ሱዳን ለዚህ የበቃችው በርካታ ክምር ችግሮች ቢኖሩባትም በዋናናት ከአገሪቱ መንግስት እኩል ሃይል ገንብቶ ክንዱን ያፈረጠመ ሃይል መፈጠሩን ተከትሎ ነው። የውጭ ሃይሎች ወገን ለይተው እጃቸውን የከተቱባት ሱዳን ቀስ እያለ ወደ ቀውስ ውስጥ ስትገባ ቀውሱ እዚህ ደረጃ ይደርሳል ብለው ያሰቡ አልነበሩም። ግን ሆነ።
ትህነግ መንግስት እያለ በጓሮ የራሱን ክንድ በመንግስት በጀትና ቁስ አደራጅቶች ” በቃህ” ሲባል ከቆሰቆሰው ጦርነት ጋር በተያያዘ ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልል ሰፊ ቀውስ የደረሰ ሲሆን በመላው አገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንድትወድቅ ምክንያት መሆኑ አይዘነጋም። በትግራይ ህይወታቸው ያለፈውን ምስኪኖች የሚያውቁት ኦና ቤት የታቀፉ ወላጆች ብቻ ናቸው። ከውድመትና ኪሳራ ያልተላቀቀው የአማራ ክልል የትግራይ ጦርነት የወለደው ሃይል እያካሄደ ባለው ትርጉሙና ዓላማው ግራ በሚያጋባ ጦርነት ዳግም የተረፈውን ሃብቱን፣ ልጆቹን፣ የለማት ተቋማቱ እያጣ ነው። መነሻው ሲታይ ኢመደበኛ የሆነ አደረጃጀት ክንዱን ማፈርጠሙና በውጭና በውስጥ ሃይሎች መደገፉ ነው። ዛሬ ሱዳን እየሆነ ያለው ሁሉ ለኢትዮጵያዊያን ልዩ ትምህርት የሚሰጠውም በብዙ ምክንያት ተመሳሳይነት ስላለው ነው።
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር የተጀመረው የሱዳን ጄኔራሎች ፍልሚያ ሚሊዮኖችን አፈናቅሎ ካርቱምን ለከባድ የሰብዓዊ ቀውስ አጋልጧል፡፡ ይህ ቀውስ እንዲያበቃ ዓረብ ኤምሬትስ ሁሉንም አማራጮች እንደምትደግፍ አስታወቀች። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በፖርት ሱዳን ያደረጉትን ጉብኝትና ውይይት ተከትሎ የሱዳን ቀውስ የሚቆምበት ፍንጭ መሰማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የዓለም ዜና ግንባር አድርጓቸዋል።
የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አብዱልፈታል አልቡርሃን ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ተከትሎ ነው ዜናው የተሰማው። በውይይታቸውም ሱዳንን ከገባችበት ቀውስ በሚያስወጡ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን የዘገበው የኤምሬትስ ዜና ወኪል ዋም ነው።

“ጉዞው ለሱዳን መረጋጋት የሚያከናውኑት ጥረት ቀጣይ እርምጃ ነው” ሲል የውጭ ጉዳይ ይፋ እንዳደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሱዳን ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለማግዝ የሱዳን የወደብ ከተማ ወደ ሆነችው ፖርት ሱዳን ሱዳን ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ከአገሪቱ ጦር ኃይሎች አዛዥ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
በጄኔራል አል ቡርሐን በሚመራው በሱዳን ጦር ሠራዊትና በጄኔራል ዳጋሎው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል በተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ሱዳን ቀውስ ውስጥ ትገኛለች። በአስራ አምስት ሺህ በላይ ሰዎች ተገለዋል። ከሰላሳ ሶስት ሺህ በላይ ቆስለዋል። አስራ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ምስኪን ዜጎች ተፈናቅለዋል። አገሪቱ በቀውሱ እየወደመች ነው። ረሃብና ጠኔ ተባብሷል። እርዳታ ለማድረስ እንኳን አልተቻለም። ይህ ሁሉ ሱዳን ውስጥ የሚሆነው በውጭ ሃይሎች የተለያየ ፍላጎት መሆኑ ደግሞ ዜናውን ሁሉ አሳዛኝ ያደርገዋል።
ወባ፣ ተቅማጥ፣ ኤች አይ ቪ፣ የተለያዩ ቋሚ ክትትል የሚያሻቸው ህመሞች፣ ህጻናት፣ ነብሰጡር እናቶች፣ ህክምና ማግኘት አልቻሉም። ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ወድመዋል። ቁስ አልባ ሆነዋል። መድሃኒት የላቸውም። ሱዳን አገሪቱም ህዝቧም በውጭ ሃይሎች የተለያየ ፍላጎት ምነሻ እየጠፉ ነው።
አብይ አህመድ ሱዳን ደርሰውና በሚስጢር መክረው ከመጡ በሁዋላ፣ ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ባደረጉት የስልክ ውይይት ለሠላማዊ ንግግር፣ ለሱዳናውያንን ፍላጎት፣ ደኅንነት እና መረጋጋት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ መጠቆማቸው ተሰምቷል።
በጄኔራል ዳጋሎው የሚመራዉን የፈጥኖ ደራሽ ሃይል እንደሚደግፉ የሚነገርላቸው ፕሬዚዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ፣ ኤምሬትስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሱዳናውያን የሰብዓዊ ድጋፍ መላኳን እንደምትቀጥል በመጥቀስም ሁሉንም የሠላም አማራጮች እንደምትደግፍ አመክተዋል። የፕሬዚዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድና በጄኔራል አል ቡርሐን መካከል የስልክ ውይይት መደረጉን መሰማቱን ተከትሎ ሱዳን ወደ ሰላማዊ ውይይት ልትመለስ እንደምትችል በርካቶች አስተያየት እየሰጡ ነው። ምክንያቱም ሼኽ መሃመድ ዳጋሎ ላይ ጫና ማድረግ ስለሚችሉ ነው።
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር የጀመረው የሁለቱ ጄኔራሎች ፍልሚያ አርባ ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ ያላትን ሱዳን በዓለማችን ከባድ የሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ካሉ ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ አስቀምጧታል። በዚህ አያያዙ ከቀጥለ የሱዳን ጉዳይ ለዘገባም የሚከብድ እንደሚሆን በርካቶች እየወተወቱ ነው። እየቃተቱ ነው።
የመንግሥታቱ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ሃያ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሱዳናውያን ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር ገጥሟቸዋል። አስጊ ከሚባለው ደረጃ ባለፈ ቀውስ ውስጥ ናቸው።
የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) የጀመሩትን ጦርነት በንግግር እንዲቆም ሳዑዲ ዓረቢያ እና አሜሪካ በጂዳ ካደረጉትና በአጭሩ ከተቋጨው ሙከራ ውጭ እስካሁን ተስፋ ሰጪ ንግግር አልተካሄደም። የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና የሱዳን ጎረቤቶች ተፋላሚ ጄኔራሎቹን ፊት ለፊት ለማገናኘት ያደረጉት ሙከራም አልተሳካም።
የመዲናዋን ካርቱም አብዛኛው ክፍል፣ አል ጀዚራ ግዛት፣ አብዛኛውን የዳርፉር እና ኮርዶፋን አካባቢ የተቆጣጠረው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምስራቅና ምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍልም ድል እየቀናው መሆኑን በቅርቡ ቪኦኤ ይዞት የወጣው ዘገባ ማሳየቱ አይዘነጋም። ከ10 ሺህ በላይ ንጹሐንን ሕይወት የቀጠፈው ጦርነት እንዲቆም ተማጽኗቸውን ቀጥለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በተደጋጋሚ ካደረጉት የሽምግልና ሙከራ ሁሉ የላቀ የተባለው በዚህ ቀውስ ፖርት ሱዳን ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ለሰላም ውይይት ማምራታቸው ነው። ይህንኑ ተከትሎ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ዜና መሰማታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን የዓለም ዜና የሰሞኑ ግንባር አድርጓቸዋል።