የተማሪዎችና የሰላማዊ ዜጎችን ዕገታ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሆነ ዓመታት አስቆጥሯል። ጉዳዩ ፖለቲካ መሆኑ ይፋ ቢሆንም አንድም አካል ሃላፊነት ወስዶ በይፋ እገታ ስለፈጸመበት ምክንያትም ሆነ ምን ለመደራደር እገታው እንደተፈጸመ አይገለጽም። ዜናውን የሚበትኑት አካላትና ሚዲያዎችም ይህ የሚያስጨንቃቸው አይመስልም። የእገታ ዜና በተሰማ ቁጥር ከየአቅጣጫው የሚወረወረው ዜና ከራስ የፖለቲካ ፍላጎትና መንግስትን ለመዝለፍ ፍጆታ ስለሚውል መረጃው የተዛባ እየሆን ዜጎችን እየረበሸ ነው። ሰሞኑን የሆነውም ይህ ነው።
ከአማራ ክልል ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በሦስት በአውቶብሶች ሲጓዙ የነበሩ ከ160 የሚበልጡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሰኔ 25/2016 ዓ.ም. ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ውስጥ በታጣቂዎች መታገታቸው ይታወሳል።
ታጋቾቹ አብዛኞቹ የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መሆናቸው የታወቀ ሲሆን፤ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ አካባቢ “ሸኔ” በተባሉ ታጣቂዎች መታገታቸውን ከእገታው ያመለጡ ተማሪዎች እና የታጋች ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በታጣቂች ታግተው የተወሰዱት ከ160 በላይ ተማሪዎች ተለቀዋል ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አስታውቋል፡፡ የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በትናንትናው እለት በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ ያወጣው መረጃ የታገቱት ተማሪዎች መንግስት እና ህዝብ በወሰዱት የተቀናጀ ኦፕሬሽን እንደሆነ አመልክቷል። ይህንኑ መረጃ ጠቅሰው የተለያዩ ሚዲያዎችና ግለሰቦች ክልሉ መዋሸቱን እየጻፉና እያሰራጩ ነው።
“የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ባለፈው ሳምንት በታጣቂዎች የታገቱ አብዛኞቹ ተማሪዎች መለቀቃቸውን ቢገልጹም የታጋች ቤተሰቦች ግን ተማሪዎቹ አሁንም ታግተው እንዳሉ ተናገሩ” ይላል የቢቢሲ ዘገባ።
ቢቢሲ ኢሰማኮ የመንግስት ባለስልጣናትን ባገኘው መረጃ እንደነገረው ከሆነ 138 የሚሆኑት መለቀቃቸውን ዘግቧል። በዛው ዘገባ “አንድ የታጋች ቤተሰብ” እያለ መቶ የሚሆኑት ታጋቾች ሙሉ በመኡሉ እንዳልተለቀቁ በመጥቀስ የኦሮሚያ ባለስልጣናት የቅጥፈት ዜና መናገራቸውን አስፍሯል።
አሁን ላይ በጋዜጠኛነት ስራ እንደማይሰሩ የሚናገሩት አቶ ኤሊያስ መሰረት “በተደረገ ጥብቅ ኦፕሬሽን ከ167 ታጋች ተማሪዎች መካከል 160ዎቹ ተለቀዋል” ሲሉ የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ መናገራቸውን ጠቅሶ በኤክስ ገጻቸው ላይ የሚከተለውን አስፍረዋል።
“እውነት ይሆን? ብዬ የታጋቾች ቤተሰቦችን፣ የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ወንጌላዊያን ህብረትን እና የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንትን ማምሻውን ጠየቅኩ። ምላሹ ይህን ይመስላል” በለው የጥርጣሬያቸውን መነሻ ሳይዘረዝሩ ማጣራት ማካሄዳቸውን ይገልጻሉ።
“አሁንም ልጆቻችን በእገታ ስር ናቸው፣ የማስለቀቂያ ገንዘብ ከህዝብ እየለመንን ነው። በዚህ ግዜ እንዲህ አይነት መረጃ ማውጣት የጭካኔ ስራ ነው” የሚለውን የታጋቾች ቤተሰቦች እንደነገሯቸው ያመለክታሉ። የታጋቾች ቤተሰቦች ሲሉ ምን ያህሉን እንዳናገሩ፣ ታገቱ የተባሉት ተማሪዎች ቤተሰቦች ሲሉ የት የሚኖሩትን እንደሆነ አቶ ኤሊያስ አላስታወቁም።
“ታግተው ያሉ በርካታ ተማሪ አልተለቀቁም፣ ተለቀቁ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ከየት እንደመጣ አናውቅም” የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ወንጌላዊያን ህብረት ምላሽ እንደሰጣቸው የጻፉት አቶ ኤሊያስ መሰረት ተማሪዎቹ ደባርቅን ለቀው ከወጡ ከደባርቅ ዩኒቨርስቲ እንዴት የተሟላ መረጃ ማግነት እንደሚቻል ሳይተቅሱ የዩኒቨስርስቲውን ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስማማው ዘገዬን አነጋግረዋል። “አንዴ መረጃ ሰጥቻለሁ፣ እኔ ጋር ለምን ትደውላላችሁ?” የሚል መልስ እንደሰጡዋቸው ጽፈዋል።
ቢቢሲም ሆነ አቶ ኤሊያስ ልጆች የታገተባቸውን ቤተሰቦች “እንድ” በሚል ሲገልጹ ለምን ስምና አድራሻን ማስታወቅ እንዳልፈለጉ ያሉት ነገር የለም። ተማሪዎቹ ዳባርቅ ዩኒቨርስቲ የሚማሩ የለኤላ አካባቢ ተወላጆች መሆናቸውን የሚጠቅሱ ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ አንቂ ነን ባዮች ለሚሰራቸው ዜና እርምት እንዲሆን ያሉትን ጽፈው አሰራጭተዋል።
“የታገቱት ተማሪዎች ለእረፍት ወደ ቤተሰቦቻቸው እየተመለሱ ያሉ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንጂ የደባርቅ ነዋሪዎች አይደሉም” ይላል ናትናኤል መኮንን። ይቀጥልና “አንዳንዶች ሙሉ መረጃ በሌላቸው ጉዳዮችም ላይ የማይሆን ነገር መጻፋቸውን ታዚቢያለሁ። ህዝብን ለማደናገር” እንደሆነ ያመልክታል።
ናትናኤል እንደሚለው የታገቱት ተማሪዎች በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኘው ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ የኦሮሚያና የሌሎች ክልሎች ተወላጆች ናቸው። ይህን ካለ በሁዋላ “መረጃ አለኝ የምትሉ ሰዎች ወይም ጉዳዩን እውንታ ማጣራት የምትፈልጉ ጋዜጠኞች ወደ ኦሮሚያ ክልል በተለይ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የወለጋ ልጆች ስለሆኑ ወደ ወለጋ ደውላችሁ እውነቱን ለህዝብ አድርሱ” ሲል ይመክራል። ሲያጠቃልልም መረጃ ለመውሰድ ደባርቅ ዩኒቨርስቲ ሳይሆን ወለጋ ወይም ኦሮሚያና ሌሎች ክልሎችን ማግኘት እግባብነት እንዳለው ያመልክታል። እንደ ጥቆማው ከሆነ ልጆቹ ከአማራ ክልል ደባርቅ ስለወጡ ትክክለኛ መረጃ የሚገኘው አሁን ላይ ደባርቅ ሊሆን የማይችልበትን አመክንዮ ያሳያል።
አቶ ኤሊያ መሰረት@EliasMeseret ባሰራጩት ዜና ስር ” ልጄ ታገተ ብሎ መናገር ለምን ያስፈራል? ምንስ ችግር አለው?” የሚል ጥያቄ ቀርቧል። በአብዛኛው ተለቀዋል የሚለውን ዜና ሳይሆን ” አልተለቀቁም፣ መንግት ላይ ተስፋ ቆርተዋል፣ መንግስትን አይምኑም ወዘተ” በሚሉ ተቀጽላዎች የታጀበው የዕገታ ሪፖርት በርካቶችን ግራ ያጋባውም በዚህና በበርካታ ምክንያቶች ነው።
ሲጀመር በተለያዩ ጊዜያት እገታ ሲፈጸሙ የቆዩ በስም የሚታወቁና የማይታወቁ አካላት ለድርጊታቸው ሃላፊነት አይወስዱም። ምን እንዲፈጸምላቸው አስበው እገታ እንደሚፈጽሙ አያስታውቁም። በመቶ የሚቆተር ተማሪዎች ታግተው ሲነዱ የሚመከቱ ለህግ አካላት ወዲያውኑ ሪፖርት አይደርጉም። በመቶ የሚቆጠሩ ታጋቾች በቀያቸውና ደጃቸው፣ በማሳቸው በታጣቂዎች ሲነዱ ነዋሪዎች ፈጥነው መረጃ የማይሰጡ ከሆነ አጋቾቹ ከሩቅ መጡ ለማለት እንደሚቸገሩ በርካቶች ይናገራሉ።
በዚህ መነሻ እገታው ዓላማና ከጀርባው ፖለቲካዊ ጥያቄ ከሌለው በየመንደሩ የተደራጁ ቡድኖች የሚፈጽሙት ተግባር ከመሆን አያልፍም። ለዚህ ነው የእገታ ዜና ሲሰማ፣ ዜናውን የሚያቀጥጥሉት ወገኖች ጉዳይም አብሮ የሚነሳው። አብርሃም ሃይሌ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ” እገታ ኢትዮጵያ ውስጥ ሴራ ተኮር ድራማ ነው። ዜናውን የሚያጨሱት ወገኖች በአብዛኛው በሰብአዊነት ሳይሆን ከራሳቸው፣ ወይም ከተቀጠሩለት ዓላማቸው አንጻር የሚቃኙት ጉዳይ ነው” በሚል አዘኔታቸውን ጠቅሰው መናገራቸው ይታወሳል። ሳትታገት ታገተች የተባለውችውንና ሰፊ የሚዲያ ሽፋን አግኝታ የነበረችውን እንስት አንስተው ግርምታቸውን ገልሰው ነበር እኚሁ አስተያየት ሰጪ የቋጩት።
ዜናውን መጀመሪያ የሰራው ቲክቫህ ኢትዮጵያ አንድ ያመለተ ልጅ እንደነገረው ጠቅሶ ዜናውን ሲያሰራጭ እንዳለው ሰኞ ዕለት ከደባርቅ ዩኒቨርስቲ በአውቶብስ ተሳፍረው ወደ ቤተሰብ እየተጓዙ የነበሩ ተማሪዎች ገብረ ጉራቻ ከተማ ሲደርሱ በታጣቂዎች መታገታቸውን አንድ ያመለጠ ተማሪ አረጋግጦ ነበር። ቲክቫህ ያነጋገረው ይህ ተማሪ “ሁለት አውቶብስ ተማሪዎች በታጣቂዎች ታግተዋል” ነበር ያለው።
ከቀን በሁዋላ በተሰማ ዜና በርካታዎቹ ያለምንም ክፍያ ተለቀዋል። የተረፉት እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር እየተጠየቁ ነው። እገታው እንደተፈጸመ “ መከላከያ አብዛኛዎቹን ልጆች አስመልሶ መከላከያ ካምፕ ውስጥ ያደሩ ልጆች እንዳሉ፣ የተወሰኑ ደግሞ በሌላ መኪና ተሳፍረው አዲስ አበባ መግባታቸውን የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አስታወቀዋል” ሲል ቲክቫህ በዘገባው አካቷል። እንግዲህ ኦሮሚያ ይህንኑ ዜና ሲደግመው አቶ ኤሊያስ መሰረትን ጥርጣሬ ውስጥ የከተታቸው ዋና ቁልፍ ጉዳይ ምን ይሆን? የሚለው ጥያቄ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።
ከ2ኛ እስከ 4ኛ ዓመት ተማሪዎች መታገታቸውን የዓይን እማኞች፣ የታጋች ቤተሰብና ዩኒቨርሲቲው አረጋጠው መስክረው ተጨማሪ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። እንደተባለው ከሆነ ሁለት አውቶብሶች ከደባርቅ፣ አንድ ደግሞ ከባህር ዳር ሰው ሞልተው ሲጓዙ የነበሩት አውቶቡሶች ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች የታገቱት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገብረ ጉራቻ አካባቢ ነው። አጋቾቹም የሸኔ ታጣቂዎች እንደሆኑ ተመልክቷል። ከእገታው የተወሰኑ ተማሪዎች ሲያመልጡ ዛሬ ደግሞ የተወሰኑት 150 የሚደርሱ መለቀቃቸውን ቲክቫክ ቤተሰቦቻቸውን ጠቅሶ ዘግቧል። በሚል መዘገባችን ይታወሳል።