊ ግብ ያለው አለመሆኑ አሳዝኝ ሆኗል።
ልጆቹን ጭኖ ወደ ትምህርት ቤት እያደረሰ መሆኑንን የሚናገር አንድ የማህበራዊ ሚዲያ ፊት አውራሪ በኢትዮጵያ ወጣቶች እንዲያምጹ፣ አቅማቸው የቻለውን ሁሉ እርምጃ እንዲወስዱ ሲቀሰቅስ ነበር። ይህ ከብዙ ተመሳሳይ ጥሪ አቅራቢዎች አንዱ የሆነው የአውሮፓ ነዋሪ ልጆቹ እንዲማሩለት ወደ ትምህርት ቤት እያደረሰ የድሃ ልጆች ወደ እሳት እንዲማገዱ ጥሪ ሲያደርግ ከስሩ ላይክና አበባ የሚበትኑ ነበሩ። አንዳንዶች ደግሞ ” መጀመሪያ ልጆችህን ልካቸው” በሚል የተሳለቁ የገባቸው ነበሩ።

በኬንያ የወደሙ የህዝብ መናፈሻዎችን፣ የህዝብ መገልገያዎችን፣ ፓርላማውን እንዲሁም ሌሎችን ተቋማት ምሳሌ በማድረግ ” ልክ እንደ ጀግኖቹ ኬንያዊያን አውድሟቸው” በሚል በገሃድ ጥሪ ያቀረቡ የጎዳና ዓመጽ ያስነሱት ተቃዋሚዎች የናይሮቢ ነዋሪዎችንም ሆነ የመንግስትን ንብረት ሙልጭ አድረገው ስለመዘረፋ፣ ነዋሪውችም በዝርፊያው ባዶ እጃቸውን መቅረታቸውን አልተነፈሱም።
በገሃድ ለሚታወቁና በሚታወቁ ሚዲያዎች የሚጽፉ፣ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጥቃቅን ጉዳዮችን እየነቀሱ አጀንዳ የሚያሰራጩና ህዝብን ምሬት ውስጥ እንዲገባ የሚያደራጁ፣ “የኬንያው አመጽ እንዴት ተጀመረ? እነማን አደራጁት? እንዴት የግንኙነት ኔት ዎርክ መሰረቱ?” በሚል የስልጠና ያህል በተከታታይ እየጻፉ ነው።
ፕሬዚዳንት ሩቶ ወደ አሜሪካ ሲሄዱና በዋይት ሃውስ ቀይ ምንጣፍ ሲራመዱ ” ኬንያን አከበሯት፣ አስከበሯት፣ ይህ ለኢትዮጵያ ሃፍረት ነው” በማለት መንግስትን እየነቀፉ በግልጽ የጻፉ ዛሬ ተመልሰው አመጹን ወደ ኢትዮጵያ በማከፋፈል ላይ ናቸው። አመጹ የተቀሰቀስው እነሱ ጀግና” ያሉዋቸው ፕሬዚዳንት ሩቶ አሜሪካ ሆነው የተጫኑትን ጭነት ኬንያ ደርሰው ካራገፉት በሁዋላ ስለመሆኑ እነዚሁ የአገራችን ጉዶች ባላየ አልፈውታል።
ፕሬዚዳንት ሩቶ አሜሪካ ሄደው 1000 ወታደሮችን ወደ ሃይቲ ለመላክ ከመፈረም ጀምሮ በዓለም ገንዘብ አበዳሪዎች እጃቸውን ተጠምዝዘው የታክስ ማሻሻያ አዋጅ እንዲያውጁ የታዘዙትን አገራቸው በተመለሱ ማግስት ተግባራዊ ማድረጋቸውን “ኬንያን አኮሯት፣ ኢትዮጵያ ነበረች በቦታው መገኘት የነበረባት። መለስ ቢኖሩ ኖሮ…።” በማለት ሲመጻደቁ ለነበሩ “የኢትዮጵያ ልጆች” ሩቶ ዛሬም ጀግናቸው ናቸው።
በነጩ ቤተመንግስት የኬንያን አንድ ሺህ ወታደሮች ወደ ሃይቲ መላካቸውን ያደነቁና ስምምነቱን የኬንያና የአሜሪካ ታላቁ ወዳጅነት ውጤት እንደሆነ ሲሰብኩ የነበሩ “ዓለም ዓቀፍ ጋዜጠኞች” የሃይቲው ጋንግሰተር መሪ የኬንያ ወታደሮች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ጉዳያቸው አልነበረም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ይህን ጥያቄ አስቀድማ ውድቅ ማድረጓ ከተገለጸ መንግስትን የማጣጣሉ ዘመቻ ይከሽፋልና።
አራጅ ስለሆነ ባር ቢኪው የሚባለው የሃይቲ ወነበዴዎች መሪ “ኬንያዊያን ምን ሊሰሩ እዚህ ይመጣሉ? እኛ ላይ ብር ሊሰሩብን አይደል ግደሏቸው” የሚል መመሪያ ሰጥቷል። ይኸው ሰው ለአልጀዚራ ” ሩቶን እንበቀላለን” ሲልም ዝቶ ነበር። ይህ ሁሉ አደገኛ የሞት ዜና የታወጀው የሃይቲን 80 ከመቶ የሚቆጣጠሩት፣ በሚቆጣጠሩት ቦታ ሁሉ እንዳሻቸው የሚዘውርፉ፣ የሚገድሉ፣ የሚደፍሩ ጋንጊስተርስ መሂናቸው ትርጉሙ ለኢትዮጵያዊያን ጥልቅ በመሆኑ ለአገራችን የዓመጽ ጠማቂዎች ይህ ህዝብ ዘንዳ እንዲደርስ አይፈለግም።
የፕሬዚዳንት ኡሁሩ ምክትል የነበሩት ሩቶ በስልታን ዘመናቸው ልክ እንደ ኡህሩ ሁሉ በጄኖሳይድ መወንጃላቸውን የሚያስታውሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይንም በተመሳሳይ በጄኖ ሳይድ ክስ ለማስፈራራት የተሞከረው ሙከራ መክሸፉን ዛሬ ያስታውሳሉ። አብይ አህመድ ላይ ከዛሬ ነገ ይከፈታል የተባለውና ትህነግ ነጋ ጠባ ሲያስተጋባው የነበረው ዜና ውድቅ መሆኑ፣ አሜሪካም ፋይሉን መዝጋቷ አይዘነጋም። የሩቶ ግን እንዳለ ነው። አንዳንድ ተንታኞች ሩቶን በዚህ የክስ ፋይል አስፈራርተው እዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ እነደጣሏቸው እየተገለጸ መሆኑም ለኢትዮጵያዊያን ዜናው እንዲደርሳቸው አይፍለግም።
ኬንያ የምስራቅ አፍሪቃ ብቸኛዋ የኔቶ አጋር አገር እንደሆነች ይፋ ሲደረግ ” ኬኒያ ወሰደችው አፈሰችው ኢትዮጵያ ተነጠቀች ሩቶ በአሜሪካ!” በሚል ርዕስ ዘሃበሻ ባሰራጨው ዜና ” ኢትዮጵያ እንዲህ ያለ መሪ ላይ ትውደቅ” በሚል ሰፊ የውዳሴ ዜና ለሩቶ አጉርፎ ነበር። እዛው ዜና ስር ” የኬንያ ማደግደግ የሚደነቅ ሳይሆን የሚወገዝ ነው::የአፍሪካውያን የቅኝ ተገዥነት ክፉ ደዌ ዛሬም አልሻረም ::የናቶ ተለጣፊ መሆን ጊዜያዊ ጠንቀኛ ጥቅም እንጅ ዘለቄታዊ ጥቅም ለአፍሪካ አይሰጥም ::እንደውም የአውሮፓ ሃያላን ከገናናዋ አሜሪካ ጋር ያላቸው ልዩነት መስፋፋት መጀመሩን በፓለስታይን የይሁዲዎች ጭፍጨፋ እየተባባሰ ለፓለስቲያን እውቅና መስጠታቸው አመልካች ነው። ” ሲሉ ፓስተር ዲጎኔ ሞረቴው የተባሉ አስተያየታቸውን አስፍረው ነበር።
ኬንያ የአሜሪካ ልዩ አጋር እንድትሆን እንዳስቻሉ ተደርገው በአገራችን ሚዲያዎች ከውስጥና ከውጭ የተሞካሹት ፕሬዚዳንት ሩቶ በዕዳ እየሰመጠች ያለችው ኬንያ ላይ በግድ የተጫነውን የታክስ ማሻሻያ ዓይነት ማስገደድን ኢትዮጵያ አልቀበልም ማለቷን ቢያውቁም ያሉት ነገር የለም። ይልቁኑም “ኢትዮጵያ ብሯን ልታገሽብ ነው” በሚል ያልተጨበጠ ዜና ኢኮኖሚውን የሚያናጋ ዜና አሁን ድረስ እየረጩ ነው።
ሮይተርስ ኢትዮጵያ በዓለም የገንዘብ አበዳሪው ተቋም የደረሰባትን ጫና ዘርዝሮ ባሰራጨው አስተያየት ተኮር ጽሁፍ ላይ የቀረቡ ጭብጦች እንደሚያሳዩት መንግስት የደረሰበት መከራ እጅግ ከባድ ነበር። ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ከፍላ ከተቀረቀረችበት የእዳ ዋሻና ከገባችበት የዕዳ መስመር ጫፍ በመጠኑ ያፈገፈገችው ኢትዮጵያ፣ በተበዳሪነት የተመደበችበት ደረጃ መሻሻሉ ሳይገልጽ የአጠቃላይ አገራዊ ኢኮኖሚዋ ሰባና ሰማኒያ ከመቶ ዕዳ ለሆነባት ኬንያ የሚያለቀልቁ እጆች የበዙባትን ኢትዮጵያ “ያልታደልሽ” ሲሉ በርካቶች ይገልጿታል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ሙከራ ከጠላት አገሮች ጋር በመሆን እያወገዙና እየተቃወሙ ያሉት “ኢትዮጵያዊያን” ዛሬ በኢትዮጵያ ያለውን የኑሮ ውድነት ተንተርሰው “አብይ የገነባውን መናፈሻ አውድሙ” እያሉ ነው። የባህር በር ባለቤት መሆን በአገር ደረጃ ማንም መንግስት ቢመጣ ጠቃሚ መሆኑ እጅግ ግልጽ ጉዳይ ሆኖ ሳለ መንግስትን በመጥላት ሂሳብ ለሶማሌ፣ ለግብጽና ለኤርትራ ማደር የተመረጠበት ዘመን ላይ መደረሱ በርካቶችን አሳዝኗል።
መንግስትን መቃወምና መተቸት የሚዲያ ተግባር ቢሆንም የኢትዮጵያን ሚዲያዎች በአብዛኛው ለመገምገም እንደሚቸግራቸው ባለሙያዎች በተደጋጋሚ በተለያዩ መድረኮች ላይ ገልጸዋል።
“መረጃ ቲቪ” በሚባለውና በሻዕቢያ የሚረዳ ሚዲያ ላይ የሚሰራው ዘመድኩን “ዘመዴ” ለተከታዮቹ የጻፈውንና በሚዲያው ያሰራጨውን ከላይ ለጥፈነዋል ይመልከቱ።
ከዚህ ቀደም “የአባይ ግድብ ተሸጠ፣ አብይ አህመድ ግድቡን አስመልክቶ ለግብጽ እንዲመች ሆኖ የቀርበውን ሰነድ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች እንዲፈርሙ በስክ አዘዙ” ያሉ፣ ይህ እስከተጻፈ ድረስ ማረሚያ ወይም ይቅርታ አልጻፉም። “የኢትዮጵያ ጦር ሶማሌን ወረረ” በሚል እንደ ባዕድ የሚከሱ ዜናው ሃሰት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በጎ ውይይት ማድረጋቸውን በወጉ አልዘገቡም። በረሃብ በየትምህርት ቤቱ ሲደፉ የነበሩ ህሳጻናት ጠግበው መብላታቸው ዜናቸው አይደለም። የመንገድ ግንባታና የኮሪዶር ልማት ቅንጦት ነው። አስር ሚሊዮን የሚጠጋ የአዲስ አበባ ነዋሪ መረማመጃ አጥቶ እንደ አህያ በሚጋፋባት ከተማ መረማመጃ አስፍቶና አስውቦ ማዘጋጀት አርመኔነት ተደርጎ እየተሳለ ነው።
የሚያስደንቀው ህጻናትና አዛውንቶች ማረፊያ አጥተው ከተማዋ ክፍት ቦታ ሁሉ እየታደነ ሲቸቸብ፣ መናፈሻና የኳስ ሜዳዎች እየታጠሩ ሲዘፈፉ ዝም ብለው የኖሩ ዛሬ መናፈሻ እንዲቃጠል፣ የኮርሪዶር መንገድ እንዲያፈርሱ፣ የሳይንስ ማዕከልንና አብርሆት ላይብረሪን እንዲያፈርሱ፣ ቤተመንግስትን እንዲወሩ ወዘተ ጥሪ እያቀረቡ ነው። ለምን ተቋማት እንዲፈርሱ እንደሚፈለግ ግን ምክንያት ዘርዝረው አያስረዱም።
በሃይማኖት ስም ቀስቅሰው መጨረሻ ላይ “ቤተመንግስት ውረሩ” ብለው ያዘዙ በጠሩት የሃይማኖት ሰልፍ ውስጥ በሚነሳ ሁከት ለሚሞቱ ወገኖች ቅንጣት አይሳሱም። ሁከቱን በሚከፈላቸው ገንዘብና ጥቅም የሚያሰሉት እነዚህ ክፍሎች መስመር የያዘ፣ መሬት የነከሰ፣ የተደራጀ፣ መነሻና መድረሻ ያስቅመጠ የህዝብ ትግል ጊዜ ስለሚወስድ አይፍለጉትም። አገር ስለማያወድምና ሁከትን ስለሚያስወግድ ስፖንሰር አድራጊዎቻቸው አይፈልጉትምና ዘወትር ምርጫቸው የትርምስ፣ የሞትና የውድመት መንገድ ብቻ ነው።