የአማራ ህዝብ ማንም ተነስቶ የሚፈተፍትበት ፖለቲካ ሰለባ እንደሆነ፣ አብሮ ለመታገል፣ ለማኩረፍና ለመቆጣት፣ ብሎም በተደራጀና በሰከነ አግባብ ጥያቄ ለማንሳት ከበቂ በላይ ምክንያት ያለው ህዝብ መሆኑ፣ በዚሁ ሳቢያ ይህ ታላቅ ህዝብ ደሙን በሊትር በማይታወቅ ዋጋ እየቸረቸሩ ለሚነግዱበት አቅለ ቀላሎች ሲሳይ እንደሆነ በርካቶች ድምዳሜ ላይ እየደረሱ ነው።

ይህ ድምዳሜ ዝም ብሎ በወፍ ዘራሽ የመጣ ሳይሆን በገሃድ በሚታየው የክልሉ ወቅታዊ ቁመና፣ በአማራ ህዝብ ስም ከየአቅጣጫው በሚሰሙ ተግዳሮቶች ሳቢያ ነው። “ተቀብቻለሁ፣ አንቂ ነኝ፣ተንታኝ ነኝ፣ ጋዜጠኛ ነኝ፣ አርቲስት ነኝ፣ ተወዛዋዥ ነበርኩ፣ ተኳሽ ነኝ፣ ጦር አለኝ፣ ዩቲዩበር ነኝ ወዘተ ” የሚሉ ድንኳን ሰባሪ ፖለቲከኞች መምሽቶ በነጋ ቁጥር ሰፈር እየቀያየሩ እንዳሻቸው የሚንጡት የአማራ ክልልና ህዝብ እጅግ አሳዛኝ ነው። ያሻቸው ተነስተው የሚውረገረጉበትና ኪሳቸውን የሚያደልቡበት የአማራ ህዝብ ደም የሚታደገው መጥፋቱ ደግሞ ሌላ ህመም ነው።
ትናንት የተናገሩትን መልሰው የማይደግሙ፣ ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን በጋራ፣ የበለጠ ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን እየተጣሉ በግል ወገን፣ ደምና፣ አካባቢ እየመረጡ የአማራን ህዝብ ተቀራምተው የሚነግዱበት ዩቲዩበሮች፣ አክቲቪስት ነን ባዮችና የጋዜጠኛ እራፊ ላያቸው ላይ ጣል ያደረጉ አቅለ ቢሶች የሚያንቦራጭቁት የሱቅ በደረቴ ዓይነት ፖለቲካ ዛሬ ላይ የደረሰበት ደረጃ ሰክነው ለሚያስቡ አስደንጋጭ ሆኗል። ህዝቡንም አማሯል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን የሚያስቡ “አባቶቻችን ችግር ቢኖርባቸውም በአሁኑ ደረጃ እንደሚታየው ሴረኞች አልነበሩም። ሞራላቸውም የላሸቀና ለብልጭልጩ ሁሉ የሚቃዡ የበዙባቸውም አልነበሩም። ጥቂት ባንዳዎች ቢኖሩም ለአገራቸውና ለወዳጆቻቸው ሁሉ ሟቾች ነበሩ። ከምንም በላይ እምነት ነበራቸው። ፈጣሪያቸውንም ይፈሩ ነበር። የዕምነት ደጅ ላይ ቸርቻሪዎችም አልነበሩም። አሁን ላይ እንደሚታየው የሃሰት ካባ፣ የነብይነት ማዕረግ ተሸክመው የሚወሰልቱ አልነበሩም። ዛሬ ድረስ የሚያወዛግበንን ጥፋት ያኖሩልን ጥቂት አጥፊዎች ቢኖሩም የሚልቁት የሚወደስ እንጂ የሚኮንን ስብዕና ባለቤት አልነበሩም” ሲሉ በሰው ልጆች ስቃይና ደም በሚነግዱት የዘመናችን ጉደኞች መደነቃቸውን የገለጹና በዚሁ ሚዲያ አስተያየት የጻፉ ነበሩ።
እነ ዘመድኩን፣እነ ሃብታሙ፣ እነ ምናላቸው፣ እነ አበበ በለው፣ አስመራ ተቀብተው የመጡት የኢሳት የቀድሞ ተዋንያኖች፣ በየስፍራው ክላሽ ተሸክመው ፎቶና ቪዲዮ የሚያከፋፍሉ ጀግኖች፣ እነዚህኑ ተከትለው የሚያጨበጭቡ፣ በሻዕቢያ መሪነት መርዝ የሚረጨው የመረጃ ቲቪ፣ ያለ አንዳች ሃፍረት ሃሰት የሚያራቡ ተከፋይ ቅጥረኞች፣ ዓለም ዓቀፍ ጋዜጠኛ ነን ባዮች፣ አገር ቤት ሆነው መርዝ የሚረጩ የነጻ ፕሬስ አቀንቃኞች ወዘተ ተባብረው እያተራመሱት ያለው የአማራ ክልል ኪሳቸው ምን ደረስ ሲያብጥ ከዚህ ተግባራቸው እንደሚታቀቡ ለመገመት አዳጋች ነው።
አንዳንዶቹ በልመናና በተቀጠሩበት ልክ በሚያገኙት ሃብት ውጭ ተቀምጠው የልጆቻቸውን ልደት፣ የሚስቶቻቸውን አኒቨርሰሪ፣ የራሳቸውን የባህር ላይ ውሎና እረፍት፣ የገዙትን ቤትና ዘመናዊ ተሽከርካሪ ሳይቀር በምስል ሲያሳዩ ምንም የማይመስላቸው፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአማራ ህጻናት ከትምህርት መለየታቸው ቁባቸው አይደለም። ደም በሰበር ዜና እየቸረቸሩ ቤተሰቦቻቸውን የደም አበላ የሚቀልቡት እነዚህ ዜጎች ከበቂ በላይ የትግል አጀንዳ ያለውን የአማራ ህዝብ የግል የንግድ ተቋቸው አድርገው እያፈረሱት ነው። ኢትዮጵያንም ለጠላት አሳብ አሳልፈው እየሰጧት ነው። በደሙ አገር ያቆመውን የመከላከያ ሰራዊትን እይንኳሰሱ ክንዱ በማላላት አገር እንድትበተን እየለፉ ነው። ለዚህ ተግባራቸው ስለሚከፈላቸው እዛም እዚሁም ሴራ እየጎነጎኑ፣ ሴራውን እየተነተኑ፣ ሴራው የሚያስከትለውን ውጤት ሰበር ዜና እያደረጉ ዘልቀዋል።
የአማራን ሕዝብ ካለበት ችግር አስፈንጥረው እንደሚያወጡ የተነገረላቸው ሶስት “አርበኞች” ጥንት እነ ንጉስ ዳዊት፣ ሳሙኤልና ሳኦል እንደተቀቡት አይነት ቅባት መቀባታቸውን በስፋት፣ በግልጽና በማብራሪያ የነዚሁ “ተቀቡ” የተባሉት መሪዎች አንደበት ሚዲያዎች ሲነገሩ የተሰማው በተደጋጋሚ ነው። እነሱም እስክንድር ነጋ፣ ዘመነ ካሴና አሰግድ መኮንን ናቸው። ይህ የሚሆነው ጉዳዩን ሃይማኖት ላይ አጣብቀውና ከመስቀል ጋር አብረው ገምደው ህዝብ ላይ ለመጫን ነው።
የቀቢዎቹ ማንነት በስም አለመታወቁ እንጂ፣ ያው ቅባቱ የተሰጠው በገዳማትና ታዋቂ ደብሮች ነው። ተቀቢዎቹ መሪዎች ማዕረጋቸውን ለማጽናት የበኩላቸውን ሲያደርጉና “ይሆነናል” ባሉት ልክ ሲጓተቱ መቆየታቸው የሚታወስ ነው። ንግስናቸውን እውን ለማድረግ አደረጃጀት እየቀየሩ ለጠቅላይ ሲሄዱ፣ መልሰው ሲያፈርሱና ሲጋጩ ከርመው ሰሞኑን እስክንድር ነጋ የፋኖ መሪ እንደሆነ ይፋ ሆኗል።
እስክንድር ነጋ የአማራ ፋኖ መሪ ሆኖ መመረጡን የዩቲዩብ ገጾች በሰበር ሲያጨሱት፣ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያቀጣጥሉት ወዲያውኑ ማስተንፈሻ ማዕበል ገጠመው። የአማራ ህዝብ አንድ መሪና ወጥ ዓላማና ግብ ያለው አደረጃጀት እንደሚያስፈልገው ሲወተውቱ የነበሩ “አሁን ነገሩ ቅርጽ ያዘ” ብለው ሳይጨርሱ ከጎጃምና ሸዋ እስክንድር ላይ የተቃውሞ ጥሪና እርምጃ እንዲወሰድ የሚያዝ ትዕዛዝ ተሰማ።
የሚዲያ ግብግቡን በዋናነት ሃብታሙ አያሌው ከእስክንድር ነጋ ወገን ሆኖ ከወያኔ ደጋፊ ሚዲያዎች ጋር ሲመራ ማክሸፊያውን ከጎጃምና ከሸዋ እያቀነባበረ ምናላቸው ስማቸው ይወዘውዘው ጀመር።
ከላይ የተገለጸው እንዳለ ሆኖ፣ ትናንት አብረው ሲሰሩ የነበሩት ሃብታሙና ምናላቸው በሁለት ክንፍ በፊት አውራሪነት የሚነዱት የፋኖ ትግል፣ ሌሎችም ፍልፍል ሚዲያዎች እዚያና እዚህ እየረገጡ የሚያተራምሱት የአማራ ፖለቲካ ለደጋፊውም ሆነ በገልለተኛነት ለሚከታተሉት ግራ የሚያጋባ ሆኗል። እነዚህ የሚዲያ ክንፎች በዋናነት ይጠቀሱ እንጂ ሌሎችም ያዋጣል ባሉት መስመር ግንኙነት መስርተው የሰበር ዜናውን ሰፈር የሚያሞቁ፣ አራት ኪሎ መደረሱን የሚያበስሩ “አጋር” ሚዲይዎች ትርምሱን በዘፈንና በከበሮ ሲያጅቡት፣ ዲያስፖራው እንደተለመደው ኪሱን ሲገለብጥ የሚታየው ድራማ ገራሚ ነው።
በዚህ የሚድያ አጀብ ተበጣጥሰው ለዲያስፖራው ተስፋ የሚሰጡትና ብር የሚቀበሉት በርካታ አደረጃጀቶች የፈጠሩት ትርምስ ክልሉን እንደ ክልል፣ ህዝቡንም እንደ ህዝብ ለከፋ መከራ መዳረጉን የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድ፣ የማዳበሪያ፣ የመሰረተ ልማት፣ የሰላም፣ የመታገት፣ ግብር ለማንም መክፍለ፣ እንደ ልብ መንቀሳቀስ አለመቻል… ወዘተ አስመልክቶ በየቀኑ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይም ህጻናት፣ እናቶችና አዛውንቶች፣ ተማሪዎቾ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር በታሪክም ጥቁር ጠባሳ ሆኖ የሚቀጥል እንደሆነ እየተነገረ ነው።
ይህ በንዲህ እንዳለ ትላንት እሁድ ቀን ለአቶ ምናላቸው ጊዮን ሚዲያ ቃለ ምልልስ የሰጠ የሸዋ ፋኖ እዝ መሪ አሰግድ መኮንን ቃለ ምልልሱ በተላለፈ ሃያ አራት ሰዓት ሳይሞላ ለመንግስት እጅ መስጠቱ ተሰማ። የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይልም ዜናው ትክክል መሆንን በይፋ መግለጫው አመልክቷል።
በሃይል አሰላለፉ መሰረት የአርበኛ፣ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች እስክንደር ነጋ የፋኖ መሪ ሆኖ እንደተመረጠ በሰበር ዜና መሰራጨቱን ተከትሎ፣ ይፋ በሆነው አሰላለፍ ከእነ ዘመነ ካሴ፣ ምሬ ወዳጆ፣ና አስረስ አማረ ጋር በአንድ መስመር የነበረው አሰግድ ኮምቦልቻ ከተማ እጅ ከሰጠ በሁዋላ አዲስ አበባ ደርሶ ከፋና ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል።
አሰግድ እጅ ከመስጠቱ አንድ ቀን ባለሞላ ጊዜ ለምናላቸው ስማቸው በሰጠው ቃለ ምልልስ ስለ እስክንድር ከተናገረው በተጨማሪ ጫጫን መቆጣጠራቸውንና አራት ኪሎ ለመድረስ መቃረባቸውን አስታውቆ ነበር። “እመነኝ” እያለ አሰግድ በሰጠው ቃለ ምልል
- እስክንድር የአማራ ሕዝብ ሾተላይ ነው
- ምርጫ በሚደረግበት ስብሰባ ላይ አንተ የአማራ ፋኖ ውስጥ ምን ልታደርግ ገባህ ስለው እመለሳለሁ ብሎ መድረኩን ረግጦ ወጣ
- ለምርጫ አስራ አራት መስፈርቶች ነበሩን፤ አንዱ የማንነት ጥያቄ ነው፤ ሌላው የሠራዊት ወዘተ፤ እስክንድር አስራ አራቱንም መስፈርቶች አላሟላም፣አላለፈም
- እስክንድር በወር እስከ 15ሺህ ብር እከፍላለሁ እያለ ወታደር ይገዛል
- ብርጌድ ጭምር ይገዛል
- እንዲህ ያለውን ሰው ነው እጩ ሆኖ እንዲመረጥ ያደረጉት
- ትግላችን አሁን ሰዎችን እያነጠረ ነው
- እስክንድርንም ሰዉ እንዲያውቀው ሆኗል
- ካሁን በኋላ ምንም የሚያስፈራ ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር ጠርቷል
- በቅርብ ጊዜ እውነተኛ የአማራ ልጆች አንድነት መሥርተው ይወጣሉ
- ምንም ነገር ቢፈጠር ከአሁን በኋላ የአማራን ትግል ከአራት ኪሎ የሚመልሰው የለም
- ይህንን በእርግጠኝነት እነግርሃለሁ
ሌላው አሰግድ ያነሳው ትልቁ ጉዳይ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ሲገደሉ እስክንድር ባህርዳር እንደነበር አንስቶ የሰጠው ማብራሪያ ነው። ዓመጹ በባህር ዳር በተቀጣተለበት እስክንድር ለምንና እንዴት ባህር ዳር ሊገኝ ቻለ?በዛን ቀውጢ ወቅት አሳምነው ሲገደሉ እስክንድር በምን ፍጥነትና ማን ከባህርዳር አሾልኮ አወጣው? የሜው አስግድ በእስክንድር ላይ በርካታ ጉዳዮችን ያነሳል። ጎጃም ላይ ታስሮ መፈታቱ፣ ከጎጃም ወደ ሸዋ የመጣበት ምክንያትና ከሻለቃ ዳዊት ጋር አብሮ የሆነበት መነሻ ቢመረመር በርካታ ጉዳዮች እንደሚገኙ ጠቅሷል። ሻለቃ ዳዊት አማራን ርስት አልባ፣ መሬት አልባ አስደርጎ በርሃብ ስም ካሰደደ በሁዋላ እየተፈናቀለ እንዲገደል ያደረገ ሰውና እስክንድር ምን አገናኛቸው? የሚለውን ጥያቄ አጉልቶ የተናገረው አሰግድ። እስክንድር ቀደም ባለው መጽሃፉ ከፕሮፌሰር አስራት ግድያ ጋር አገናኝቶ ስሙን ያነሳዋል። በቃለ ምልልሱ ላይም ይህንኑ ደግሟል።
“እስክንድር የአማራ ሕዝብ ሾተላይ ነው” ሲል አስተያየቱን በማብራሪያ ያጀበው አሰግድ በዚህና በበርካታ ምክንያቶች እስክንድርን ይከሳል። ይህን ቃለ ምልልስ በልበ ሙሉነት የሰጠው አሰግድ ታዲያ ይህን ባለና “ጀግና” እየተባለ አበባ እየተረጨለት ሳለ አንድ ቀን ሳይሞላ ኮምቦልቻ መገኘቱ የተለያየ ስሜት ፈጥሯል።
ምናላቸው ስማቸው እያነጋገረው እያለ ስልኩ ተጠልፎ ተከቦ መያዙን በመግለጽ የቢሆን ትንተና የሚሰጡ ምናላቸው ስማቸው ሆን ብሎ እንዳሲያዘውና ይህንኑ ለማድረግ ከብአዴን ሰዎች ጋር መምከሩን ይጠቅሳሉ። በዛው አያይዘው ኤመስቀል ይዞ ለሚያጭበረብረው ዘመድኩን በራቸውን ከፍተው ጉድ ሆኑ” ሲሉ የገለጹም አሉ። አሰግድ ግን በፋና ቲቪ በቀረበ ቪዲዮ የሚከተለውን ብሏል።
እርስ በርስ ከተጫረስን ምን ዋጋ አለው። ማጀቴን መጥተው ወረሩ። ዘረፉ፣ ገደሉ። ብዙ አደረጉ። ህዝብ እንዳይሞት የኔ ሃይሎች ለቀው እንዲወጡ አዘዝኩ …. የአማራ ትግል የግል የንግድ ተቋቸው ያደረጉት፣ የሚዘርፉበት ሆኗል። የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው የውጭ ሃይሎች ጠልፈውታል።
ዝግጅት ክፍሉ ያነጋገራቸው እንደሚሉት የአማራ ህዝብን የሚመጥኑ ወገኖች ዝምታቸውን ሰብረው ጣልቅ ሊገቡና ከየትም እየተነሱ ክልሉን የሚያተራምሱ፣ የአማራን ፖለቲካ የሚያንቦጫርቁትን ” በቃችሁ” ሊሉዋቸው ይገባል። ታላቅ አጀንዳ ያለውን ህዝብ ማንም መንገደኛና ድንኳን ሰባሪ ሊደንስበት እንደማይገባ ይገልጻሉ። አሰግድ “እመክራለሁ” ሲል መጨረሻ ላይ “የባሰው እንዳይመጣ” እንዳለው እንዳይሆን ሃላፊነት የሚሰማቸው ወገኖች የአማራን ጉዳይ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ሆኖ ሊያስተካክሉ ይገባል።