የገዛ ልጁን አንድ እንቁላል ሰርቀሃል በሚል የግራ እጁን 5ቱን ጣቶቹ በእሳት አቃጥሎ ከባድ የአካል ጉዳት ያደረሰ ተከሳሽ አባት በእስራት መቀጣቱን ተገለፀ። የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመዉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዲዮ ዞን ይርጋ ጨፌ ወረዳ ዉስጥ ነዉ።
ተከሳሽ ጌታቸው ገመዴ ህርባዬ የእስራት ቅጣቱ ሊወሰንበት የቻለዉ መስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 2:00 ላይ በይርጋጨፌ ወረዳ ቀዲዳ ቀቀሌ ልዩ ቦታ ሞቶቃሞ ህዋስ ላይ በልጁ ላይ ከባድ የአካል ጉዳት በማድረሱ ነዉ።
የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ተከሳሽ ጌታቸው ገመዴ ህርባዬ የተባለዉ ግለሰብ የገዛ ልጁን የሆነውን የ13 ዓመት ህፃን እንቁላል ሰርቀህ ሽጠህ በልተሃል በማለት ሁለቱን እጅ በገመድ ጠፍሮ በማሰር እሳት እስክጋል ድረስ አንድዶ ጭካኔ በተሞላ ያቃጠለና ከፍተኛ የአካል ጉዳት አደርሶበታል ።
ጉዳት የደረሰው ህፃን የድረሱልኝ ጩኸት ቢያሰማ የደረሰለት አካል አለመኖሩን ነዉ የተገለፀዉ።በፖሊስ መረጃ ሲደርሰዉ ተጎጂዉን ታዳጊ ወደህክምና ወስዶ ህክምና እንዲያገኝ ማድረጉ ተብራርቷል።

በታዳጊዉ ላይ የተፈፀመበት ወንጀል ምክንያት የግራ እጁን 5ቱም ጣቶች በደረሰው እሳት ቃጠሎ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የእጅ ጣቶቹ አንድ ላይ ተጣብቀው የማያገለግሉ እና አካል ጉዳት ተዳርጓል ሲል ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሶ ግለሰቡን ከባድ አካል ጉዳት በማድረስ ወንጀል ክስ መስርቶበታል።
በታዳጊዉ ላይ ነደረሰዉን ወንጀል የይርጋጨፌ ወረዳ አቃቤ ህግና ሴቶችና ህፃናት ጉዳዮች ጽ/ቤት በጋራ በመሆን ወንጀለኛው ለህግ ቀርቦ ተገቢዉን ውሳኔ እስክያገኝ ሲከታተሉ ቆይተዋል።
የይርጋጨፌ ወረዳ ፍርድ ቤት የወንጀሉን መዝገብ ሲመረምር ቆይተው ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሸ ጌታቸው ገመዴ በ4 ዓመት ፅኑ እስራት እንድቀጣ ሲወሰንበት ፍርድ ቤቱ ተጎጅው ህፃን ሀዋሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህክምናውን እንድከታተልም ጨምሮ ስለማዘዙ ከይርጋጨፌ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተገኘዉ መረጃ ያመለክታል።