የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጸጥታ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል።
ክልሉ የገጠመውን ችግር ለመቀልበስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ወደ ሥራ ከተገባበት ጊዜ ጀምሮ በከተማ አሥተዳደሩ ራሱን የቻለ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ሲሠራ እንደቆየ አንስቷል።
የፌደራል፣ የክልል እና የከተማዋ የጸጥታ ኃይሎች ባደረጉት ብርቱ ተጋድሎ እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ባሳዩት የጸና ሰላም ወዳድነት የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታው ከጊዜ ጊዜ እየተሻሻለ እንዲመጣ ማድረግ እንደተቻለ ገልጿል።
በተሠራው ክንውንም የከተማ አሥተዳደሩ የታቀዱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊ እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ማከናወን እንደተቻለ ተገልጿል። በሂደቱም ተጨባጭ ውጤትም ማስመዝገብ ተችሏል ብሏል የከተማዋ ጸጥታ ምክር ቤት።
የባሕር ዳር ከተማን ዘመናዊ ለማድረግ አዳዲስ እና ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ተጀምረው በመሠራት ላይ እንደኾኑም አመልክቷል።
እነዚህን የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች በተጀመሩበት መንገድ አጠናክሮ ለማስቀጠል እና የሚታዩ ችግሮች በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ምክር ቤቱ በጥልቀት ተወያይቷል ።
ምክር ቤቱ በውይይቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት እና መልካም አሥተዳደር ሥራዎች ያለምንም እንቅፋት እንዲከናወኑ አሁንም በከተማዋ አንዳንድ የጸጥታ ስጋቶችን ማስወገድ እንደሚገባ መክሯል።
በተጨባጭ እየታዬ ያሉ የጸጥታ ችግሮችንም በዝርዝር ተመልክቷል። በመኾኑም የጸጥታ ችግሮችን መከላከል እና መፍታት የማይታለፍ እና ችላ የማይባል እንደኾነ በምክር ቤቱ ታምኖበታል።
ምክር ቤቱ ለእነዚህ ችግሮች እና ክስታቶች አባባሽ ምክንያቶችን በዝርዝር የለየ ሲኾን በተለይ አብዛኞቹ ችግሮች የሚፈጸሙት በባጃጅ ተሽከርካሪዎች በመታገዝ መኾኑን ተመልክቷል።
ይህን መሠረት ባደረገ እና ሌሎችን ጉዳዮች ባካተተ መንገድ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጸጥታ ምክር ቤት የክልከላ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በዚህም መሠረት-
1ኛ – በተሽከርካሪዎች ላይ የተጣሉ ክልከላዎች:-
- ማንኛውም ተሽከርካሪ ታርጋ ሳይኖረው ወይም ሳያስር መንቀሣቀሥ የተከለከለ ነው።
- ከተፈቀደላቸው ተሽከርካሪዎች ውጭ ስቲከር መለጠፍ የተከለከለ ነው።
2ኛ- የባጃጅ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች እና ማኅበራት ላይ የተደረጉ ክልከላዎች እና ለባሕር ዳር ከተማ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተሰጡ ግዴታዎች:-
- ከዛሬ ጀምሮ ማንኛውም ባጃጅ መጋረጃ እና የግራ ጎን ሸራን ሳያነሱ ማሽከርከር በፍጹም የተከለከለ ነው።
- የባጃጅ ተሽከርካሪ ማኀበራት ከተሰጣችው የሥምሪት ቦታ ውጭ ማሽከርከር አይፈቀድም።
- በባሕዳር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ተመዝግበው በማኀበራት ተደራጅተው ሥምሪት ከተሰጣቸው ባጃጆች ውጭ ማሽከርከር የተከለከለ ነው።
- የባጃጅ ተሸከርካሪዎች የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት በአዲስ የሚሰጠውን መለያ ወይም ባር ኮድ ግልጽ እና በሚታይ መንገድ የመለጠፍ ግዴታ አለባችው።
- የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፓርት ጽሕፈት ቤት ከላይ የተገለጹትን ግዴታዎች ላላሟሉ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች ምንም አይነት ሥምሪት እንዳይሰጥ ተወስኗል።
- የባጃጅ ባለ ንብረቶች ለቀን ገቢ ወይም ለተለያዩ የጊዜ ገደብ ለሚያከራዮቸው ግለሰቦች የውል ስምምነት በመያዝ ለፓሊስ እና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ማሳወቅ አለባቸው።
- ለባጃጅ ተሸከርካሪዎች ከቀኑ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ማሽከርከር የተከለከለ ነው። ወይም ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ማሽከርከር የተከለከለ ነው።
3ኛ. ባለ 2 እግር ሞተር ተሽከርካሪ በከተማው ላልተወሰነ ጊዜ ማሽከርከር የተከለከለ ነው።
4ኛ. የመኪና እና የሰው እንቅሥቃሤን በተመለከተ:-
- ለኅብረተሰቡ ቀጥተኛ አገልግሎት የሚሰጡ የቤት መኪና፣ ታክሲ፣ የመንግሥት መኪና፣ ማንኛውም የጭነት መኪና ተሽከርካሪ እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ድረስ ብቻ ማሽከርከር የተፈቀደ ሲኾን ከተፈቀደው ሰዓት እላፊ ሲያሽከረክሩ መገኘት ግን በሕግ ያስቀጣል።
- የሰው እንቅስቃሴም በተመሳሳይ እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት የተፈቀደ ሲኾን ከተፈቀደው ሰዓት በኋላ መንቀሣቀሥ ግን የተከለከለ ነው።
5ኛ. ይህ ክልከላ የማይመለከታቸው ተሽከርካሪዎች በጸጥታ ሥምሪት ላይ የሚገኙ፣ አንቡላሶች፣ የእሳት አደጋ መኪናዎች ናቸው። ነገር ግን በማንኛውም ሰዓት በአንቡላንስም ኾነ በሌሎች ተሽከርካሪዎች ላይ ፍተሻ ይደረጋል ።
6ኛ. በጦር መሣሪያ አያያዝ ላይ የተደረገ ክልከላ:-
- ከጸጥታ መዋቅሩ አባላት እና ለጸጥታ ሥራ ተሰማርተው የመንቀሣቀሻ ፈቃድ ከተሰጣቸው ሰዎች ውጭ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሣቀሥ የተከለከለ ነው።
- ማንኛውም የጸጥታ አባል ከሥምሪት ውጭ በሚኾንበት ጊዜ ሲቪል ለብሶ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሣቀሥ ክልክል ነው።
7ኛ. በከተማችን የሚገኙ ቤት አከራዮች እና ተከራዮች ማሟላት የሚኖርባቸው ግዴታዎች፦
- አከራዮች የአከራይ ተከራይ ውል በመያዝ ለቀበሌው አሥተዳደር እና በአቅራቢያቸው ለሚገኙ ፓሊስ ጣቢያዎች የውል ኮፒ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው።
- በተመሳሳይ ተከራይ የተከራየበትን ውል ይዞ መገኘት ይጠበቅበታል። ይህ ሳይኾን ቀርቶ ተከራይ በወንጀል ወይም በሌላ በሕገ-ወጥ ድርጊት ተሠማርቶ ቢገኝ አከራይ ጭምር በሕግ ተጠያቂ ይኾናል።
8ኛ. የክልከላዎች እና ግዴታዎች ተፈጻሚነትን በተመለከተ:-
- የተሽከርካሪ ክልከላዎችን ተላልፎ በተገኘ ማንኛውም ተሽከርካሪ ላይ የከተማ አሥተዳደሩ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት እንደየ አግባቡ እርምጃ ይወስዳል፣ በሌሎች የሕግ አካላትም ተጠያቂ እንደኾን ይደረጋል።
- ክልከላውን ጥሶ የጦር መሣሪያ ይዞ የሚገኝ የጦር መሣሪያውን እንደሚነጠቅ ከባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።